YouVersion Logo
Search Icon

2 ነገሥት 18

18
የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ
18፥2-4 ተጓ ምብ – 2ዜና 29፥1-231፥1
18፥5-7 ተጓ ምብ – 2ዜና 31፥20-21
18፥9-12 ተጓ ምብ – 2ነገ 17፥3-7
1የእስራኤል ንጉሥ የኤላ ልጅ ሆሴዕ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የአካዝ ልጅ ሕዝቅያስ ነገሠ። 2በነገሠም ጊዜ ዕድሜው ሃያ ዐምስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ። እናቱ የዘካርያስ ልጅ ስትሆን፣ ስሟ አቢያ#18፥2 በዕብራይስጡ አቢ ይለዋል። ይህም የአቢያ ሌላ መጠሪያ ነው። ይባል ነበር። 3አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ። 4በየኰረብታው ላይ ያሉትን የማምለኪያ ዐምዶች አስወገደ፤ አዕማደ ጣዖታትን ሰባበረ፤ የአሼራን ምስል ዐምዶች ቈራረጠ፤ ሙሴ የሠራውን የናስ እባብ፣ እስራኤላውያን እስከ እነዚያ ጊዜያት ድረስ ዕጣን ያጤሱለት ስለ ነበር ሰባበረው፤ ይህም ነሑሽታን#18፥4 ነሑሽታን የሚለው በዕብራይስጡ ንሓስ እና እባብ ከሚለው ጋራ ይመሳሰላል። ይባል ነበር።
5ሕዝቅያስም በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ታመነ፤ ከርሱ በፊትም ሆነ ከርሱ በኋላ ከይሁዳ ነገሥታት ሁሉ፣ እንደ እርሱ ያለ አልነበረም። 6እግዚአብሔር ጋራ ተጣበቀ፤ እርሱን ከመከተል ወደ ኋላ አላለም፤ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠውንም ትእዛዞች ጠበቀ። 7እግዚአብሔር ከርሱ ጋራ ስለ ነበር የሚያደርገው ሁሉ ተከናወነለት። በአሦር ንጉሥ ላይ ዐመፀ፤ ግብር መገበሩንም ተወ። 8እስከ ጋዛና እስከ ግዛቷ ዳርቻ በመዝለቅ ፍልስጥኤማውያንን ከመጠበቂያ ማማ እስከ ተመሸገችው ከተማ ድረስ ድል አደረጋቸው።
9ሕዝቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ የእስራኤልም ንጉሥ የኤላ ልጅ ሆሴዕ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት፣ የአሦር ንጉሥ ስልምናሶር ወደ ሰማርያ ገሥግሦ ከተማዪቱን ከበባት፤ 10በሦስተኛውም ዓመት መጨረሻ ያዛት። ሰማርያ የተያዘችውም ሕዝቅያስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት፣ ሆሴዕ በእስራኤል ላይ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት ነበር። 11የአሦር ንጉሥ እስራኤልን ማርኮ ወደ አሦር በማፍለስ በአላሔ፣ በጎዛን ውስጥ በአቦር ወንዝ አጠገብና በማዴ ከተሞች አሰፈራቸው። 12ይህ የደረሰባቸውም የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ያዘዘውን የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ከመስማት ይልቅ ኪዳኑን ስላፈረሱ ነበር፤ ትእዛዞቹን አላደመጡም፤ ደግሞም አልፈጸሙም።
13ንጉሥ ሕዝቅያስ በነገሠ በዐሥራ አራተኛው ዓመት፣ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም የተመሸጉትን የይሁዳ ከተሞች ሁሉ አጥቅቶ ያዛቸው። 14ስለዚህ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ፣ “በደለኛው እኔ ነኝ፤ ተመለስልኝ፤ እኔም የምትጠይቀኝን ሁሉ እከፍላለሁ፤” ሲል በለኪሶ ወደ ሰፈረው ወደ አሦር ንጉሥ ይህን መልእክት ላከ። የአሦርም ንጉሥ፣ የይሁዳን ንጉሥ ሕዝቅያስን ሦስት መቶ መክሊት#18፥14 10 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው። ብርና ሠላሳ መክሊት#18፥14 አንድ ሜትሪክ ቶን ያህል ነው። ወርቅ እንዲያገባለት ጠየቀው። 15ስለዚህ ሕዝቅያስ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤቶች የሚገኘውን ብር ሁሉ ሰጠው።
16በዚህ ጊዜም የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ፣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መዝጊያዎችና መቃኖች ላይ የለበጠውን ወርቅ ነቃቅሎ ለአሦር ንጉሥ ሰጠው።
ሰናክሬም ኢየሩሳሌምን አስፈራራ
18፥1318፥17-37 ተጓ ምብ – ኢሳ 36፥1-22
18፥17-35 ተጓ ምብ – 2ዜና 32፥9-19
