ዘፀአት 14
14
1ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ 2“እስራኤላውያን ተመልሰው በሚግዶልና በባሕሩ መካከል ባለው በፊሀሒሮት አጠገብ እንዲሰፍሩ ንገራቸው፤ በበኣልዛፎንም አንጻር በባሕሩ አጠገብ ይስፈሩ። 3‘ፈርዖን እስራኤላውያን ግራ ተጋብተው በምድረ በዳ በመቅበዝበዝ ይንከራተታሉ’ ብሎ ያስባል። 4እኔም የፈርዖንን ልብ ስለማደነድነው ያሳድዳቸዋል፤ ነገር ግን በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ ለራሴ ክብርን አገኛለሁ፤ ግብፃውያንም እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) መሆኔን ያውቃሉ።” እስራኤላውያንም ይህንኑ አደረጉ።
5የግብፅ ንጉሥ ሕዝቡ መሄዳቸው በተነገረው ጊዜ፣ ፈርዖንና ሹማምቱ ስለ እነርሱ የነበራቸውን ሐሳብ በመለወጥ፣ “ምን ማድረጋችን ነው? እስራኤላውያን እንዲሄዱ ለቀቅናቸው፤ አገልግሎታቸውንም ዐጣን” አሉ። 6ስለዚህ ሠረገላው እንዲዘጋጅለት አደረገ፤ ሰራዊቱንም ይዞ ተንቀሳቀሰ። 7ስድስት መቶ ምርጥ ሠረገላዎችን ከሌሎች የግብፅ ሠረገላዎች ጋር ከነጦር አዛዦቻቸው አሰልፎ ተነሣ። 8እግዚአብሔር (ያህዌ) የንጉሡን የፈርዖንን ልብ ስለ አደነደነው በልበ ሙሉነት ከግብፅ የሚወጡትን እስራኤላውያን አሳደዳቸው። 9ግብፃውያን፣ ይኸውም የፈርዖን ፈረሶችና ሠረገላዎች፣#14፥9 በዚህ ስፍራና በ17፡18፡23 እንዲሁም በ28 ሠረገለኞች ፈረሰኞችና እግረኞች ሁሉ እስራኤላውያንን አሳደዷቸው፤ በበአልዛፎን አንጻር በባሕሩ አጠገብ በፊሀሒሮት ሰፍረው ሳሉ ደረሱባቸው።
10ፈርዖን በቀረበ ጊዜ እስራኤላውያን ቀና ብለው ተመለከቱ፤ እነሆ፣ ግብፃውያን ይከታተሏቸው ነበር፤ እነርሱም በታላቅ ፍርሀት ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጮኹ። 11እነርሱም ሙሴን እንዲህ አሉት፤ “በምድረ በዳ እንድንሞት ያመጣኸን በግብፅ መቃብር ቦታ ጠፍቶ ነውን? ከግብፅ አውጥተህ ምን አደረግህልን? 12በግብፅ ሳለን፣ ‘ተወን እባክህ፤ ግብፃውያንን እናገልግል’ አላልንህም ነበርን? በምድረ በዳ ከምንሞት ግብፃውያንን ብናገለግል ይሻል ነበር!”
