ነህምያ 4
4
ቅጥሩ እንዳይሠራ የተደረገ ተቃውሞ
1ሰንባላጥ ቅጥሩን እንደምንሠራ በሰማ ጊዜ ተቈጣ፤ እጅግም ተበሳጨ። በአይሁድም ላይ ተሣለቀ፤ 2በተባባሪዎቹና በሰማርያ ሰራዊት ፊት፣ “እነዚህ ደካማ አይሁድ ምን እያደረጉ ነው? ቅጥራቸውን መልሰው ሊሠሩ ነውን? መሥዋዕት ሊያቀርቡ ነውን? በአንዲት ጀንበር ሠርተው ሊጨርሱ ነውን? እንደዚያ ተቃጥሎ የፍርስራሽ ክምር የሆነውን ድንጋይ ነፍስ ሊዘሩበት ይችላሉን?” አለ።
3በአጠገቡም ቆሞ የነበረው አሞናዊው ጦቢያ፣ “ለመሆኑ የሚገነቡት ምንድን ነው? በድንጋይ የሚሠሩት ቅጥር እኮ ቀበሮ እንኳ ብትወጣበት ሊፈርስ ይችላል” አለ።
4አምላካችን ሆይ፤ ተንቀናልና ስማን፤ ስድባቸውን በራሳቸው ላይ አውርድባቸው፤ በምርኮ ምድር እንዲበዘበዙ አሳልፈህ ስጣቸው። 5የፈረሰውን በሚሠሩት ፊት የስድብ ናዳ አውርደዋልና#4፥5 ወይም የፈረሰውን በሚሠሩት ፊት እንድትቈጣ አድር ገውሃልና በደላቸውን ይቅር አትበል፤ ኀጢአታቸውንም ከፊትህ አታጥፋው።
6ሕዝቡ ከልቡ ስለሚሠራ፣ ቅጥሩን እኩሌታው ድረስ መልሰን ሠራነው።
7ሰንባላጥ፣ ጦቢያ፣ ዐረቦች፣ የአሞንና የአሽዶድ ሰዎች፣ የኢየሩሳሌም ቅጥር ሥራ እየተፋጠነና ክፍት ቦታዎቹም ሁሉ እየተሞሉ መሆናቸውን በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቈጡ። 8መጥተውም ኢየሩሳሌምን ይወጉ ዘንድ፣ ሽብርንም ይፈጥሩ ዘንድ ሁሉም በአንድነት አደሙ። 9እኛ ግን ወደ እግዚአብሔር ጸለይን፤ ዛቻቸውንም ለመቋቋም ቀንና ሌሊት የሚጠብቁ ዘቦችን መደብን።
10በዚህ ጊዜ የይሁዳ ሕዝብ፣ “የሠራተኞቹ ጕልበት እየደከመ ነው፤ ከፍርስራሹም ብዛት የተነሣ ቅጥሩን መልሰን ለመሥራት አንችልም” አሉ።
11ጠላቶቻችን ደግሞ፣ “በመካከላቸው ገብተን እስክንገድላቸውና ሥራውን እስክናስቆም ድረስ አያውቁም ወይም አያዩም” አሉ።
12ከዚያም በአጠገባቸው የሚኖሩ አይሁድ መጥተው፣ “እናንተ የትም ቦታ ብትሆኑ፣ እኛን ማጥቃታቸው አይቀርም!” በማለት ዐሥር ጊዜ ደጋግመው ነገሩን።
13ስለዚህ ከቅጥሩ በስተ ኋላ በሚገኙ ግልጽ ቦታዎች ላይ ከሕዝቡ አንዳንዶቹ ሰይፋቸውን፣ ጦራቸውንና ቀስታቸውን እንደ ያዙ በየቤተ ሰባቸው በመመደብ ቦታቸውን እንዲይዙ አደረግሁ። 14ነገሩን በጥሞና ከተመለከትሁ በኋላ መኳንንቱን፣ ሹማምቱና የቀረውን ሕዝብ፣ “አትፍሯቸው፤ ታላቁንና የተፈራውን ጌታ አስቡ፤ ስለ ወንድሞቻችሁ፣ ስለ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ፣ ስለ ሚስቶቻችሁና ስለ ቤት ንብረታችሁ ተዋጉ” አልኋቸው።
15አድማቸውን እንዳወቅንባቸውና እግዚአብሔርም ዕቅዳቸውን ከንቱ እንዳደረገባቸው ጠላቶቻችን በሰሙ ጊዜ፣ ሁላችን ወደ ቅጥሩ፣ እያንዳንዳችንም ወደየሥራችን ተመለስን።
16ከዚያን ቀን ጀምሮ ከሰዎቼ እኩሌቶቹ ሥራውን ሠሩ፤ የቀሩት ደግሞ ጋሻና ጦር፣ ቀስትና ጥሩር ይዘው ነበር። የጦር አለቆች ከመላው የይሁዳ ሕዝብ በስተ ኋላ ቆሙ፤ 17እነርሱም ቅጥሩን ይገነቡ ነበር፤ ዕቃ የሚሸከሙት በአንድ እጃቸው ሥራቸውን ሲሠሩ፣ በሌላው እጃቸው የጦር መሣሪያቸውን ይዘው ነበር፤ 18እያንዳንዱም ግንበኛ ቅጥሩን በሚሠራበት ጊዜ ሰይፉን በወገቡ ላይ ታጥቆ ነበር፤ መለከት የሚነፋው ሰው ግን ከእኔ አይለይም ነበር።
19ከዚያም ለመኳንንቱ፣ ለሹማምቱና ለቀረው ሕዝብ እንዲህ አልሁ፤ “ሥራው ታላቅ ነው፤ ብዙም ነው፤ እርስ በርሳችን በቅጥሩ ላይ እጅግ ተራርቀናል፤ 20የመለከት ድምፅ በምትሰሙበት ጊዜ፣ ወደ እኛ ተሰብሰቡ። አምላካችን ስለ እኛ ይዋጋል።”
21ስለዚህ ጎሕ ሲቀድ ጀምሮ ከዋክብት እስኪወጡ ድረስ እኩሌቶቹ ሰዎች ጦራቸውን እንደ ያዙ ሥራውን ቀጠልን። 22በዚያን ጊዜ ለሕዝቡ፣ “ሌሊት ዘብ በመጠበቅና ቀን ሥራ በመሥራት እንዲያገለግለን እያንዳንዱ ሰው ከነረዳቱ በኢየሩሳሌም ይቈይ” አልኋቸው። 23እኔም ሆንሁ ወንድሞቼ፣ ሰዎቼም ሆኑ ከእኔ ጋር ያሉት ጠባቂዎች ልብሳችንን አላወለቅንም፤ ለውሃ እንኳ በምንሄድበት ጊዜ እያንዳንዱ ሰው የጦር መሣሪያውን እንደ ያዘ ነበር።#4፥23 በዕብራይስጡ የዚህ ሐረግ ትርጕም በትክክል አይታወቅም።
Currently Selected:
ነህምያ 4: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.