17የአሦር ንጉሥ ከለኪሶ የጦሩን ጠቅላይ አዛዥ፣ ዋና አዛዡንና የጦር መሪውን ከታላቅ ሰራዊት ጋራ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ወዳለበት ወደ ኢየሩሳሌም ላከ፤ እነርሱም ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው፣ ወደ ልብስ ዐጣቢው ዕርሻ በሚወስደው መንገድ ላይ የሚገኘው የላይኛው ኵሬ ውሃ ቦይ በሚወርድበት ስፍራ ሲደርሱ ቆሙ። 18ወደ ንጉሡም ላኩበት፤ ከዚያም የቤተ መንግሥቱ አዛዥ፣ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣ ጸሓፊው ሳምናስ፣ ታሪክ መዝጋቢውም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ወደ እነርሱ ሄዱ።
19የጦር አዛዡም እንዲህ አላቸው፤ “ሕዝቅያስን እንዲህ በሉት፤
“ ‘ታላቁ ንጉሥ፣ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፤ እስከዚህ የተማመንህበት ነገር ምንድን ነው? 20የጦር ስልትና ኀይል አለኝ ትላለህ፤ ነገር ግን ባዶ ቃል ብቻ ትናገራለህ። በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተደግፈህ ነው? 21እነሆ፤ እንዲህ የምትመካባት ግብጽ የሚደገፍባትን ሰው እጅ ወግታ የምታቈስል፣ የተቀጠቀጠች ሸንበቆ ናት። የግብጽ ንጉሥ ፈርዖንም ለሚመኩበት ሁሉ እንደዚሁ ነው። 22ደግሞም፣ “በአምላካችን በእግዚአብሔር እንታመናለን” የምትለኝ ከሆነ፣ የኰረብታ ላይ ማምለኪያዎቹንና መሠዊያዎቹን ሕዝቅያስ አፍርሶበት ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም፣ “እናንተ መስገድ ያለባችሁ በዚህ መሠዊያ ፊት ብቻ ነው” ብሎ የለምን?
23“ ‘አሁን ናና፣ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋራ ተደራደር፤ የሚጋልቧቸው ሰዎች ካሉህ፣ ሁለት ሺሕ ፈረሶች እሰጥሃለሁ። 24የምትመካው በግብጽ ሠረገሎችና#18፥24 ወይም፣ ሠረገለኞች ፈረሶች ሆኖ ሳለ፣ ከጌታዬ የበታች የጦር ሹማምት እንኳ አንዱን እንዴት መመለስ ትችላለህ? 25በተጨማሪም አደጋ ጥዬ ይህችን ስፍራ ለማጥቃትና ለማጥፋት የመጣሁት፣ ያለ እግዚአብሔር ይመስልሃል? በዚህች አገር ላይ ዘምቼ እንዳጠፋት የነገረኝ ራሱ እግዚአብሔር ነው።’ ”
26ከዚያም የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣ ሳምናስና ዮአስ የጦር አዛዡን፣ “እኛ አገልጋዮችህ ስለምንሰማ፣ እባክህን በሶርያ ቋንቋ ተናገር፤ በቅጥሩ ላይ ያሉት ሰዎች በሚሰሙት በዕብራይስጥ አትናገረን” አሉት።
27ነገር ግን የጦር አዛዡ መልሶ፣ “ጌታዬ እነዚህን ቃሎች እንድናገር የላከኝ ለጌታህና ለአንተ ብቻ ነበርን? እንደ እናንተ የራሳቸውን ኵስ ለመብላትና ሽንታቸውንም ለመጠጣት በቅጥሩ ላይ ለተቀመጡት ሰዎችም አይደለምን?” አላቸው።
28የጦር አዛዡም ቆሞ በዕብራይስጥ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “እንግዲህ የታላቁን የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ! 29ንጉሡ እንዲህ ይላል፤ ከእጄ ሊያድናችሁ አይችልምና ሕዝቅያስ አያታልላችሁ፤ 30ደግሞም ሕዝቅያስ፣ ‘እግዚአብሔር በርግጥ ያድነናል፤ ይህች ከተማ ለአሦር ንጉሥ ዐልፋ አትሰጥም’ እያለ በእግዚአብሔር እንድትታመኑ አያድርጋችሁ።
31“ሕዝቅያስን አትስሙ። የአሦር ንጉሥ የሚለው ይህ ነው፤ ‘ከእኔ ጋራ ተስማሙ፤ ወደ እኔም ውጡ። ከዚያም እያንዳንዳችሁ ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ትበላላችሁ፤ ከጕድጓዳችሁም ውሃ ትጠጣላችሁ፤ 32ይኸውም የእናንተኑ ወደምትመስለው ምድር እህልና የወይን ጠጅ፣ ዳቦና የወይን ተክል፣ የወይራ ዛፍና ማር ወዳለባት እስካገባችሁ ድረስ ነው፤ እናንተም ሞትን ሳይሆን ሕይወትን ምረጡ።’
“ሕዝቅያስ፣ ‘እግዚአብሔር ይታደገናል’ በማለት ስለሚያሳስታችሁ አትስሙት። 33ለመሆኑ ምድሩን ከአሦር ንጉሥ እጅ የታደገ ከአሕዛብ አማልክት የትኛው ነው? 34የሐማትና የአርፋድ አማልክት ወዴት አሉ? የሴፈርዋይም፣ የሄናና የዒዋም አማልክት ታዲያ የት ደረሱ? ሰማርያን ከእጄ አድነዋታልን? 35ከእነዚህ አገሮች አማልክት ሁሉ አገሩን ከእጄ የታደገ ማን አለ? ታዲያ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን እንዴት ከእጄ ሊታደጋት ይችላል?”
36ነገር ግን ሕዝቡ ዝም አለ፤ ምንም መልስ አልሰጠም፤ ንጉሡ፣ “መልስ እንዳትሰጡ” ሲል አዝዞ ነበርና።
37ከዚያም የቤተ መንግሥቱ አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣ ጸሓፊው ሳምናስ እንዲሁም ታሪክ መዝጋቢው የአሳፍ ልጅ ዮአስ ልብሳቸውን ቀድደው ወደ ሕዝቅያስ መጡ፤ የጦር አዛዡ የተናገረውንም ሁሉ ነገሩት።

Currently Selected:

2 ነገሥት 18: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in