YouVersion Logo
Search Icon

ዘፀአት 13

13
በኵር ሁሉ ለእግዚአብሔር መቀደሱ
1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ 2“መጀመሪያ የተወለደውን ወንድ ሁሉ ለእኔ ቀድስልኝ፤ ከእስራኤላውያን መካከል የእናቱ የበኵር ልጅ የሆነው ማሕፀን ከፋች ሰውም ሆነ እንስሳ የእኔ ነው።”
3ከዚያም ሙሴ ሕዝቡን እንዲህ አለ፤ “ከባርነት ምድር ከግብፅ የወጣችሁባትን ይህችን ዕለት አስታውሱ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር (ያህዌ) በኀያል ክንዱ አውጥቷችኋል። እርሾ ያለበትን ማንኛውንም ነገር አትብሉ። 4እነሆ በዚች ዕለት በአቢብ ወር ወጥታችኋል። 5እግዚአብሔር (ያህዌ) ለእናንተ ለመስጠት ሲል ቀድሞ ለአባቶቻችሁ ወደ ማለላቸው ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ወደ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ አሞራውያን፣ ኤዊያውያን፣ ኢያቡሳውያን ምድር በምትገቡበት ጊዜ ይህን በዓል በዚህ ወር ታከብራላችሁ። 6ለሰባት ቀን ያለ እርሾ የተጋገረ ቂጣ ትበላላችሁ፤ በሰባተኛውም ቀን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓል ታደርጋላችሁ። 7በእነዚህም ሦስት ቀናት ያልቦካ ቂጣ ትበላላችሁ፤ በእናንተ ዘንድ እርሾ ያለበት ነገር ፈጽሞ አይገኝ፤ በምድራችሁም አዋሳኝ በየትኛውም ቦታ እርሾ ፈጽሞ አይኑር። 8በዚያችም ዕለት፣ ‘እኔ ይህን የማደርገው ከግብፅ ምድር በወጣሁበት ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) ስላደረገልኝ ነገር ነው’ ብለህ ለልጅህ ንገረው። 9የእግዚአብሔር (ያህዌ) ሕግ በከንፈራችሁ ላይ እንዲሆን ይህ በዓል ለእናንተ በእጃችሁ ላይ እንደ ታሰረ ምልክት፣ በእግራችሁ ላይ እንደሚገኝ መታሰቢያ ይሆንላችኋል። እግዚአብሔር (ያህዌ) በኀያል ክንዱ ከግብፅ አውጥቷችኋልና። 10ይህን ሥርዐት በተወሰነው ጊዜ በየዓመቱ ጠብቁት።
11እግዚአብሔር (ያህዌ) ለእናንተና ለቀደሙት አባቶቻችሁ በመሐላ በሰጠው ተስፋ መሠረት ወደ ከነዓናውያን አገር በሚያስገባችሁና ምድሪቱንም ለእናንተ በሚሰጣችሁ ጊዜ፣ 12የእናቱን ማሕፀን የሚከፍተውን ሁሉ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ትሰጣላችሁ፤ እንደዚሁም እንስሶቻችሁ በመጀመሪያ የወለዷቸው ወንዶች ሁሉ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ይሆናሉ። 13ከአህያ በመጀመሪያ የተወለደውን ውርንጫ ግን በጠቦት ትዋጁታላችሁ፤ አህያውን ካልዋጃችሁት ግን ዐንገቱን ስበሩት። ከወንድ ልጆቻችሁ መካከል በኵር የሆኑትን ሁሉ ዋጁ።
14“በሚመጡት ዘመናት ልጅህ፣ ‘ይህ ምን ማለት ነው?’ ብሎ ቢጠይቅህ እንዲህ በለው፤ ‘ከባርነት ምድር ከግብፅ እግዚአብሔር (ያህዌ) በኀያል ክንዱ አወጣን፤ 15ፈርዖን እኛን አልለቅም ብሎ ልቡን ባደነደነ ጊዜ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ በኵር ሆኖ በግብፅ የተወለደውን ሁሉ እግዚአብሔር (ያህዌ) ገደለው። እንግዲህ በመጀመሪያ የእናቱን ማሕፀን የከፈተውን ወንድ ሁሉ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የምሠዋውና የልጆቼ በኵር ሆኖ የተወለደውን ወንድ ልጅ ሁሉ የምዋጀው በዚህ ምክንያት ነው።’ 16እግዚአብሔር (ያህዌ) በኀያል ክንዱ እኛን ከግብፅ ያወጣን ስለሆነ ይህ ሥርዐት በእጅህም ሆነ በግንባርህ ላይ እንደ ምልክት ይሆናል።”
ቀይ ባሕርን መሻገር
17ፈርዖን ሕዝቡን በለቀቀ ጊዜ አቋራጭ ቢሆንም እንኳ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በፍልስጥኤም ምድር በሚያልፈው መንገድ አልመራቸውም፤ “ጦርነት ቢያጋጥማቸው ሐሳባቸውን ለውጠው ወደ ግብፅ ይመለሱ ይሆናል” ብሏልና። 18ስለዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሕዝቡን ዙሪያ በሆነው በምድረ በዳው መንገድ ወደ ቀይ ባሕር#13፥18 በዕብራይስጡ ያም ሱፍ ይላል፤ ትርጕሙም የሸንበቆ ባሕር ማለት ነው። መራቸው፤ እስራኤላውያንም ለጦርነት ዝግጁ ሆነው ከግብፅ ወጡ። 19ዮሴፍ፣ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በርግጥ ይጐበኛችኋል፤ በዚያን ጊዜም ዐፅሜን ይዛችሁ ከዚች ምድር መውጣት አለባችሁ”#13፥19 ዘፍ 50፥25 ይመ ብሎ የእስራኤልን ልጆች አስምሏቸው ስለ ነበር ሙሴ የዮሴፍን ዐፅም ይዞ ወጣ። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሕዝቡን ዙሪያ በሆነው በምድረ በዳው መንገድ ወደ ቀይ ባሕር መራቸው፤ እስራኤላውያንም ለጦርነት ዝግጁ ሆነው ከግብፅ ወጡ።
20እነርሱም ከሱኮት ከተነሡ በኋላ ከምድረ በዳው ጥግ ባለው በኤታም ሰፈሩ። 21ስለዚህ በቀንም ሆነ በሌሊት መጓዝ ይችሉ ዘንድ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) በቀን በመንገዳቸው ሊመራቸው በደመና ዓምድ፣ በሌሊት ደግሞ ብርሃን ሊሰጣቸው በእሳት ዐምድ በፊታቸው ይሄድ ነበር። 22በቀንም ሆነ በሌሊት የደመናውና የእሳቱ ዐምድ ከሕዝቡ ፊት የተለየበት ጊዜ አልነበረም።

Currently Selected:

ዘፀአት 13: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in