YouVersion Logo
Search Icon

መዝሙር 139

139
መዝሙር 139
ሁሉን ዐዋቂ አምላክ
ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።
1 እግዚአብሔር ሆይ፤ መረመርኸኝ፤
ደግሞም ዐወቅኸኝ።
2አንተ መቀመጤንና መነሣቴን ታውቃለህ፤
የልቤንም ሐሳብ ገና ከሩቁ ታስተውላለህ።
3መሄድ መተኛቴን አጥርተህ ታውቃለህ፤
መንገዶቼንም ሁሉ ተረድተሃቸዋል።
4 እግዚአብሔር ሆይ፤ ገና ቃል ከአንደበቴ ሳይወጣ፣
እነሆ፤ አንተ ሁሉንም ታውቃለህ።
5አንተ ከኋላም ከፊትም ዙሪያዬን ከለልኸኝ፤
እጅህንም በላዬ አደረግህ።
6እንዲህ ያለው ዕውቀት ለእኔ ድንቅ ነው፤
ልደርስበትም የማልችል ከፍ ያለ ነው።
7ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ?
ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ?
8ወደ ሰማይ ብወጣ፣ አንተ በዚያ አለህ፤
መኝታዬንም በሲኦል#139፥8 አንዳንድ ትርጕሞች በጥልቁ ውስጥ ይላሉ። ባደርግ በዚያ ትገኛለህ።
9በንጋት ክንፍ ተነሥቼ ብበርር፣
እስከ ባሕሩ ዳርቻ መጨረሻ ብሄድ፣
10በዚያም ቢሆን እጅህ ትመራኛለች፤
ቀኝ እጅህም አጥብቃ ትይዘኛለች።
11እኔም፣ “ጨለማው በርግጥ ይሰውረኛል፤
በዙሪያዬ ያለውም ብርሃን ሌሊት ይሆናል” ብል፣
12ጨለማ የአንተን ዐይን አይዝም፤
ሌሊቱም እንደ ቀን ያበራል፤
ጨለማም ብርሃንም ለአንተ አንድ ናቸውና።
13አንተ ውስጣዊ ሰውነቴን ፈጥረሃልና፤
በእናቴም ማሕፀን ውስጥ አበጃጅተህ ሠራኸኝ።
14ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤
ሥራህ ድንቅ ነው፤
ነፍሴም ይህን በውል ተረድታለች።
15እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፣
ዐጥንቶቼ ከአንተ አልተደበቁም፤
በምድር ጥልቀት ውስጥ በጥበብ በተሠራሁ ጊዜ፣
16ዐይኖችህ ገና ያልተበጀውን አካሌን አዩ፤
ለእኔ የተወሰኑልኝም ዘመናት፣
ገና አንዳቸው ወደ መኖር ሳይመጡ፣
በመጽሐፍ ተመዘገቡ።
17አምላክ ሆይ፤ ለእኔ ያለህ ሐሳብ እንዴት ክቡር ነው!
ቍጥሩስ ምንኛ ብዙ ነው!
18ልቍጠራቸው ብል፣
ከአሸዋ ይልቅ ይበዙ ነበር።
ተኛሁም ነቃሁም፣
ገና ከአንተው ጋር ነኝ።
19አምላክ ሆይ፤ ክፉዎችን ብትገድላቸው ምናለበት!
ደም የተጠማችሁ ሰዎች ሆይ፤
ከእኔ ራቁ!
20ስለ አንተ በክፋት ይናገራሉና፤
ጠላቶችህም ስምህን በከንቱ ያነሣሉ።
21 እግዚአብሔር ሆይ፤ የሚጠሉህን አልጠላምን?
በአንተ ላይ የሚነሡትንስ አልጸየፍምን?
22በፍጹም ጥላቻ ጠልቻቸዋለሁ፤
ባላጋራዎቼም ሆነዋል።
23እግዚአብሔር ሆይ፤ መርምረኝ፤ ልቤንም ዕወቅ፤
ፈትነኝ፤ ሐሳቤንም ዕወቅ፤
24የክፋት መንገድ በውስጤ ቢኖር እይ፤
በዘላለምም መንገድ ምራኝ።

Currently Selected:

መዝሙር 139: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in