YouVersion Logo
Search Icon

ኢዮብ 42

42
ኢዮብ
1ኢዮብም እንዲህ ሲል ለእግዚአብሔር መለሰ፤
2“አንተ ሁሉን ማድረግ እንደምትችል፣
ዕቅድህም ከቶ እንደማይሰናከል ዐወቅሁ።
3አንተ፣ ‘ያለ ዕውቀት ዕቅዴን የሚያደበዝዝ ይህ ማን ነው?’ አልኸኝ፤
በርግጥ ያልገባኝን ነገር፣
የማላውቀውንና ላስተውለው የማልችለውን ጕዳይ ተናገርሁ።
4“ ‘ስማኝ፣ ልናገር እኔ እጠይቃለሁ፤
አንተ ትመልስልኛለህ’ አልኸኝ።
5ጆሮዬ ስለ አንተ ሰምታ ነበር፤
አሁን ግን ዐይኔ አየችህ።
6ስለዚህ ራሴን እንቃለሁ፤
በትቢያና በዐመድ ላይ ተቀምጬ ንስሓ እገባለሁ።”
መደምደሚያ
7 እግዚአብሔር ይህን ለኢዮብ ከተናገረ በኋላ፣ ቴማናዊውን ኤልፋዝን እንዲህ አለው፤ “እንደ አገልጋዬ እንደ ኢዮብ ስለ እኔ ቅን ነገር ስላልተናገራችሁ፣ ቍጣዬ በአንተና በሁለቱ ባልንጀሮችህ ላይ ነድዷል። 8አሁን እንግዲህ ሰባት ወይፈኖችና ሰባት አውራ በጎች ይዛችሁ ወደ አገልጋዬ ወደ ኢዮብ ሂዱ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትም ስለ ራሳችሁ አቅርቡ። እንደ አሳፋሪ ተግባራችሁ እንዳላደርግባችሁ አገልጋዬ ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልያል፤ እኔም ጸሎቱን እቀበላለሁ፤ እንደ አገልጋዬ እንደ ኢዮብ ስለ እኔ ቅን ነገር አልተናገራችሁምና።” 9ቴማናዊው ኤልፋዝ፣ ሹሐዊው በልዳዶስና ናዕማታዊው ሶፋር እግዚአብሔር እንደ ተናገራቸው አደረጉ፤ እግዚአብሔርም የኢዮብን ጸሎት ተቀበለ።
10ኢዮብ ለወዳጆቹ ከጸለየ በኋላ፣ እግዚአብሔር እንደ ገና አበለጸገው፤ ቀድሞ በነበረው ፈንታ ዕጥፍ አድርጎ ሰጠው። 11ወንድሞቹና እኅቶቹ፣ ቀድሞም ያውቁት የነበሩ ሁሉ ወደ እርሱ መጡ፤ በቤቱም ከእርሱ ጋር ምግብ በሉ። እነርሱም ሐዘናቸውን ገለጡለት፤ እግዚአብሔርም ካመጣበት መከራ ሁሉ አጽናኑት፤ እያንዳንዳቸውም ጥሬ ብርና#42፥11 ዕብራይስጡ፣ ኬሊታ ይላል፤ ኬሊታ የገንዘብ ዐይነት ነው፤ ክብደቱና መጠኑ ግን በትክክል አይታወቅም። የወርቅ ቀለበት ሰጡት።
12 እግዚአብሔርም ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን የኢዮብን ሕይወት ባረከ። እርሱም ዐሥራ አራት ሺሕ በጎች፣ ስድስት ሺሕ ግመሎች፣ አንድ ሺሕ ጥማድ በሬዎች፣ አንድ ሺሕ እንስት አህዮችም ነበሩት። 13ደግሞም ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ 14የመጀመሪያዋን ይሚማ፣ ሁለተኛዋን ቃሥያ፣ ሦስተኛዋንም አማልቶያስ ቂራስ ብሎ ሰየማቸው። 15እንደ ኢዮብ ሴቶች ልጆች የተዋቡ ሴቶች በምድሪቱ ሁሉ አልተገኙም፤ አባታቸውም ከወንድሞቻቸው ጋር ርስት ሰጣቸው።
16ከዚህ በኋላ ኢዮብ አንድ መቶ አርባ ዓመት ኖረ፤ ልጆቹንና የልጅ ልጆቹን እስከ አራት ትውልድ ድረስ አየ። 17በዚህ ሁኔታ አርጅቶ፣ ዕድሜ ጠግቦ ሞተ።

Currently Selected:

ኢዮብ 42: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy