YouVersion Logo
Search Icon

መዝሙር 143

143
መዝሙር 143
ትሑት ልመና
የዳዊት መዝሙር።
1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ጸሎቴን ስማ፤
ልመናዬን አድምጥ፤
በታማኝነትህና በጽድቅህም፣
ሰምተህ መልስልኝ።
2ሰው ሆኖ በፊትህ ጻድቅ የለምና፣
ባሪያህን ወደ ፍርድ አታቅርበው።
3ጠላት እስከ ሞት አሳድዶኛል፤
ሕይወቴንም አድቅቆ ከዐፈር ቀላቅሏል፤
ቀደም ብለው እንደ ሞቱትም፣
በጨለማ ውስጥ አኑሮኛል።
4ስለዚህ መንፈሴ በውስጤ ዝላለች፤
ልቤም በውስጤ ደንግጧል።
5የቀድሞውን ዘመን አስታወስሁ፤
ሥራህንም ሁሉ አሰላሰልሁ፤
የእጅህንም ሥራ አውጠነጠንሁ።
6እጆቼን ወደ አንተ ዘረጋሁ፤
ነፍሴም እንደ ምድረ በዳ አንተን ተጠማች። ሴላ
7 እግዚአብሔር ሆይ፤ ፈጥነህ መልስልኝ፤
መንፈሴ ደከመች፤
ወደ ጕድጓድ እንደሚወርዱት እንዳልሆን፣
ፊትህን ከእኔ አትሰውር።
8በአንተ ታምኛለሁና፣
በማለዳ ምሕረትህን አሰማኝ፤
ነፍሴን ወደ አንተ አንሥቻለሁና፣
የምሄድበትን መንገድ አሳየኝ።
9 እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተን መሰወሪያ አድርጌአለሁና፣
ከጠላቶቼ አድነኝ።
10አንተ አምላኬ ነህና፣
ፈቃድህን እንድፈጽም አስተምረኝ፤
መልካሙ መንፈስህም፣
በቀናችው መንገድ ይምራኝ።
11 እግዚአብሔር ሆይ፤ ስለ ስምህ ሕያው አድርገኝ፤
በጽድቅህም ነፍሴን ከመከራ አውጣት።
12ጠላቶቼንም ለእኔ ስላለህ ምሕረት ደምስሳቸው፤
እኔ ባሪያህ ነኝና፣
ነፍሴን የሚያስጨንቋትን ሁሉ አጥፋቸው።

Currently Selected:

መዝሙር 143: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in