13ሙሴም ለሕዝቡ መለሰላቸው፤ “አትሸበሩ፣ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ዛሬ የሚያደርግላችሁን መታደግ ታያላችሁ፤ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ዳግም አታዩአቸውም። 14እግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ እናንተ ይዋጋል፤ እናንተ ያለባችሁ መታገሥ ብቻ ነው።”
15ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለምን ትጮኹብኛላችሁ? ይልቅስ እስራኤላውያንን ወደ ፊት እንዲጓዙ ንገራቸው፤ 16ውሃውን ለመክፈል በትርህን አንሣና እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፤ እስራኤላውያን በባሕሩ ውስጥ በየብስ ይሻገራሉ። 17ተከትለዋቸው እንዲገቡም የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፤ በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ፣ በሠረገሎቹና በፈረሰኞቹ ለራሴ ክብርን አገኛለሁ። 18በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ በከበርሁ ጊዜ፣ ግብፃውያን እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።”
19ከዚያም ከእስራኤል ሰራዊት ፊት ፊት ሆኖ ሲሄድ የነበረው የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) መልአክ ተመለሰና ወደ ኋላቸው መጣ፤ የደመናውም ዐምድ እንዲሁ ከፊት ተነሥቶ ከኋላቸው ቆመ፤ 20በግብፅና በእስራኤል ሰራዊት መካከል በመሆን፣ ሌሊቱን ሙሉ ደመናው በአንድ በኩል ጨለማን ሲያመጣ፣ በሌላው በኩል ብርሃን አመጣ፤ ስለዚህ ሌሊቱን በሙሉ አንዱ ወደ ሌላው ሊጠጋ አልቻለም።
21ሙሴ እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሌሊቱን በሙሉ ብርቱ የምሥራቅ ነፋስ አስነሥቶ ባሕሩን ወደ ኋላ በማሸሽ ደረቅ ምድር አደረገው፤ ውሃውም ተከፈለ። 22እስራኤላውያን ውሃው በግራና በቀኝ እንደ ግድግዳ ሆኖ በየብስ በባሕሩ ውስጥ ዐለፉ።
23ግብፃውያንም አሳደዷቸው፤ የፈርዖን ፈረሶች፣ ሰረገሎችና ፈረሰኞች በሙሉ ተከትለዋቸው ወደ ባሕሩ ገቡ። 24ሲነጋጋም እግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳትና በደመና ዐምድ ሆኖ የግብፃውያንን ሰራዊት ቍልቍል ተመለከተ፤ በግብፃውያን ሰራዊት ላይም ሽብር ላከባቸው። 25መንዳት እንዳይችሉም የሠረገላዎቹን መሽከርከሪያዎች አቈላለፈባቸው፤#14፥25 ወይም፤ የሠረገላዎቻቸው መሽከርከሪያዎች ዘለው ወጡ ግብፃውያኑም፣ “ከእስራኤላውያን እንሽሽ! እግዚአብሔር (ያህዌ) ግብፅን እየተዋጋላቸው ነው” አሉ።
26ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “ውሃው ግብፃውያንን ሠረገሎቻቸውንና ፈረሰኞቻቸውን ተመልሶ እንዲሸፍናቸው እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ” አለው። 27ሙሴም እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ ንጋት ላይም ባሕሩ ወደ ቀድሞ ቦታው ተመለሰ። ግብፃውያን ከውሃው ሸሹ፤#14፥27 ወይም፣ ወደ ውሃው ሸሹ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ግብፃውያንን በባሕሩ ውስጥ ጣላቸው። 28ውሃውም ተመልሶ እስራኤላውያንን ተከትለው ወደ ባሕሩ የገቡትን ሠረገሎች፣ ፈረሰኞች፣ መላውን የግብፅ ሰራዊት ሁሉ ሸፈነ። አንድም እንኳ አልተረፈም።
29እስራኤላውያን ግን ውሃው ግራና ቀኝ እንደ ግድግዳ ሆኖ፣ በደረቅ ምድር ባሕሩን ተሻገሩ። 30በዚያች ዕለት እግዚአብሔር (ያህዌ) እስራኤልን ከግብፃውያን እጅ አዳናቸው፤ እስራኤልም የግብፃውያን ሬሳ በባሕሩ ዳርቻ ወድቆ ተመለከቱ። 31እስራኤላውያን እግዚአብሔር (ያህዌ) በግብፃውያን ላይ ያደረገውን ታላቅ ኀይል ባዩ ጊዜ፣ እግዚአብሔርን (ያህዌ) ፈሩ፤ በእግዚአብሔርና (ያህዌ) በባሪያው በሙሴም አመኑ።
Currently Selected:
ዘፀአት 14: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.