አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 11
11
ሰሎሞን ከእግዚአብሔር እየራቀ መሄዱ
1ሰሎሞን ብዙ የባዕዳን አገሮችን ሴቶች አፈቀረ፤ በዚህም መሠረት ከግብጽ ንጉሥ ልጅ ሌላ የሒታውያን፥ የሞአባውያን፥ የዐሞናውያን፥ የኤዶማውያንና የሲዶናውያን ሴቶች ልጆችን አፈቀረ። #ዘዳ. 17፥17። 2እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን፥ “አሕዛብ ሴቶችን ያገባችሁ እንደ ሆነ በእርግጥ ወደ አማልእክታቸው ስለሚስቡአችሁ እነርሱን አታግቡ” ብሎ አስጠንቅቆአቸው ነበር፤ እነዚህን ሰሎሞን የወደዳቸው ሴቶች እግዚአብሔር እንዳይጋቡ ከከለከላቸው ሕዝቦች መካከል ናቸው፤ ሰሎሞን ግን ከእነርሱ ጋር በፍቅር ተሰባበረ። #ዘፀ. 34፥16፤ ዘዳ. 7፥3-4። 3ሰሎሞን የነገሥታት ልጆች የሆኑ ሰባት መቶ ሚስቶችና ሦስት መቶ ቊባቶች ነበሩት፤ እነርሱም ሰሎሞንን ከእግዚአብሔር እንዲርቅ አደረጉት፤ 4በተለይም በዕድሜ እየሸመገለ በሄደ መጠን ለባዕዳን አማልክት እንዲሰግድ አደረጉት፤ ሰሎሞን እግዚአብሔርን በታማኝነት በማገልገል እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ሆኖ አልተገኘም። 5የሲዶናውያን ሴት አምላክ ለነበረችው ለዐስታሮትና ሞሎክ ተብሎ ለሚጠራው ለአጸያፊው ለዐሞናውያን አምላክ ሰገደ። 6በደል በመሥራትም እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ ሰሎሞን እግዚአብሔርን በቅንነት በመከተል ረገድ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ሆኖ አልተገኘም። 7ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ በሚገኘው ተራራ ላይ አጸያፊዎች ለሆኑት ከሞሽ ተብሎ ለሚጠራው ለሞአባውያን አምላክና ሞሎክ ተብሎ ለሚጠራው ለዐሞናውያን አምላክ የመስገጃ ስፍራዎችን አዘጋጀላቸው። 8እንዲሁም የባዕዳን አገሮች ሚስቶቹ ለየአማልክታቸው ዕጣን የሚያጥኑባቸውንና መሥዋዕት የሚያቀርቡባቸውን ስፍራዎች ሠራ።
9-10የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሁለት ጊዜ ተገልጦለት ባዕዳን አማልክትን እንዳያመልክ ያዘዘው ቢሆንም እንኳ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር አልታዘዘም፤ ይልቁንም ከእግዚአብሔር እየራቀ ሄደ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር በሰሎሞን ላይ ተቈጣ፤ 11እንዲህም አለው፤ “ከእኔ ጋር የገባኸውን ቃል ኪዳን ሆን ብለህ ስላፈረስክና ሕጌንም ስላልፈጸምክ፥ መንግሥትህን ከአንተ ወስጄ ከአገልጋዮችህ ለአንዱ ልሰጠው ወስኛለሁ። 12ይሁን እንጂ ለአባትህ ለዳዊት ስል ይህን የማደርገው አንተ ባለህበት ዘመን ሳይሆን በልጅህ መንግሥት ጊዜ ይሆናል፤ 13ከልጅህም ቢሆን መንግሥቱን በሙሉ አልወስድበትም፤ ለአገልጋዬ ለዳዊትና ለራሴ ርስት እንድትሆን ለመረጥኳት ለኢየሩሳሌም ከተማ ስል አንድ ነገድ እተውለታለሁ።”
በሰሎሞን ላይ የተነሡበት ጠላቶች
