ኢሳይያስ 14
14
1 እግዚአብሔር ለያዕቆብ ይራራለታል፤
እስራኤልን እንደ ገና ይመርጠዋል፤
በራሳቸውም አገር ያኖራቸዋል።
መጻተኞች አብረዋቸው ይኖራሉ፤
ከያዕቆብም ቤት ጋር ይተባበራሉ።
2አሕዛብም ይወስዷቸዋል፤
ወደ ገዛ ስፍራቸውም ይመልሷቸዋል።
የእስራኤል ቤት አሕዛብን ርስት ያደርጓቸዋል፤
በእግዚአብሔርም ምድር ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎች አድርገው ይገዟቸዋል፤
የማረኳቸውን ይማርኳቸዋል፤
የጨቈኗቸውንም ይገዟቸዋል።
3 እግዚአብሔር ከሥቃይህ፣ ከመከራህና ከጽኑ ባርነትህ ባሳረፈህ ቀን፣ 4በባቢሎን ንጉሥ ላይ ትሣለቃለህ፤ እንዲህም ትላለህ፤
ጨቋኙ እንዴት አበቃለት!
አስገባሪነቱስ#14፥4 የሙት ባሕር ጥቅልል፣ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕምና የሱርስቱ ቅጅ ከዚህ ጋር ይስማማል፤ ነገር ግን በማሶሬቱ ቅጅ የቃሉ ትርጕም በትክክል አይታወቅም። እንዴት አከተመ!
5 እግዚአብሔር የክፉዎችን ዘንግ፣
የገዦችንም በትረ መንግሥት ሰብሯል፤
6ሕዝቦችን በማያቋርጥ ቍጣ የመታውን፣
ያለ ርኅራኄ እያሳደደ
የቀጠቀጠውን ሰብሯል።
7ምድር ሁሉ ሰላምና ዕረፍት አግኝታለች፤
የደስታም ዝማሬ ታስተጋባለች።
8ጥድና የሊባኖስ ዝግባ እንኳ ደስ ብሏቸው፣
“አንተም ወደቅህ፤
ዕንጨት ቈራጭም
መጥረቢያ አላነሣብንም” አሉ።
9በመጣህ ጊዜ
ሲኦል#14፥9 በዚህና በቍጥር 11 እንዲሁም 15 ላይ አንዳንድ ቅጆች፣ መቃብር ይላሉ። ልትቀበልህ ተነሣሥታለች፤
ይቀበሉህም ዘንድ የሙታንን መናፍስት፣
በዓለም ገዥ የነበሩትን ሁሉ ቀስቅሳለች፤
በአሕዛብ ላይ የነገሡትን ነገሥታት
ከዙፋናቸው አውርዳለች።
10እነርሱ ሁሉ ይመልሱልሃል፤
እንዲህም ይሉሃል፤
“አንተም እንደ እኛ ደከምህ፤
እንደ እኛም ሆንህ።”
11ክብርህ፣ ከነበገና ድምፁ
ወደ ሲኦል ወረደ፤
ብሎች ከበታችህ ተነጥፈዋል፤
ትሎችም መደረቢያህ ይሆናሉ።
12አንተ የንጋት ልጅ፣ አጥቢያ ኮከብ ሆይ፤
እንዴት ከሰማይ ወደቅህ!
አንተ ቀድሞ መንግሥታትን ያዋረድህ፣
እንዴት ወደ ምድር ተጣልህ!
13በልብህም እንዲህ አልህ፤
“ወደ ሰማይ ዐርጋለሁ፤
ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ አደርጋለሁ፤
በተራራው መሰብሰቢያ፣
በተቀደሰውም ተራራ#14፥13 ወይም ሰሜኑ፤ በዕብራይስጡ፣ ዛፎን ተብሎ መተርጐም ይችላል። ከፍታ ላይ በዙፋኔ
እቀመጣለሁ፤
14ከደመናዎችም ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፤
ራሴንም እንደ ልዑል አደርጋለሁ።”
15ነገር ግን ወደ ሲኦል፣
ወደ ጥልቁም ጕድጓድ ወርደሃል።
16የሚያዩህም አትኵረው እየተመለከቱህ፣
በመገረም ስለ አንተ እንዲህ ይላሉ፤
“ያ ምድርን ያናወጠ፣
መንግሥታትን ያንቀጠቀጠ፣ ይህ ሰው ነውን?
