2 ነገሥት 14
14
የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ
14፥1-7 ተጓ ምብ – 2ዜና 25፥1-4፤ 25፥11-12
14፥8-22 ተጓ ምብ – 2ዜና 25፥17–26፥2
1የእስራኤል ንጉሥ የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ ነገሠ። 2በነገሠም ጊዜ ዕድሜው ሃያ ዐምስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ። እናቱም ዮዓዳን የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች። 3እርሱም በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ፤ ነገር ግን አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ዐይነት አልነበረም፤ በማናቸውም ረገድ የአባቱን የኢዮአስን ፈለግ ተከተለ። 4በየኰረብታው ላይ ያሉት የማምለኪያ ስፍራዎች ገና አልተወገዱም፤ ሕዝቡም በዚያ መሥዋዕት ማቅረቡንና ዕጣን ማጤሱን እንደ ቀጠለ ነበር።
5መንግሥቱም በእጁ ከጸናለት በኋላ፣ ንጉሡን አባቱን የገደሉትን ሹማምት ገደላቸው። 6ይሁን እንጂ በሙሴ የሕግ መጽሐፍ እግዚአብሔር፣ “ሰው ሁሉ በገዛ ኀጢአቱ ይሙት እንጂ ወላጆች በልጆቻቸው አይገደሉ፣ ልጆችም በወላጆቻቸው ኀጢአት አይገደሉ”#14፥6 ዘዳ 24፥16 ይመ። ሲል ያዘዘ በመሆኑ፣ የነፍሰ ገዳዩን ልጆች አልገደላቸውም።
7የጨው ሸለቆ በተባለው ቦታ ዐሥር ሺሕ ኤዶማውያንን ድል ያደረገ፣ ሴላን በጦርነት የያዘና እስከ ዛሬም ድረስ ዮቅትኤል ተብላ የምትጠራበትን ስም ያወጣላት አሜስያስ ነው።
8ከዚያም አሜስያስ የኢዩ የልጅ ልጅ፣ የኢዮአካዝ ልጅ ወደ ሆነው ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ዮአስ፣ “ናና ፊት ለፊት እንጋጠም” ሲል መልእክተኞች ላከበት።
9የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ግን ለይሁዳ ንጉሥ ለአሜስያስ እንዲህ ሲል ላከበት፤ “አንድ የሊባኖስ ኵርንችት፣ ለአንድ የሊባኖስ ዝግባ፣ ‘ሴት ልጅህን ለልጄ ሚስት እንድትሆነው ስጠው’ አለው፤ ከዚያም አንድ የሊባኖስ ዱር አውሬ መጥቶ ኵርንችቱን በእግሩ ረገጠው። 10በርግጥ ኤዶምን ድል አድርገሃል፤ ልብህ በትዕቢት ተወጥሯል። ክብርህን ጠብቀህ ዐርፈህ በቤትህ ተቀመጥ! ጠብ በመጫር በራስህና በይሁዳ ላይ ውድቀት ለማምጣት ችግር የምትፈጥረው ለምንድን ነው?”