14ስለዚህም እግዚአብሔር የኤዶም ንጉሣዊ ቤተሰብ ወገን የሆነውን ሀዳድን በሰሎሞን ላይ ጠላት አድርጎ አስነሣበት፤ 15ዳዊት ከኤዶማውያን ጋር ይዋጋ በነበረ ጊዜ የጦር አዛዡ ኢዮአብ የሞቱትን ለመቅበር ወጥቶ የኤዶማውያንን ወንዶች ልጆች ሁሉ ፈጅቶ ነበር፤ 16ኢዮአብና የእስራኤል ሠራዊት የኤዶምን ወንዶች ልጆች ገድለው እስኪጨርሱ ድረስ ስድስት ወራት በዚያ ቈይተዋል። 17ከሞት የተረፉት ሀዳድና ወደ ግብጽ ሸሽተው የሄዱ ጥቂቶች ኤዶማውያን የአባቱ አገልጋዮች ብቻ ነበሩ፤ በዚያን ጊዜ ሀዳድ ገና ሕፃን ነበር፤ 18እነርሱም ከምድያም ተነሥተው ወደ ፋራን ሄዱ፤ በዚያም ጥቂቶች ሰዎች ከእነርሱ ጋር ተቀላቀሉ፤ ከዚህ በኋላ ወደ ግብጽ ተጒዘው ወደ ንጉሡ ቀረቡ፤ ንጉሡም ለሀዳድ መሬትና አንድ መኖሪያ ቤት ሰጥቶ ምግብ ፈቀደለት፤ 19ሀዳድም የንጉሡ ወዳጅ ሆነ፤ ንጉሡም የሚስቱን የጣፍኔስን እኅት ለሀዳድ ዳረለት፤ 20እርስዋም ገኑባት ተብሎ የሚጠራውን ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ እርሱንም ንግሥቲቱ ወስዳ በቤተ መንግሥት አሳደገችው፤ ከንጉሡም ወንዶች ልጆች ጋር አብሮ ኖረ።
21ሀዳድ በግብጽ ሳለ የንጉሥ ዳዊትንና የሠራዊቱን አዛዥ የኢዮአብን መሞት በሰማ ጊዜ “ወደ አገሬ ተመልሼ እንድሄድ አሰናብተኝ” ሲል ንጉሡን ጠየቀ።
22ንጉሡም “ስለምን ትሄዳለህ? ወደ አገርህ ለመሄድ ያሰብከው ከቶ ምን ተጓድሎብህ ነው?” አለው።
ሀዳድም “ምንም የተጓደለብኝ ነገር የለም፤ ብቻ ወደ ትውልድ አገሬ እንድመለስ ፍቀድልኝ” ሲል ለንጉሡ መለሰ፤
23እንደገናም እግዚአብሔር ረዞን ተብሎ የሚጠራውን የኤሊዓዳን ልጅ በሰሎሞን ላይ ጠላት አድርጎ አስነሣ፤ ረዞን የጾባ ንጉሥ ከነበረው ከጌታው ከሀዳድዔዜር ኮብልሎ፥ 24የሸፍቶች አለቃ ሆኖ ነበር፤ ይህም የሆነው ዳዊት ሀዳድዔዜርን ድል ነሥቶ የእርሱ ጦር ተባባሪዎች የሆኑትን ሶርያውያንን ከፈጀ በኋላ ነበር፤ ረዞንና ተከታዮቹም ወደ ደማስቆ ሄዱ፤ በዚያም ሲኖሩ እርሱን የሶርያ ንጉሥ እንዲሆን አደረጉት፤ 25ሰሎሞን በኖረበት ዘመን ሁሉ ሃዳድ ካደረሰበት ችግር በተጨማሪ ረዞን የእስራኤል ጠላት ሆነ። ስለዚህ ረዞን በሶርያ ላይ ገዢ ሆኖ በእስራኤል ላይ ጠላትነቱን ቀጠለ።
እግዚአብሔር ለኢዮርብዓም የሰጠው ተስፋ
26በሰሎሞን ላይ ያመፀው ሌላው ሰው በኤፍሬም ጸሬዳ ተብላ የምትጠራው ክፍል ተወላጅ የሆነ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ነው፤ እርሱም ከሰሎሞን አገልጋዮች አንዱ ነበር፤ እናቱም ጽሩዓ ተብላ የምትጠራ ባልዋ የሞተባት ሴት ነበረች። 27ኢዮርብዓም ለዐመፅ የተነሣሣበትም ታሪክ እንደሚከተለው ነው፥ በዚያን ጊዜ ሰሎሞን ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ ሚሎ ተብሎ የሚጠራውን ጐድጓዳ ስፍራ በመሙላት እየደለደለና የአባቱን የዳዊትን ከተማ ቅጽሮች እየጠገነ በማደስ ላይ ነበር። 28ኢዮርብዓም ከፍ ያለ የሥራ ችሎታ ያለው ወጣት ነበር፤ ሰሎሞንም ይህ ወጣት ትጉህና ብርቱ ሠራተኛ መሆኑን በተመለከተ ጊዜ በምናሴና በኤፍሬም ነገዶች ግዛት ውስጥ ባሉት ገባሮች ሁሉ ላይ ኀላፊ አድርጎ ሾመው። 