YouVersion Logo
Search Icon

ዘኍልቍ 32

32
ከዮርዳኖስ ማዶ ያሉ ነገዶች
1እጅግ ብዙ የሆነ የቀንድ ከብት፣ የበግና የፍየል መንጋዎች የነበሯቸው የሮቤልና የጋድ ነገዶች የኢያዜርና የገለዓድ ምድር ለከብት ምቹ ስፍራዎች መሆናቸውን አዩ። 2ስለዚህ የሮቤልና የጋድ ሰዎች ወደ ሙሴ፣ ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛርና ወደ ማኅበረ ሰቡ መሪዎች መጥተው እንዲህ አሉ፤ 3“አጣሮት፣ ዲቦን፣ ኢያዜር፣ ኒምራ፣ ሐሴቦን፣ ኤልያሊ፣ ሴባማ፣ ናባውና፣ ባያን፣ 4እግዚአብሔር በእስራኤል ሕዝብ ፊት እንዲሸነፍ ያደረገው ይህ ሁሉ ምድር ለከብት ምቹ ነው፤ እኛ አገልጋዮችህም ከብቶች አሉን። 5በፊትህ ሞገስ ያገኘን ከሆነ ይህ ምድር ለእኛ ለአገልጋዮችህ በርስትነት ይሰጠን፤ ዮርዳኖስንም እንድንሻገር አታድርገን።”
6ሙሴም የጋድንና የሮቤልን ነገዶች እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ እዚህ ተቀምጣችሁ ወገኖቻችሁ ወደ ጦርነት ይሂዱ? 7እስራኤላውያን ተሻግረው እግዚአብሔር ወደ ሰጣቸው ምድር እንዳይገቡ ተስፋ የምታስቈርጧቸው ለምንድን ነው? 8አባቶቻችሁ ምድሪቱን እንዲሰልሉ ከቃዴስ በርኔ በላክኋቸው ጊዜም ያደረጉት ይህንኑ ነበር። 9ወደ ኤሽኮል ሸለቆ ሄደው ምድሪቱን ካዩ በኋላ፣ እግዚአብሔር ወደ ሰጣቸው ምድር እንዳይገቡ እስራኤላውያንን ተስፋ አስቈረጧቸው። 10በዚያም ቀን የእግዚአብሔር ቍጣ ነደደ፤ እንዲህም ሲል ማለ፤ 11‘በፍጹም ልባቸው ስላልተከተሉኝ ከግብጽ ከወጡት፣ ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው ሰዎች አንዳቸውም ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅና ለያዕቆብ ልሰጥ በመሐላ ቃል የገባሁላቸውን ምድር አያዩዋትም፤ 12እግዚአብሔርን በፍጹም ልባቸው ተከትለውታልና፣ ከቄኔዛዊው ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር አንዳቸውም አያዩዋትም።’ 13እግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ስለ ነደደ፣ በፊቱ ክፉ ነገር ያደረገው ያ ትውልድ በሙሉ እስኪያልቅ ድረስ አርባ ዓመት በምድረ በዳ እንዲንከራተቱ አደረጋቸው።
14“እናንተ የኀጢአተኞች ልጆች ይኸው በአባቶቻችሁ እግር ተተክታችሁ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ይበልጥ እንዲቈጣ ታደርጋላችሁ። 15እርሱን ከመከተል ብትመለሱ አሁንም ይህን ሁሉ ሕዝብ በምድረ በዳ ይተወዋል፤ ለሚደርስበትም ጥፋት ምክንያቱ እናንተው ትሆናላችሁ።”
16ከዚህ በኋላ ወደ እርሱ ቀርበው እንዲህ አሉት፤ “እዚህ ለከብቶቻችን በረቶች፣ ለሴቶቻችንና ለልጆቻችን ከተሞች መሥራት እንወድዳለን፤ 17ይሁን እንጂ ወደ ስፍራቸው እስክናገባቸው ድረስ ታጥቀንና በእስራኤላውያን ፊት ግንባር ቀደም ሆነን ለመሄድ ዝግጁ ነን፤ በዚህም ጊዜ ሴቶቻችንና ልጆቻችን በምድሪቱ ላይ ካሉት ነዋሪዎች እንዲጠበቁ በተመሸጉ ከተሞች ይኖራሉ። 18እኛም እያንዳንዱ እስራኤላዊ ርስቱን እስኪወርስ ድረስ ወደየቤታችን አንመለስም። 19ድርሻችንን ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምሥራቅ ስላገኘን፣ ከዮርዳኖስ ማዶ ከእነርሱ ጋራ የምንካፈለው አንዳችም ርስት አይኖርም።”
