YouVersion Logo
Search Icon

ዘፍጥረት 25

25
የአብርሃም መሞት
25፥1-4 ተጓ ምብ – 1ዜና 1፥32-33
1አብርሃም ኬጡራ የተባለች ሌላ ሚስት አገባ።#25፥1 ወይም አግብቶ ነበር 2እርሷም፦ ዘምራንን፣ ዮቅሳንን፣ ሜዳንን፣ ምድያምን፣ የስቦቅንና ስዌሕን ወለደችለት። 3ዮቅሳንም ሳባንና ድዳንን ወለደ፤ የድዳንም ልጆች፦ አሦራውያን፣ ለጡሳውያንና ለኡማውያን ናቸው። 4የምድያም ልጆች፦ ጌፌር፣ ዔፌር፣ ሄኖኅ፣ አቢዳዕና ኤልዳድ ናቸው። እነዚህ ሁሉ የኬጡራ ልጆች ናቸው።
5አብርሃም ያለውን ሀብት ሁሉ ለይስሐቅ አወረሰው፤ 6ለቁባቶቹ ልጆች ግን በሕይወት እያለ ስጦታ አደረገላቸው፤ ከልጁ ከይስሐቅም ርቀው እንዲኖሩ ወደ ምሥራቅ ምድር ሰደዳቸው።
7አብርሃም በጠቅላላው መቶ ሰባ አምስት ዓመት ኖረ። 8ከዚያም ዐረፈ፤ ዕድሜ ጠግቦ በመልካም ሽምግልና ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ። 9ልጆቹ ይስሐቅና እስማኤል በመምሬ አጠገብ በምትገኝ በኬጢያዊው በሰዓር ልጅ በኤፍሮን ዕርሻ በመክፈላ ዋሻ ቀበሩት፤ 10ይህም የዕርሻ ቦታ አብርሃም ከኬጢያውያን#25፥10 ወይም የኬጢ ልጆች የገዛው ነበር፤ ከሚስቱ ከሣራ አጠገብ በዚያ ተቀበረ። 11አብርሃም ከሞተ በኋላ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ይስሐቅን ባረከው፤ በዚህ ጊዜ ይስሐቅ በብኤርላሃይሮኢ አቅራቢያ ይኖር ነበር።
የእስማኤል ልጆች
25፥12-16 ተጓ ምብ – 1ዜና 1፥29-31
12ግብፃዊቷ የሣራ አገልጋይ አጋር፣ ለአብርሃም የወለደችለት የእስማኤል ትውልድ ይህ ነው።
13የእስማኤል ልጆች ስም እንደ ዕድሜያቸው ቅደም ተከተል እንዲህ ነው፦
የእስማኤል በኵር ልጅ ነባዮት፣
ቄዳር፣ ነብዳኤል፣ መብሳም፣
14ማስማዕ፣ ዱማ፣ ማሣ፣
15ኩዳን፣ ቴማን፣ ኢጡር፣
ናፌስና ቄድማ።
16እነዚህ የእስማኤል ልጆች ነበሩ፤ እነርሱም በኖሩባቸውና በሰፈሩባቸው ቦታዎች የዐሥራ ሁለት ነገድ አለቆች ስሞች ናቸው።
17እስማኤል በጠቅላላው መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ። 18ዘሮቹም መኖሪያቸውን ከግብፅ ድንበር አጠገብ፣ ወደ አሦር በሚወስደው መንገድ፣ በኤውላጥና በሱር መካከል አደረጉ፤ ከወንድሞቻቸውም ሁሉ ጋር በጠላትነት ኖሩ።#25፥18 ወይም በስተ ምሥራቅ ኖሩ
ያዕቆብና ዔሳው
19የአብርሃም ልጅ የይስሐቅ ትውልድ ይህ ነው፤
አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፤ 20ይስሐቅ ርብቃን ሲያገባ ዕድሜው አርባ ዓመት ነበር፤ ርብቃ በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ የሚኖረው የሶርያዊው የባቱኤል ልጅ፣ የሶርያዊውም የላባ እኅት ነበረች።
21ይስሐቅ፣ ርብቃ መካን ስለ ነበረች ስለ እርሷ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸለየ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ጸሎቱን ሰማ፤ ርብቃም ፀነሰች። 22ልጆቹም በማሕፀኗ ውስጥ እርስ በርሳቸው ይጋፉ ጀመር፤ እርሷም “ለምን እንዲህ ይሆንብኛል?” ብላ እግዚአብሔርን (ያህዌ) ለመጠየቅ ሄደች።
23 እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲህ አላት፤
“ወገኖች በማሕፀንሽ አሉ፤
ሁለትም ሕዝቦች ከውስጥሽ ተለያይተው ይወጣሉ፤
አንደኛው ከሌላው ይበረታል፤
ታላቁም ለታናሹ አገልጋይ ይሆናል” አላት።
24የመውለጃዋ ጊዜ ሲደርስም፣ እነሆ፤ በማሕፀኗ መንታ ወንዶች ልጆች ነበሩ። 25በመጀመሪያ የተወለደው መልኩ ቀይ፣ ሰውነቱም በሙሉ ጠጕር የለበሰ ነበር፤ ስለዚህ ስሙ ዔሳው#25፥25 ዔሳው ማለት ጠጕራማ ማለት ነው፤ በተጨማሪ ኤዶም ተብሎ ተጠርቷል፤ ትርጕሙም ቀይ ማለት ነው። ተባለ። 26ከዚያም ወንድሙ ተወለደ፤ በእጁም የዔሳውን ተረከዝ ይዞ ወጣ፤ ከዚህም የተነሣ ስሙ ያዕቆብ#25፥26 ያዕቆብ ማለት ተረከዝ ይይዛል ማለት ነው፤ በምሳሌያዊ አገላለጽ ያታልላል ማለት ነው። ተባለ። ርብቃ ልጆቿን ስትወልድ፣ ይስሐቅ የስድሳ ዓመት ሰው ነበር።
27ልጆቹም ዐደጉ፤ ዔሳው ጐበዝ ዐዳኝ፣ የበረሓም ሰው ሆነ፤ ያዕቆብ ግን ጭምት፣ ከድንኳኑ የማይወጣ ሰው ነበር። 28ይስሐቅ ከዐደን የመጣ ሥጋ ደስ ይለው ስለ ነበር፣ ዔሳውን ይወድደው ነበር፤ ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወድደው ነበር።
29አንድ ቀን ያዕቆብ ወጥ እየሠራ ሳለ ዔሳው እጅግ ተርቦ ከዱር መጣ። 30ዔሳውም ያዕቆብን፣ “ቶሎ በል፤ በጣም ርቦኛልና ከዚህ ቀይ ወጥ አብላኝ” አለው። ስለዚህም ስሙ ኤዶም ተባለ።
31ያዕቆብም፣ “በመጀመሪያ ብኵርናህን ሽጥልኝ” አለው።
32ዔሳውም፣ “እነሆ፤ ልሞት ደርሻለሁ፤ ታዲያ ብኵርናው ምን ያደርግልኛል!” አለ።
33ያዕቆብም ዔሳውን፣ “እንግዲያማ፣ አስቀድመህ ማልልኝ” አለው፤ ስለዚህም ማለለት፤ ብኵርናውንም ለያዕቆብ ሸጠለት።
34ያዕቆብም ለዔሳው እንጀራና የምስር ወጥ ሰጠው፤ እርሱም ከበላና ከጠጣ በኋላ ተነሥቶ ሄደ።
ዔሳው ብኵርናውን እንዲህ አድርጎ አቃለላት።

Currently Selected:

ዘፍጥረት 25: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in