29አንድ ቀን ኢዮርብዓም ከኢየሩሳሌም ወጥቶ በጒዞ ላይ ሳለ አዲስ መጐናጸፊያ የለበሰ፥ ከሴሎ የመጣው ነቢዩ አኪያ ከከተማ ውጪ መንገድ ላይ ብቻውን አገኘው፤ 30አኪያም የለበሰውን አዲስ መጐናጸፊያ አውልቆ ከዐሥራ ሁለት ቈራረጠው፤ 31ኢዮርብዓምንም እንዲህ አለው፤ “ዐሥሩን ቊራጭ ለራስህ ውሰድ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ ‘መንግሥትን ከሰሎሞን ወስጄ ዐሥሩን ነገድ ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ 32ለአገልጋዬ ለዳዊትና ከሌላው የእስራኤል ምድር የራሴ ርስት እንድትሆን ለመረጥኳት ለኢየሩሳሌም ከተማ ስል ለሰሎሞን አንድ ነገድ አስቀርቼለታለሁ። 33ይህንንም የማደርገው ሰሎሞን እኔን ትቶ ባዕዳን የሆኑትን ዐስታሮት ተብላ የምትጠራውን የሲዶና አምላክ፥ ከሞሽ ተብሎ የሚጠራውን የሞአብ አምላክና ሚልኮም ተብሎ የሚጠራውን የዐሞን አምላክ ስላመለከ ነው፤ ሰሎሞን ለእኔ ታዛዥ አልሆነም፤ እርሱ አባቱ ዳዊት ለእኔ ይታዘዝ እንደ ነበር ሕጎቼንና ትእዛዞቼን ባለመጠበቁ በድሎአል። #11፥33 ሰሎሞን፦ ወይም እነርሱ 34ይሁን እንጂ ከሰሎሞን መንግሥትን በሙሉ አልወስድበትም፤ በሕይወት እስካለም ድረስ በሥልጣን እንዲቈይ አደርገዋለሁ፤ ይህንንም የማደርገው ለመረጥኩትና ሕጎቼንና ትእዛዞቼን ለፈጸመው ለአገልጋዬ ለዳዊት ስል ነው። 35ስለዚህ መንግሥትን ከሰሎሞን ልጅ ወስጄ ለአንተ ዐሥሩን ነገድ እሰጥሃለሁ፤ 36ይሁን እንጂ ስሜ እንዲጠራባት በመረጥኳት በኢየሩሳሌም አገልጋዬ ዳዊት በፊቴ አንድ ዘር ይኖረው ዘንድ ለልጁ አንድ ነገድ እሰጠዋለሁ 37ኢዮርብዓም ሆይ! እኔ አንተን የእስራኤል ንጉሥ አደርግሃለሁ፤ አንተ በወደድከው ግዛት ሁሉ ላይ መሪ ትሆናለህ። 38አገልጋዬ ዳዊት እንዳደረገው በፍጹም ልብህ ብትታዘዘኝ፥ በሕጎቼና በትእዛዞቼ ጸንተህ ብትኖር፥ በእኔ ፊት ሞገስ ብታገኝ፥ እኔ ዘወትር ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ በእስራኤል ላይ እንድትነግሥም አደርግሃለሁ፤ ለዳዊት ባደረግሁት ዐይነት ዘሮችህ ከአንተ በኋላ እንደሚነግሡ አረጋግጥልሃለሁ። 39በሰሎሞን ኃጢአት ምክንያት የዳዊትን ትውልዶች እቀጣለሁ፤ ይሁን እንጂ የምቀጣቸው ለዘለዓለም አይደለም።’ ”
40ከዚህም የተነሣ ሰሎሞን ኢዮርብዓምን ለመግደል ሞከረ፤ ነገር ግን ኢዮርብዓም ወደ ግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ በመኰብለል አመለጠ፤ ሰሎሞንም እስከ ሞተበት ጊዜ ድረስ እዚያው ቈየ።
የሰሎሞን መሞት
(2ዜ.መ. 9፥29-31)
41ሰሎሞን ያደረገው ሌላው ነገር፥ ያከናወነው ተግባርና ጥበቡ ሁሉ በሰሎሞን የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦአል። 42ሰሎሞን መኖሪያውን በኢየሩሳሌም አድርጎ በመላው እስራኤል ላይ የነገሠበት ዘመን አርባ ዓመት ነው፤ 43ከዚህ በኋላ ሰሎሞን ሞተ፤ በአባቱ በዳዊት ከተማም ተቀበረ፤ ልጁም ሮብዓም በአባቱ በሰሎሞን እግር ተተክቶ ነገሠ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 11: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997