YouVersion Logo
Search Icon

ዘኍልቍ 31

31
ምድያማውያንን መበቀል
1 እግዚአብሔር ሙሴን፣ 2“ለእስራኤላውያን ምድያማውያንን ተበቀልላቸው፤ ከዚያም ወደ ወገኖችህ ትከማቻለህ” አለው።
3ስለዚህ ሙሴ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፤ “ምድያማውያንን ለመውጋት እንዲሄዱና ስለ እግዚአብሔርም እንዲበቀሏቸው ከሰዎቻችሁ ጥቂቶቹን ለጦርነት አዘጋጁ። 4ከእያንዳንዱም የእስራኤል ነገድ አንዳንድ ሺሕ ሰው ለጦርነቱ ላኩ።” 5ስለዚህ ከእስራኤል ጐሣዎች ተወጣጥቶ ከእያንዳንዱ ነገድ አንድ ሺሕ፣ በአጠቃላይ ዐሥራ ሁለት ሺሕ ሰው ለጦርነት ተዘጋጀ። 6ሙሴም የቤተ መቅደሱን ንዋየ ቅድሳትና ምልክት መስጫ የሆኑትን መለከቶች ከያዘው ከካህኑ ከአልዓዛር ልጅ ከፊንሐስ ጋራ ከየነገዱ አንዳንድ ሺሕ ሰው ለጦርነት ላከ።
7 እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ከምድያም ጋራ ተዋጉ፤ ወንዱንም በሙሉ ፈጁት፤ 8ከተገደሉትም መካከል ዐምስቱ የምድያም ነገሥታት ኤዊ፣ ሮቆም፣ ሱር፣ ሑርና ሪባ ይገኙባቸዋል፤ የቢዖርን ልጅ በለዓምንም በሰይፍ ገደሉት። 9ከዚያም እስራኤላውያን የምድያማውያንን ሴቶችና ሕፃናት ማረኩ፤ የቀንድ ከብቶቻቸውን፣ የበግና የፍየል መንጋዎቻቸውን ሁሉ ነዱ፤ ሀብታቸውንም በሙሉ ወሰዱ። 10ምድያማውያኑ የሚኖሩባቸውን ከተሞች ሁሉ ሰፈሮቻቸውንም በሙሉ አቃጠሉ። 11ሰውና እንስሳትን ጨምሮ የማረኩትንና የዘረፉትን ሁሉ እንዳለ አጋዙት። 12የማረኳቸውን ሰዎች፣ የነዷቸውን እንስሳትና የዘረፉትን ሀብት በሙሉ፣ ከኢያሪኮ#31፥12 በዕብራይስጥ የኢያሪኮ ዮርዳኖስ ማለት ሲሆን፣ ይህም የዮርዳኖስ ወንዝ የጥንት ስም ሳይሆን አይቀርም። ማዶ፣ በዮርዳኖስ አጠገብ፣ በሞዓብ ወዳለው፣ ሙሴና ካህኑ አልዓዛር እንዲሁም መላው የእስራኤላውያን ማኅበር ወዳሉበት ሰፈራቸው አመጧቸው።
13ሙሴ፣ ካህኑ አልዓዛርና የማኅበረ ሰቡ መሪዎች በሙሉ ሊቀበሏቸው ከሰፈር ወጡ። 14ሙሴም ከጦርነት በተመለሱት በሰራዊቱ አዛዦች፣ ማለትም በሻለቆችና በመቶ አለቆች ላይ ተቈጣ።
15ሙሴም እንዲህ አላቸው፤ “ሴቶችን ሁሉ እንዴት በሕይወት ትተዉአቸዋላችሁ? 16የበለዓምን ምክር ተቀብለው በፌጎር በተፈጸመው ድርጊት እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር እንዲመለሱና የእግዚአብሔርም ሕዝብ እንዲቀሠፍ ያደረጉት እነርሱ ናቸው። 17አሁንም ወንዶቹን ልጆች ሁሉ፣ ወንድ ያወቁትንም ሴቶች በሙሉ ግደሏቸው፤ 18ነገር ግን ወንድ ያላወቁትን ልጃገረዶች ሁሉ ለራሳችሁ አስቀሯቸው።
19“ከእናንተ መካከል ሰው የገደለ ወይም የተገደለውን የነካ ሁሉ ከሰፈር ውጭ ሰባት ቀን ይቈይ። በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ራሳችሁንና ምርኮኞቻችሁን አንጹ። 20ማንኛውንም ልብስ እንዲሁም ከቈዳ፣ ከፍየል ጠጕር ወይም ከዕንጨት የተሠራ ማንኛውንም ነገር አንጹ።”
21ከዚያም ካህኑ አልዓዛር ወደ ጦርነት ሄደው የነበሩትን ወታደሮች እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው የሕጉ ሥርዐት ይህ ነው፤ 22ወርቅ፣ ብር፣ ናስ፣ ብረት፣ ቈርቈሮ፣ እርሳስ 23እንዲሁም እሳትን መቋቋም የሚችል ማንኛውም ነገር በእሳት ውስጥ ማለፍ አለበት፤ ከዚያም ንጹሕ ይሆናል፤ ይህም ሆኖ መንጻት አለበት። እሳትን መቋቋም የማይችል ማንኛውም ነገር በዚሁ ውሃ ውስጥ ማለፍ አለበት። 24በሰባተኛው ቀን ልብሳችሁን ዕጠቡ፤ ትነጻላችሁም፤ ከዚያም ወደ ሰፈር መግባት ትችላላችሁ።”
ምርኮን መከፋፈል
