አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 10
10
የንግሥተ ሳባ ጒብኝት በኢየሩሳሌም
(2ዜ.መ. 9፥1-12)
1ንግሥተ ሳባ እግዚአብሔር ለሰሎሞን ስለ ሰጠው አስደናቂ ጥበብ የሚነገረውን ሁሉ ሰማች፤ ስለዚህ አስቸጋሪ በሆኑ ከባድ ጥያቄዎች ልትፈትነው ወደ ኢየሩሳሌም መጣች። 2ብዙ የክብር አጃቢዎችን በማስከተል በግመሎች የተጫነ ሽቶ፥ የከበረ ዕንቊና ብዙ ወርቅ ይዛ መጣች፤ ከሰሎሞንም ጋር በተገናኙ ጊዜ በሐሳብዋ ያለውን ጥያቄ ሁሉ አቀረበችለት፤ 3እርሱም ላቀረበችለት ጥያቄ ሁሉ መልስ ሰጠ፤ ሊተረጒምላት የተሳነውና ከእርሱ የተሰወረ ምንም ዐይነት እንቆቅልሽ አልነበረም። 4ንግሥተ ሳባ ጥበብ የተሞላበትን የሰሎሞንን አነጋገር አዳመጠች፤ የሠራውንም ቤተ መንግሥት አየች፤ 5በሰሎሞን ገበታ ላይ የሚቀርበውን የምግብ ዐይነት፥ የመኳንንቱን መኖሪያ አካባቢዎች፥ የቤተ መንግሥቱን ሠራተኞች የሥራ አደረጃጀት፥ የደንብ ልብሳቸውንም ዐይነት፥ በግብዣ ጊዜ የሚያገለግሉትን አሳላፊዎችና በቤተ መቅደስም የሚያቀርባቸውን መሥዋዕቶችን ሁሉ ተመለከተች፤ በዚህም ሁሉ የተሰማት አድናቆት ከጠበቀችው በላይ ነበር። 6ንጉሥ ሰሎሞንንም እንዲህ አለችው፦ “ስለ ሥራህ ውጤትና ስለ ጥበብህ ታላቅነት በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ሁሉ እውነት ነው! 7ነገር ግን እዚህ ድረስ መጥቼ በዐይኔ እስካየው ድረስ የተነገረኝን ሁሉ አላመንኩም ነበር፤ በጆሮዬ የሰማሁት በዐይኔ ያየሁትን እኩሌታ እንኳ አይሆንም፤ በእርግጥም ጥበብህና ሀብትህ በአገሬ ሳለሁ ከተነገረኝ በጣም ይበልጣል። 8በፊትህ ሁልጊዜ በመገኘት ጥበብ የሞላበት ንግግርህን የሚሰሙ ሰዎችህና ባለሟሎችህ እንዴት የታደሉ ናቸው! 9አምላክህ እግዚአብሔር ይመስገን! እርሱ አንተን መርጦ የእስራኤል ንጉሥ በማድረግ በአንተ መደሰቱን ገልጦልሃል፤ ለእስራኤል ያለውም ፍቅር ዘለዓለማዊ ስለ ሆነ ጽድቅና ፍትሕ ጸንቶ እንዲኖር ታደርግ ዘንድ የእስራኤል ንጉሥ አድርጎሃል።”
10ንግሥተ ሳባ ያመጣችለትን ስጦታ ሁሉ ለንጉሥ ሰሎሞን አበረከተችለት፤ ይኸውም ከአራት ሺህ ኪሎ የሚበልጥ ወርቅ፥ እጅግ ብዙ ሽቶና የከበረ ዕንቊ ነበር፤ እርስዋ ለሰሎሞን ያበረከተችው የሽቶ ብዛት ከዚያ በኋላ ከቀረበለት የሽቶ ገጸ በረከት ሁሉ እጅግ የሚበልጥ ነበር። #ማቴ. 12፥42፤ ሉቃ. 11፥31።
11ከኦፊር ወርቅ ያመጡለት የኪራም መርከቦች ከዚያው ከኦፊር ብዙ የሰንደል እንጨትና የከበረ ዕንቊ አምጥተውለት ነበር። 12ሰሎሞን ከዚሁ ሰንደል እንጨት የቤተ መቅደሱንና የቤተ መንግሥቱን መከታዎች፥ መዘምራን የሚያገለግሉባቸውን በገናዎችና መሰንቆዎች አሠራ፤ ይህም የሰንደል እንጨት ወደ እስራኤል አገር ከመጣው የሰንደል እንጨት ሁሉ የሚበልጥ ነበር፤ ከዚያም በኋላ ይህን የመሰለ የሰንደል እንጨት ከቶ ታይቶ አያውቅም።
13ንጉሥ ሰሎሞን ከተለመደው የልግሥና ስጦታው ጋር የሳባ ንግሥት የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣት፤ ከዚህ በኋላ ንግሥተ ሳባ ከክብር አጃቢዎችዋ ጋር ወደ አገርዋ ተመልሳ ሄደች።
የንጉሥ ሰሎሞን ሀብት ብዛት
(2ዜ.መ. 9፥13-29)