11አሜስያስ ግን አልሰማም፤ ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ወጣ፤ እርሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም በይሁዳ ምድር በቤትሳሚስ ፊት ለፊት ተጋጠሙ። 12ይሁዳ በእስራኤል ድል ሆነ፤ እያንዳንዱም ወደ ድንኳኑ ሸሸ። 13የእስራኤል ንጉሥ ዮአስም የአካዝያስን የልጅ ልጅ፣ የኢዮአስን ልጅ የይሁዳን ንጉሥ አሜስያስን ቤትሳሚስ ላይ ማረከው። ከዚያም ዮአስ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፤ ከኤፍሬም ቅጥር በር አንሥቶ የማእዘን ቅጥር በር እስከ ተባለው ድረስ ርዝመቱ አራት መቶ ክንድ#14፥13 180 ሜትር ያህል ርዝመት ያለውን የኢየሩሳሌምን ቅጥር አፈረሰ። 14በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤቶች ያለውን ወርቅ ብርና ዕቃ በሙሉ፣ በዚያም የተገኘውን ዕቃ ሁሉ በመውሰድ ምርኮኞችንም ይዞ ወደ ሰማርያ ተመለሰ።
15በዮአስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር፣ ያደረገውና የፈጸመው ሁሉ በይሁዳ ንጉሥ በአሜስያስ ላይ ያደረገው ጦርነት ጭምር በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 16ዮአስ ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ በሰማርያም ከእስራኤል ነገሥታት ጋራ ተቀበረ፤ ልጁ ኢዮርብዓምም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።
17የኢዮአስ ልጅ የይሁዳ ንጉሥ የአሜስያስ፣ የእስራኤል ንጉሥ የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ ከሞተ በኋላ ዐሥራ ዐምስት ዓመት ኖረ። 18በአሜስያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?
19አሜስያስ በኢየሩሳሌም ሤራ ስለ ጠነሰሱበት ሸሽቶ ወደ ለኪሶ ሄደ፤ እነርሱ ግን የሚከታተሉትን ሰዎች ወደ ለኪሶ ላኩ፤ እነርሱም ገደሉት፤ 20አስከሬኑን በፈረስ ጭነው አመጡ። እንደ አባቶቹም ሁሉ በዳዊት ከተማ፣ በኢየሩሳሌም ተቀበረ።
21ከዚያም የይሁዳ ሕዝብ በሙሉ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት የሆነውን ዓዛርያስን ወስደው በአባቱ በአሜስያስ ፈንታ አነገሡት። 22ንጉሥ አሜስያስ ከአባቶቹ ጋራ ካንቀላፋ በኋላ ኤላትን እንደ ገና ሠርቶ ወደ ይሁዳ የመለሳት ይኸው ዓዛርያስ#14፥22 በተጨማሪም ኡዚያ ተብሎ ይጠራል። ነበር።
የእስራኤል ንጉሥ ዳግማዊ ኢዮርብዓም
23የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ በይሁዳ በነገሠ በዐሥራ ዐምስተኛው ዓመት፣ የእስራኤል ንጉሥ የዮአስ ልጅ ኢዮርብዓም በሰማርያ ነገሠ፤ አርባ አንድ ዓመትም ገዛ። 24በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም። 25የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በጋትሔፌር ነቢይ፣ በአማቴ ልጅ በባሪያው በዮናስ አማካይነት እንደ ተናገረው፣ ከሐማት መተላለፊያ#14፥25 ሊቦ አንሥቶ እስከ ሙት ባሕር#14፥25 የዓረባ ባሕር ድረስ የነበረውን የእስራኤልን ድንበር አስመለሰ።
26ባሪያም ይሁን ነጻ፣ በእስራኤል የሚኖር ሁሉ በመራር ሥቃይ#14፥26 ወይም እስራኤልም ይሠቃይ ነበረ። መሪ ወይም ገዥ አልነበራቸውምና። እንዴት እንደ ኖረ፣ እስራኤልንም የሚረዳ እንዳልነበረ፣ እግዚአብሔር አየ። 27ይሁን እንጂ እግዚአብሔር የእስራኤልን ስም ከምድረ ገጽ እንደሚያጠፋ ስላልተናገረ፣ በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም አማካይነት ታደጋቸው።
28በኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር፣ የፈጸመው ሁሉና ያደረጋቸው ጦርነቶች እንዲሁም የይሁዳ ግዛት የነበሩትን ደማስቆንና ሐማትን እንዴት ለእስራኤል እንዳስመለሰ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 29ኢዮርብዓም ከአባቶቹ ከእስራኤል ነገሥታት ጋራ አንቀላፋ፤ ልጁ ዘካርያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።
Currently Selected:
2 ነገሥት 14: NASV
Highlight
Share
Copy

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.