YouVersion Logo
Search Icon

ነህምያ 5

5
ነህምያ ድኾችን ረዳ
1በዚህ ጊዜ ወንዶቹና ሚስቶቻቸው አይሁድ ወንድሞቻቸውን በመቃወም ብርቱ ጩኸት አሰሙ፤ 2አንዳንዶቹ፣ “እኛም ሆን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን በቍጥር ብዙ ነን፤ ታዲያ ለመብላትም ሆነ በሕይወት ለመቈየት እህል ማግኘት አለብን” አሉ።
3ሌሎቹ፣ “በራቡ ወቅት እህል ለማግኘት ስንል ዕርሻችንን፣ የወይን ተክል ቦታችንንና ቤታችንን እስከ ማስያዝ ደርሰናል” አሉ።
4ሌሎቹ ደግሞ እንዲህ አሉ፤ “የዕርሻችንንና የወይን ተክል ቦታችንን ግብር ለንጉሡ ለመክፈል ገንዘብ እስከ መበደር ደርሰናል። 5ምንም እንኳ ከአገራችን ሰዎች ጋር በሥጋና በደም አንድ ብንሆንም፣ እንደ እነርሱ ልጆች ሁሉ የእኛም ወንዶች ልጆች ጥሩዎች ቢሆኑም፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንን ባሮች እንዲሆኑ ሰጥተናል፤ አንዳንድ ሴቶች ልጆቻችን አሁንም በባርነት ላይ ናቸው፤ ዕርሻችንና የወይን ተክል ቦታችን የሌሎች በመሆናቸው እኛ ደካሞች ሆነናል።” 6እኔም ጩኸታቸውንና እነዚህን አቤቱታዎች በሰማሁ ጊዜ፣ እጅግ ተቈጣሁ፤ 7ከዚያም ነገሩን በሐሳቤ ካወጣሁ ካወረድሁ በኋላ፣ መኳንንቱንና ሹማምቱን ገሠጽኋቸው፤ “ከገዛ አገራችሁ ሰዎች ላይ እንዴት ዐራጣ ትበላላችሁ” አልኋቸውም። ስለዚህ ከእነርሱ ጋር ለመነጋገር ታላቅ ስብሰባ ጠራሁ፤ 8“ለአሕዛብ ተሽጠው የነበሩትን አይሁድ ወንድሞቻችንን በተቻለን ሁሉ ተቤዥተናቸዋል፤ አሁንም እናንተ ወንድሞቻችሁን ትሸጣላችሁ፤ ይህም መልሰን እንድንቤዣቸው ለማድረግ ብቻ ነው!” አልኋቸው፤ እነርሱም የሚመልሱት አልነበራቸውምና ዝም አሉ።
9ስለዚህ በመቀጠል እንዲህ አልሁ፤ “ይህ የምታደርጉት ነገር ትክክል አይደለም፤ የጠላቶቻችንን የአሕዛብን ስድብ ለማስወገድ የአምላካችንን መንገድ በፍርሀት መከተል አይገባችሁምን? 10እኔ፣ ወንድሞቼና ሰዎቼም እንደዚሁ ለሕዝቡ ገንዘብና እህል አበድረናል፤ ዐራጣው ግን ያብቃ። 11ዕርሻቸውን፣ የወይንና የወይራ ዘይት ተክል ቦታቸውንና ቤታቸውን በቶሎ መልሱላቸው፤ እንዲሁም የምታስከፍሏቸውን የገንዘቡን፣ የእህሉን፣ የአዲሱን ወይንና ዘይት አንድ መቶኛ ዐራጣ መልሱላቸው”። 12እነርሱም፣ “እንመልሳለን፤ ምንም ዐይነት ትርፍ አንጠይቃቸውም፤ እንዳልኸን እናደርጋለን” አሉ። ካህናቱን ጠራኋቸው፤ መኳንንቱንና ሹማምቱም የገቡትን ቃል እንዲፈጽሙ አማልኋቸው። 13እንዲሁም የልብሴን ዘርፍ አራግፌ፣ “ይህን የተስፋ ቃል የማይፈጽመውን ማናቸውንም ሰው አምላክ ቤቱንና ንብረቱን እንደዚህ ያራግፈው፤ እንደዚህ ያለውም ሰው ይርገፍ፤ ባዶም ይሁን” አልሁ። በዚህም ጉባኤው ሁሉ፣ “አሜን” በማለት እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ሕዝቡም የገቡትን ቃል ፈጸሙ።
14ከዚህም በላይ በይሁዳ ምድር አገረ ገዥ ሆኜ ከተሾምሁበት፣ ከአርጤክስስ ሃያኛ ዓመት ጀምሮ እስከ ሠላሳ ሁለተኛው ዘመነ መንግሥቱ ድረስ፣ ለዐሥራ ሁለት ዓመት እኔም ሆንሁ ወንድሞቼ ለአንድ አገረ ገዥ የተመደበውን ምግብ ተቀብለን አልበላንም። 15ከእኔ በፊት የነበሩት የቀድሞዎቹ አገረ ገዦች ግን ከምግቡና ከወይኑ ሌላ፣ በሕዝቡ ላይ ከባድ ሸክም በመጫን አርባ ሰቅል#5፥15 0.5 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ብር ይወስዱ ነበር፤ ረዳቶቻቸውም እንዲሁ ይጭኑባቸው ነበር። እኔ ግን እግዚአብሔርን ከመፍራቴ የተነሣ እንዲህ ያለውን አላደረግሁም። 16ከዚህ ይልቅ ራሴን ለዚህ ቅጥር ሥራ ሰጠሁ። ሰዎቼም ሁሉ ለሥራው እዚያው ይሰበሰቡ ነበር፤ ምንም መሬት አልነበረንም#5፥16 ብዙ የዕብራይስጥ ቅጆች ከዚህ ጋር ይስማማሉ፤ አንዳንድ የዕብራይስጥ ቅጆች፣ የሰብዓ ሊቃናት፣ የቩልጌትና የሱረሰት ቅጆች ግን አልነበረኝም ይላሉ።
17ከዚህም በላይ በዙሪያችን ካሉት፣ ወደ እኛ ከሚመጡት አሕዛብ ሌላ አንድ መቶ አምሳ አይሁድና ሹማምት ከማእዴ ይካፈሉ ነበር። 18በየዕለቱም አንድ በሬ፣ ስድስት ምርጥ በጎችና የተወሰኑ ዶሮዎች፣ በየዐሥሩም ቀን ብዛት ያለው ልዩ ልዩ የወይን ጠጅ ይዘጋጅልኝ ነበር። ይህም ሁሉ ሆኖ ለአንድ አገረ ገዥ የተመደበውን ምግብ ከቶ ጠይቄ አላውቅም፤ በሕዝቡ ላይ የተጣለው ሸክም ከባድ ነበርና።
19አምላኬ ሆይ፤ ለዚህ ሕዝብ ያደረግሁትን ሁሉ በበጎነት ዐስብልኝ።

Currently Selected:

ነህምያ 5: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in