14ንጉሥ ሰሎሞን በየዓመቱ ኻያ ሦስት ሺህ ኪሎ ያኽል የሚመዝን ወርቅ ያገኝ ነበር፤ 15ይህም ሁሉ ነጋዴዎች ከሚከፍሉት ቀረጥ፥ ከንግድ ከሚገኘው ትርፍ፥ እንዲሁም ከዐረብ ነገሥታትና ከእስራኤል ክፍላተ ሀገር አስተዳዳሪዎች ከሚገባለት ግብር ጋር ተጨማሪ ነበር።
16ንጉሥ ሰሎሞን ሁለት መቶ ታላላቅ ጋሻዎችን አሠርቶ እያንዳንዱን ጋሻ በሰባት ኪሎ ያኽል ወርቅ አስለበጠው፤ 17እንዲሁም ሦስት መቶ ታናናሽ ጋሻዎችን አሠርቶ እያንዳንዱን በሁለት ኪሎ ያኽል ወርቅ አስለበጠው፤ እነዚህንም ሁሉ “የሊባኖስ ደን” ተብሎ በሚጠራው አዳራሽ ውስጥ አኖራቸው።
18እንዲሁም ንጉሥ ሰሎሞን ከዝሆን ጥርስ አንድ ትልቅ ዙፋን አሠርቶ በንጹሕ ወርቅ አስለበጠው፤ 19ወደ ዙፋኑ መወጣጫ ስድስት ደረጃዎች ነበሩ፤ የዙፋኑ ጀርባ ራስጌው ክብ ነበር፤ በዙፋኑ ግራና ቀኝ የክንድ ማሳረፊያዎች ነበሩ፤ በክንድ ማሳረፊያዎቹ ጐን አንዳንድ የአንበሳ ምስሎች ቈመው ነበር። 20በየአንዳንዱ ደረጃ በሁለት በኩል አንዳንድ የአንበሳ ምስል በድምሩ ዐሥራ ሁለት የአንበሳ ምስሎች ቈመዋል። ይህን የመሰለ ዙፋን በሌላ በየትኛውም አገር ተሠርቶ አይታወቅም።
21በሰሎሞን ዘመን ብር ምንም ዋጋ ስላልነበረው ሰሎሞን የሚጠጣባቸው ዋንጫዎች ሁሉና “የሊባኖስ ደን” ተብሎ በሚጠራው አዳራሽ ውስጥ የሚገኙት ዕቃዎች በሙሉ ከንጹሕ ወርቅ እንጂ ከብር አልተሠሩም፤ 22ሰሎሞን ከኪራም መርከቦች ጋር በውቅያኖስ ላይ የሚጓዙ ሌሎች የተርሴስ መርከቦችም ነበሩት፤ እነርሱም በየሦስት ዓመት ወርቅን፥ ብርን፥ የዝሆን ጥርስን፥ ጦጣዎችንና ዝንጀሮዎችን ያመጡለት ነበር።
23ንጉሥ ሰሎሞን ከምድር ነገሥታት ሁሉ የሚበልጥ ሀብታምና ጥበበኛ ነበር፤ 24በመላው ዓለም የሚገኙ ሰዎችም ሁሉ እግዚአብሔር የሰጠውን ጥበብ የሞላበትን ንግግር ይሰሙ ዘንድ ወደ እርሱ መምጣት ይፈልጉ ነበር፤ 25ወደ እርሱም የሚመጡት ሁሉ የብርና የወርቅ፥ የልብስ፥ የጦር መሣሪያዎች፥ የሽቶ፥ የፈረሶችና የበቅሎዎች ስጦታዎችን ያመጡለት ነበር፤ ይህም በየዓመቱ የሚደረግ ነበር።
26ሰሎሞንም ሠረገሎችንና ፈረሶችን ሰበሰበ፤ እርሱም አንድ ሺህ አራት መቶ ሠረገሎችና ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሰኞች ነበሩት፤ ከእነርሱም ከፊሉ ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም፥ ሌሎቹ ደግሞ በልዩ ልዩ ከተሞች ተመድበው እንዲኖሩ አደረገ፤ #1ነገ. 4፥26። 27በግዛቱም ዘመን ሁሉ በኢየሩሳሌም ብር እንደ ድንጋይ፥ የሊባኖስ ዛፍ ብዛት በይሁዳ ኰረብቶች ግርጌ በየትኛውም ስፍራ እንደሚበቅለው ሾላ ይቈጠር ነበር፤ 28ሰሎሞን ፈረሶችን ከግብጽና ከቀዌ ያስመጣ ነበር፤ የንጉሡም ነጋዴዎች ፈረሶችን በገንዘብ ገዝተው ከቀዌ ያመጡለት ነበር። #ዘዳ. 17፥16። 29ሠረገሎችን ከግብጽ አገር በማስመጣት፥ ለእያንዳንዱ ሠረገላ ስድስት መቶ ጥሬ ብር፥ ለእያንዳንዱም ፈረስ አንድ መቶ ኀምሳ ጥሬ ብር ይከፍሉ ነበር፤ ከዚያም እነርሱ ለሒታውያንና ለሶርያ ነገሥታት ይሸጡላቸው ነበር።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 10: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997