YouVersion Logo
Search Icon

1 ተሰሎንቄ ሰዎች 2

2
የጳውሎስ ሐዋርያዊ ሥራ በተሰሎንቄ
1ወንድሞች ሆይ! የእኛ ወደ እናንተ መምጣት ፍሬቢስ እንዳልሆነ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። 2እናንተ እንደምታውቁት ከዚህ ቀደም በፊልጵስዩስ በነበርንበት ጊዜ መከራና ስድብ ደርሶብናል፤ ነገር ግን ታላቅ ተቃውሞ ቢደርስብንም እንኳ ወንጌሉን ለእናንተ እንድናስተምር አምላካችን ድፍረትን ሰጥቶናል። #ሐ.ሥ. 16፥19-24፤ 17፥1-9። 3እኛ የመከርናችሁ በስሕተት ወይም በርኩስ ዓላማ ተመርተን አይደለም፤ እናንተን ለማታለል ያደረግነው ምንም ነገር የለም። 4ይልቅስ እግዚአብሔር ወንጌሉን ለእኛ በዐደራ የሰጠን በእኛ ተማምኖ ስለ ሆነ እንናገራለን፤ ይህንንም የምናደርገው ልባችንን የሚመረምረውን እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ብለን ነው እንጂ ሰውን ለማስደሰት ብለን አይደለም። 5አንድም ጊዜ በቃላት በማቈላመጥ ወይም የገንዘብ ፍላጎት ኖሮን ከቶ እንዳልተናገርን እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤ እግዚአብሔርም ምስክራችን ነው። 6ከእናንተም ሆነ ከሌሎች ከማንም ሰው ክብርን አልፈለግንም። 7የክርስቶስ ሐዋርያት እንደ መሆናችን አስፈላጊውን ከእናንተ ለመጠየቅ እንችል ነበር፤ ነገር ግን ለልጆችዋ እንደምትጠነቀቅ እናት በገርነት በመካከላችሁ ተመላለስን። 8እንዲሁም በጣም ስለምንወዳችሁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ ማብሠር ብቻ ሳይሆን ሕይወታችንንም እንኳ ልንሰጣችሁ ዝግጁዎች ነበርን። 9ወንድሞች ሆይ! እንዴት እንደ ሠራንና እንደ ደከምን ታውቃላችሁ፤ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ በምናበሥርበት ጊዜ በአንዳችሁም ላይ ሸክም እንዳንሆን ሌሊትና ቀን በመሥራት እንደክም ነበር።
10በእናንተ በአማኞች መካከል በነበርንበት ጊዜ እንዴት ባለ ቅድስናና ጽድቅ ነቀፋም በሌለበት ሕይወት እንደ ኖርን እናንተ ምስክሮች ናችሁ፤ እግዚአብሔርም ምስክር ነው፤ 11አባት ለልጆቹ እንደሚያደርገው ዐይነት እኛም ለእናንተ ለእያንዳንዳችሁ እንዳደረግንላችሁ ታውቃላችሁ፤ 12ዘወትር እየመከርናችሁና እያበረታታናችሁ መንግሥቱንና ክብሩን እንድትካፈሉ የጠራችሁ አምላክ ደስ በሚሰኝበት ሁኔታ እንድትኖሩ ዐደራ እንዳልናችሁ ታውቃላችሁ።
13ደግሞም ስለ እናንተ ሳናቋርጥ እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት ምክንያት አለን፤ ይኸውም ከእኛ የሰማችሁትን የእግዚአብሔርን ቃል በተቀበላችሁ ጊዜ በእናንተ በአማኞች የሚሠራውን ይህንን ቃል የተቀበላችሁት እንደ ሰው ቃል ሳይሆን ልክ እንደ እግዚአብሔር ቃል አድርጋችሁ ነው፤ በእርግጥም የእግዚአብሔር ቃል ነው። 14ወንድሞች ሆይ፥ እናንተም በይሁዳ ምድር የሚገኙትን በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያን የሆኑትን አርአያ ተከትላችኋል፤ እነርሱ በአይሁድ መከራ እንደ ደረሰባቸው ሁሉ እናንተም ከገዛ ወገኖቻችሁ መከራ ደርሶባችኋል። #ሐ.ሥ. 17፥5። 15አይሁድ ጌታ ኢየሱስንና ነቢያትን የገደሉ እኛንም አሳደው ከአገር ያስወጡ ናቸው፤ እነርሱ እግዚአብሔርን የሚያሳዝኑና ሰዎችን ሁሉ የሚጠሉ ናቸው፤ #ሐ.ሥ. 9፥23፤29፤ 13፥45፤ 14፥2፤5፤ 19፤ 17፥5፤13፤ 18፥12። 16አሕዛብ የሚድኑበትን ቃል እንዳንናገር እንኳ ይከለክሉናል፤ በዚህ ዐይነት ኃጢአትን በኃጢአት ላይ እየጨመሩ ይሄዳሉ፤ ስለዚህ በመጨረሻ የእግዚአብሔር ቊጣ መጥቶባቸዋል።
ጳውሎስ የተሰሎንቄን ሰዎች እንደገና ለመጐብኘት የነበረው ምኞት
17ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! በመንፈስ ሳይሆን በሥጋ ለጥቂት ጊዜ ከእናንተ በመለየታችን ስለ እናንተ ያለን ናፍቆት ብዙ ስለ ሆነ በዐይነ ሥጋ ልናያችሁ ብዙ ጥረት አደረግን። 18ወደ እናንተ መምጣት ፈልገን ነበር፤ በተለይም እኔ ጳውሎስ ወደ እናንተ ለመምጣት ደጋግሜ ሞክሬ ነበር፤ ነገር ግን ሰይጣን ከለከለን። 19ታዲያ፥ ተስፋችን ወይም ደስታችን ወይም ጌታችን ኢየሱስ በሚመጣበት ጊዜ በፊቱ የምንመካበት የድል አክሊላችን እናንተ አይደላችሁምን? 20በእርግጥ ክብራችንና ደስታችን እናንተ ናችሁ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in