20ከዚያም ሙሴ እንዲህ አላቸው፤ “ይህን ብታደርጉ ማለትም በእግዚአብሔር ፊት ታጥቃችሁ ለጦርነት ብትዘጋጁ፣ 21እንዲሁም ጠላቶቹን ከፊቱ አሳድዶ እስኪያስወጣ ድረስ ሁላችሁም በእግዚአብሔር ፊት ለጦርነት ዝግጁ ሆናችሁ ዮርዳኖስን ብትሻገሩ፣ 22ምድሪቱ ለእግዚአብሔር ከተገዛች በኋላ ልትመለሱ ትችላላችሁ፤ ለእግዚአብሔርና ለእስራኤል ካለባችሁም ግዴታ ነጻ ትሆናላችሁ፤ ይህችም ምድር በእግዚአብሔር ፊት ርስታችሁ ትሆናለች።
23“ይህን ባታደርጉ ግን እግዚአብሔርን ትበድላላችሁ፤ ኀጢአታችሁ እንደሚያገኛችሁም ዕወቁ። 24ለሴቶቻችሁና ለልጆቻችሁ ከተሞች፣ ለበግና ለፍየል መንጎቻችሁም ጕረኖች ሥሩላቸው፤ የገባችሁበትን የተስፋ ቃል ግን ፈጽሙ።”
25የጋድና የሮቤል ሰዎች ሙሴን እንዲህ አሉት፤ “እኛ አገልጋዮችህ ጌታችን ያዘዘንን እንፈጽማለን። 26ልጆቻችንና ሚስቶቻችን፣ የበግና የፍየል እንዲሁም የከብት መንጎቻችን እዚሁ በገለዓድ ከተሞች ይቀራሉ፤ 27ባሮችህ ግን ልክ ጌታችን እንዳለው እያንዳንዱ ሰው ለጦርነት ዝግጁ ሆኖ በእግዚአብሔር ፊት ለመዋጋት እንሻገራለን።”
28ከዚያም ሙሴ ለካህኑ ለአልዓዛር፣ ለነዌ ልጅ ለኢያሱና ለእስራኤል ነገድ ቤተ ሰብ አለቆች እነርሱን አስመልክቶ ትእዛዝ ሰጠ፤ 29እንዲህም አላቸው፤ “የጋድና የሮቤል ወንድ ሁሉ፣ እያንዳንዱ ለጦርነት በመዘጋጀት በእግዚአብሔር ፊት ከእናንተ ጋራ ዮርዳኖስን የሚሻገር ከሆነ፣ ምድሪቱም በእጃችሁ ስትገባ የገለዓድን ምድር ርስት አድርጋችሁ ስጧቸው። 30ለጦርነት ተዘጋጅተው ከእናንተ ጋራ ካልተሻገሩ ግን፣ ርስታቸውን ዐብረዋችሁ በከነዓን መካፈል አለባቸው።”
31የጋድና የሮቤል ሰዎች እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “ባሪያዎችህ እግዚአብሔር ያለውን ያደርጋሉ፤ 32ለጦርነት ዝግጁ ሆነን በእግዚአብሔር ፊት ወደ ከነዓን እንሻገራለን፤ የምንወርሰው ርስት ግን ከዮርዳኖስ ወዲህ እዚሁ ይሆናል።”
33ከዚያም ሙሴ፣ የአሞራውያንን ንጉሥ የሴዎንን ግዛትና የባሳንን ንጉሥ የዐግን ግዛት፣ ማለትም ምድሪቱንና ከነከተሞቿ በዙሪያዋ ያለውን ግዛት በሙሉ ለጋድና ለሮቤል ነገዶች እንዲሁም ለዮሴፍ ልጅ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ሰጣቸው።
34የጋድ ልጆች፤ ዲቦንን፣ አጣሮትን፣ አሮዔርን፣ 35ዓጥሮትሾፋንን፣ ኢያዜርን፣ ዮግብሃን፣ 36ቤትኒምራንና ቤትሃራንን የተመሸጉ ከተሞች አድርገው ሠሯቸው፤ እንዲሁም ለበግና ለፍየል መንጎቻቸው ጕረኖዎች አበጁላቸው። 37የሮቤልም ልጆች ሐሴቦንን፣ ኤልያሊንና ቂርያታይምን 38እንዲሁም ስማቸው የተለወጠውን ናባውን፣ በኣልሜዎንን፣ ሴባማንን ዐደሱ፤ ላደሷቸውም ከተሞች ስም አወጡላቸው።
39የምናሴ ልጅ የሆነው የማኪር ዘሮች ወደ ገለዓድ ሄደው ምድሪቱን በመያዝ፣ እዚያ የነበሩትን አሞራውያን አሳደዷቸው፤ 40ስለዚህ ሙሴ ገለዓድን የምናሴ ዘሮች ለሆኑት ለማኪራውያን ሰጣቸው፤ እነርሱም መኖሪያቸውን በዚያው አደረጉ። 41ከምናሴ ነገድ የሆነው ኢያዕር መኖሪያቸውን ወስዶ፣ የኢያዕር መንደሮች ብሎ ሰየማቸው። 42እንዲሁም ኖባህ ቄናትንና በዙሪያዋ ያሉትን መንደሮች በመያዝ በራሱ ስም፣ ኖባህ ብሎ ጠራቸው።

Currently Selected:

ዘኍልቍ 32: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Video for ዘኍልቍ 32