17ዓለምን ምድረ በዳ ያደረገ፤
ከተሞችን ያፈራረሰ፣
ምርኮኞቹንም ወደ አገራቸው እንዳይሄዱ የከለከለ ይህ ነውን?”
18የአሕዛብ ነገሥታት ሁሉ በክብር አንቀላፍተዋል፤
በየመቃብራቸው ዐርፈዋል።
19አንተ ግን እንደማይፈለግ ቅርንጫፍ፣
ከመቃብር ወጥተህ ተጥለሃል፤
በሰይፍ በተወጉት፣
ወደ ጥልቁ ድንጋዮች በወረዱት፣
በተገደሉትም ተሸፍነሃል፤
እንደ ተረገጠም ሬሳ ሆነሃል።
20ከእነርሱ ጋር በመቃብር አትሆንም፤
ምድርህን አጥፍተሃልና፤
ሕዝብህንም ፈጅተሃልና።
የክፉ አድራጊዎች ዘር
ፈጽሞ አይታወስም።
21ተነሥተው ምድርን እንዳይወርሱ፣
ዓለምንም በከተሞቻቸው እንዳይሞሉ፣
ስለ አባቶቻቸው ኀጢአት፣
ወንድ ልጆቹ የሚታረዱበትን ስፍራ አዘጋጁ።
22“በእነርሱ ላይ እነሣለሁ”
ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
“ስሟንና ትሩፋኖቿን፣
ዘሯንና ትውልዷን ከባቢሎን እቈርጣለሁ”
ይላል እግዚአብሔር።
23“የጃርት መኖሪያ፣
ረግረጋማ ቦታ አደርጋታለሁ፤
በጥፋትም መጥረጊያ እጠርጋታለሁ”
ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
በአሦር ላይ የተነገረ ትንቢት
24የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ምሏል፤
“እንደ ዐቀድሁት በርግጥ ይከናወናል፤
እንደ አሰብሁትም ይሆናል።
25አሦርን በምድሬ ላይ አደቅቃለሁ፤
በተራራዬም ላይ እረግጠዋለሁ፤
ቀንበሩ ከሕዝቤ ላይ ይነሣል፤
ሸክሙም ከትከሻቸው ላይ ይወርዳል።”
26ለምድር ሁሉ የታሰበው ዕቅድ ይህ ነው፤
በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተዘረጋው እጅ ይኸው ነው።
27የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አስቧል፤
ማንስ ያግደዋል?
እጁም ተዘርግቷል?
ማንስ ይመልሰዋል?
በፍልስጥኤማውያን ላይ የተነገረ ትንቢት
28ንጉሡ አካዝ በሞተበት ዓመት እንዲህ የሚል ንግር መጣ፤
29“እናንት ፍልስጥኤማውያን ሆይ፤
የመታችሁ በትር ስለ ተሰበረ ሁላችሁ ደስ አይበላችሁ፤
ከእባቡ ሥር እፉኝት ይወጣልና፤
ፍሬውም ተወርዋሪ መርዘኛ እባብ ይሆናል።
30ከድኻም ድኻ የሆኑት መሰማሪያ ያገኛሉ፤
ችግረኞችም ተዝናንተው ይተኛሉ፤
ሥርህን ግን በራብ እገድላለሁ፤
ትሩፋንህንም እፈጃለሁ።
31“በር ሆይ፤ ዋይ በል! ከተማ ሆይ፤ ጩኽ!
ፍልስጥኤማውያን ሆይ፤ ሁላችሁም በፍርሀት ቅለጡ!
ጢስ ከሰሜን መጥቶብሃል፤
ከሰልፉ ተነጥሎ የሚቀር የለምና።
32ከዚያ ሕዝብ ለሚመጡ መልእክተኞች ምን መልስ ይሰጣል?
መልሱ፣ ‘እግዚአብሔር ጽዮንን መሥርቷል፤
መከራን የተቀበለው ሕዝብም፣
በእርሷ ውስጥ መጠጊያን አግኝቷል’ የሚል ነው።”
Currently Selected:
ኢሳይያስ 14: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.