25 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 26“አንተ፣ ካህኑ አልዓዛርና በማኅበረ ሰቡ ውስጥ ያሉት የየቤተ ሰቡ አለቆች ሆናችሁ የተማረከውን ሕዝብና እንስሳት ሁሉ ቍጠሩ። 27ምርኮውንም ለሁለት ከፍላችሁ በጦርነቱ ለተካፈሉት ወታደሮችና ለቀረው ማኅበረ ሰብ አከፋፍሉት። 28በጦርነቱ ከተካፈሉት ወታደሮች ድርሻ ላይ፣ ከሰውም ሆነ ከቀንድ ከብት፣ ከአህያ፣ ከበግ ወይም ከፍየል ከየዐምስት መቶው አንዱን ለእግዚአብሔር ግብር አውጣ። 29ይህንም ግብር ከድርሻቸው ላይ ወስደህ የእግዚአብሔር ፈንታ በማድረግ ለካህኑ ለአልዓዛር ስጠው። 30ከእስራኤላውያን እኩሌታ ድርሻ ደግሞ ከሰውም ይሁን ከቀንድ ከብት፣ ከአህያ፣ ከበግ፣ ከፍየል ወይም ከሌሎች እንስሳት ከየዐምሳው አንዳንድ መርጠህ፣ የእግዚአብሔርን ማደሪያ ድንኳን በኀላፊነት ለሚጠብቁ ሌዋውያን ስጣቸው።” 31ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።
32ወታደሮቹ ማርከው ከወሰዱለት ምርኮ ውስጥ የቀረው ይህ ነበር፤ ስድስት መቶ ሰባ ዐምስት ሺሕ በግ፣ 33ሰባ ሁለት ሺሕ የቀንድ ከብት፣ 34ስድሳ አንድ ሺሕ አህያ 35ወንድ ያላወቁ ሠላሳ ሁለት ሺሕ ሴቶች።
36በጦርነቱ ላይ የነበሩት ወታደሮች እኩሌታ ድርሻ ይህ ነበር፤
ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺሕ ዐምስት መቶ በግ፣ 37ከእነዚህም በጎችና ፍየሎች ለእግዚአብሔር የተሰጠ ግብር ስድስት መቶ ሰባ ዐምስት ነበር።
38ሠላሳ ስድስት ሺሕ የቀንድ ከብት፣ ከእነዚህም ለእግዚአብሔር የተሰጠው ግብር ሰባ ሁለት ነበር።
39ሠላሳ ሺሕ ዐምስት መቶ አህያ፣ ከእነዚህም ለእግዚአብሔር የተሰጠው ግብር ስድሳ አንድ ነበር።
40ዐሥራ ስድስት ሺሕ ሰው፣ ከእነዚህም ለእግዚአብሔር የተሰጠው ግብር ሠላሳ ሁለት ነበር።
41ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው የእግዚአብሔር ድርሻ የሆነውን ግብር ለካህኑ አልዓዛር ሰጠው።
42ሙሴ ከዘመቱት ሰዎች የለየው የእስራኤላውያን እኩሌታ ድርሻ ማለትም፣ 43የማኅበረ ሰቡ ድርሻ ይህ ነበር፤ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺሕ ዐምስት መቶ በግ፣ 44ሠላሳ ስድስት ሺሕ የቀንድ ከብት፣ 45ሠላሳ ሺሕ ዐምስት መቶ አህያ፣ 46ዐሥራ ስድስት ሺሕ ሰው። 47ከእስራኤላውያን እኩሌታ ድርሻ ላይ፣ ሙሴ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ከየዐምሳው ሰውና እንስሳ አንዳንድ መርጦ የእግዚአብሔርን ማደሪያ ድንኳን በኀላፊነት ለሚጠብቁ ሌዋውያን ሰጣቸው።
48ከዚያም በኋላ በሰራዊቱ ክፍሎች ላይ የተሾሙት የሻለቆችና የመቶ አለቆች ወደ ሙሴ ቀርበው፣ 49እንዲህ አሉት፤ “እኛ አገልጋዮችህ በእጃችን ሥር ያሉትን ወታደሮች ቈጥረናል፤ አንድም የጐደለ የለም። 50ስለዚህ እያንዳንዳችን ያገኘነውን የወርቅ ጌጣጌጥ፣ የእግር ዐልቦዎች፣ የእጅ አንባሮች፣ የጣት ቀለበቶች፣ የጆሮ ጕትቻዎችና የዐንገት ሐብሎች በእግዚአብሔር ፊት ማስተስረያ እንዲሆነን መባ አድርገን ለእግዚአብሔር አምጥተናል።”
51ሙሴና ካህኑ አልዓዛር በጌጣጌጥ መልክ የተሠራውን ወርቅ ሁሉ ተቀበሏቸው። 52ሙሴና አልዓዛር ከሻለቆቹና ከመቶ አለቆቹ በመቀበል ስጦታ አድርገው ለእግዚአብሔር ያቀረቡት ወርቅ ዐሥራ ስድስት ሺሕ ሰባት መቶ ዐምሳ ሰቅል#31፥52 አንድ መቶ ዘጠና ኪሎ ግራም ያህል ነው። መዘነ። 53እያንዳንዱም ወታደር ለራሱ የወሰደው ምርኮ ነበረው። 54ሙሴና ካህኑ አልዓዛር ወርቁን ከሻለቆቹና ከመቶ አለቆቹ ተቀብለው በእግዚአብሔር ፊት ለእስራኤላውያን መታሰቢያ እንዲሆን ወደ መገናኛው ድንኳን አመጡት።

Currently Selected:

ዘኍልቍ 31: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Video for ዘኍልቍ 31