YouVersion Logo
Search Icon

1 ተሰሎንቄ ሰዎች 1

1
1የእግዚአብሔር አብና የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወገኖች ለሆኑ ለተሰሎንቄ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን፥ ከጳውሎስ፥ ከሲላስና ከጢሞቴዎስ የተላከ መልእክት ነው፤ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። #ሐ.ሥ. 17፥1።
የተሰሎንቄ ሰዎች ሕይወትና እምነት
2እኛ ሁልጊዜ እናንተን በጸሎታችን እያስታወስን ለእግዚአብሔር ምስጋና እናቀርባለን። 3በአምላካችንና በአባታችን ፊት እምነታችሁ የሚሠራውን፥ ለፍቅር የምታደርጉትንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያላችሁን ተስፋ በትዕግሥት መጠባበቃችሁን ሳናቋርጥ እናስታውሳለን። 4በእግዚአብሔር የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንደ መረጣችሁ እናውቃለን። 5ወንጌላችንን ያበሠርንላችሁ በቃል ብቻ ሳይሆን በኀይልና በመንፈስ ቅዱስ፥ ስለ ወንጌልም እውነት እርግጠኞች በመሆን ነው፤ ከእናንተ ጋር በነበርንበት ጊዜ ለእናንተ ስንል እንዴት እንደ ኖርን ታውቃላችሁ። 6ብዙ መከራ ቢደርስባችሁም እንኳ ከመንፈስ ቅዱስ በተገኘ ደስታ አማካይነት ቃሉን ተቀብላችሁ የእኛንና የጌታ ኢየሱስን አርአያ የምትከተሉ ሆናችኋል። #ሐ.ሥ. 17፥5-9። 7ስለዚህ በመቄዶንያና በአካይያ ለሚገኙት ምእመናን ሁሉ መልካም ምሳሌ ሆናችኋል። 8የጌታ ቃል ከእናንተ ወጥቶ የተሰማው በመቄዶንያና በአካይያ ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር ያላችሁ እምነት በሁሉ ቦታ ታውቆ ነበር፤ በዚህ ምክንያት እኛ ስለዚህ ጉዳይ ምንም መናገር አያስፈልገንም። 9ወደ እናንተ በመጣን ጊዜ እንዴት እንደ ተቀበላችሁን ሕያውና እውነተኛውን አምላክ ለማገልገል ከጣዖቶች ተለይታችሁ ወደ እግዚአብሔር እንዴት እንደ ተመለሳችሁ እነዚያ ሰዎች ራሳቸው ይመሰክራሉ። 10እንዲሁም እግዚአብሔር ከሞት ያስነሣውን፥ ከሚመጣው ቊጣ የሚያድነንን፥ የልጁን የኢየሱስን ከሰማይ መምጣት እንዴት እንደምትጠባበቁም ይመሰክራሉ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in