ኢዮብ 37
37
1“ልቤ በዚህ በኀይል ይመታል፤
ከስፍራውም ዘለል ዘለል ይላል።
2ስሙ! የድምፁን ጩኸት ስሙ፤
ከአፉ የሚወጣውን ጕርምርምታ አድምጡ።
3መብረቁን ከሰማይ ሁሉ በታች ያባርቃል፤
ወደ ምድርም ዳርቻ ይልካል።
4ከዚያም በኋላ የድምፁ ጩኸት ይመጣል፤
በድምፁም ግርማ ያንጐደጕዳል፤
ድምፁ በተሰማ ጊዜ፣
መብረቁን የሚከለክል የለም።
5የእግዚአብሔር ድምፅ በሚያስደንቅ ሁኔታ ያንጐደጕዳል፤
እኛ የማናስተውለውንም ታላቅ ነገር ያደርጋል።
6በረዶውን፣ ‘በምድር ላይ ውደቅ’
ውሽንፍሩንም ‘ዶፍህን አውርደው’ ይላል።
7እርሱ የፈጠራቸው ሰዎች ሁሉ ሥራውን ያውቁ ዘንድ፣
እያንዳንዱ ሰው እንዳይሠራ ይገታዋል።#37፥7 ወይም፣ ሰዎችን ሁሉ በኀይሉ ያስፈራቸዋል ማለትም ነው።
8እንስሳት ይጠለላሉ፤
በየዋሻቸውም ይቈያሉ።
9ዐውሎ ነፋስ ከማደሪያው፣
ብርድም ከብርቱ ነፋስ ይወጣል።
10የእግዚአብሔር እስትንፋስ በረዶ ያስገኛል፤
ሰፋፊ ውሆች ግግር በረዶ ይሆናሉ።
11ደመናትን ርጥበት ያሸክማቸዋል፤
መብረቁንም በውስጣቸው ይበትናል።
12ያዘዘውን ለመፈጸም፣
እርሱ በሚሰጠው መመሪያ፣
በመላው የምድር ገጽ ላይ ይሽከረከራሉ።
13ሰዎችን ለመቅጣት ደመና ያመጣል፤
ወይም በዚሁ ምድሩን አጠጥቶ#37፥13 ወይም፣ ፍቅሩንም ለመግለጽ ደመናን ያመጣል ፍቅሩን ይገልጻል።
14“ኢዮብ ሆይ፤ ይህን ስማ፤
ቆም ብለህ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ ዐስብ።
15እግዚአብሔር ደመናትን እንዴት እንደሚቈጣጠር፣
መብረቁንም እንዴት እንደሚያባርቅ ታውቃለህን?
16ደመናት ሚዛን ጠብቀው እንዴት እንደሚንሳፈፉ፣
በዕውቀቱ ፍጹም የሆነውን፣ የእርሱን ድንቅ ሥራ ታውቃለህን?
17ምድር በደቡብ ነፋስ ጸጥ ባለች ጊዜ፣
ከሙቀት የተነሣ በልብስህ ውስጥ የምትዝለፈለፍ ሆይ፤
18ከቀለጠ ናስ እንደ ተሠራ መስተዋት የጠነከረውን ሰማይ ሲዘረጋ፣
አብረኸው መዘርጋት ትችል ነበርን?
19“ከጨለማችን የተነሣ እኛ ጕዳያችንን መግለጽ አንችልም፤
ለእርሱ የምንለውን ንገረን።
20እኔ መናገር እንደ ፈለግሁ ሊነገረው ይገባልን?
ይዋጥ ዘንድ የሚጠይቅ ሰው አለን?
21እንግዲህ ነፋስ ሰማያትን ካጠራ በኋላ፣
እጅግ የምታበራዋን ፀሓይ፣
ሊመለከት የሚችል የለም።
22እንደ ወርቅ በሚያበራ ክብር ከሰሜን ይወጣል፤
እግዚአብሔር በሚያስፈራ ግርማ ይመጣል።
23ሁሉን የሚችል አምላክ ከአእምሯችን በላይ ነው፤ በኀይልና በፍርድ ታላቅ ነው፣
ጽድቁም ብዙ ነው፤ ማንንም አይጨቍንም።
24ስለዚህ፣ ሰዎች ይፈሩታል፤
በልባቸው#37፥24 ወይም፣ በልባቸው አስተዋዮች ወደ ሆኑ አስተዋዮች እንደ ሆኑ የሚያስቡትን አይመለከትም?”
Currently Selected:
ኢዮብ 37: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.