2 ነገሥት 13
13
የእስራኤል ንጉሥ ኢዮአካዝ
1የይሁዳ ንጉሥ የአካዝያስ ልጅ ኢዮአስ በነገሠ በሃያ ሦስተኛው ዓመት፣ የኢዩ ልጅ ኢዮአካዝ በሰማርያ ከተማ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ዐሥራ ሰባት ዓመትም ገዛ። 2እርሱም የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ያሳተበትን ኀጢአት በመከተል በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠራ፤ ከዚህ ድርጊቱም አልተመለሰም። 3የእግዚአብሔር ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፤ ስለዚህ የሶርያ ንጉሥ አዛሄልና ልጁ ቤን ሃዳድ በነበሩበት ዘመን ሁሉ አሳልፎ በእጃቸው ሰጣቸው።
4ከዚያም ኢዮአካዝ እግዚአብሔርን ለመነ፤ እግዚአብሔርም የሶርያ ንጉሥ እስራኤልን እንዴት አድርጎ እንዳስጨነቀ አይቷልና ልመናውን ሰማው። 5ስለዚህ እግዚአብሔር ለእስራኤል የሚታደጋቸውን ሰው ሰጠ፤ እነርሱም ከሶርያውያን ጭቈና ተላቀቁ፤ እንደ ቀድሞውም በየድንኳናቸው መኖር ጀመሩ፤ 6ይሁን እንጂ እስራኤልን ከአሳተው ከኢዮርብዓም ቤት ኀጢአት አልተመለሱም፤ በዚያው ገፉበት እንጂ። የአሼራም ምስል ዐምድ#13፥6 በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ሁሉ ይህ የአሼራን ሴት ጣዖት የሚያመለክት ነው። በሰማርያ መመለኩ ቀጠለ።
7ከኢዮአካዝ ሰራዊት የተረፈው ዐምሳ ፈረሰኞች፣ ዐሥር ሠረገሎችና ዐሥር ሺሕ እግረኛ ወታደር ብቻ ነው፤ ይህ የሆነበትም ምክንያት የሶርያ ንጉሥ የቀረውን ስለ አጠፋውና እንደ ዐውድማ ብናኝ ስለ አደረገው ነበር።
8ኢዮአካዝ በዘመነ መንግሥቱ ያከናወነው ሌላው ሥራ፣ ያደረገውና የፈጸመውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 9ኢዮአካዝ ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ በሰማርያም ተቀበረ። ልጁ ዮአስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።
የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ
10በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአስ ዘመን፣ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት፣ የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ በሰማርያ ከተማ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ዐሥራ ስድስት ዓመትም ገዛ። 11እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠራ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ከአሳተበት ኀጢአት ሁሉ አልራቀም፤ በዚያው ገፋበት።
12ዮአስ በዘመነ መንግሥቱ ያከናወነው ሌላ ሥራ፣ ያደረገውና የፈጸመው ሁሉ እንዲሁም በይሁዳ ንጉሥ በአሜስያስ ላይ ያካሄደው ጦርነት ጭምር በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 13ዮአስም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ ኢዮርብዓም በእግሩ ተተክቶ በዙፋኑ ተቀመጠ። ዮአስም በሰማርያ ከእስራኤል ነገሥታት ጋራ ተቀበረ።
14በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ ለሞት ባደረሰው ሕመም ታምሞ ነበር። የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ ሊጠይቀው ወርዶ አለቀሰለት፤ “ወየው አባቴን! ወየው አባቴን! ወየው የእስራኤል ሠረገሎችና ፈረሰኞች!” እያለም ጮኸ።
15ኤልሳዕም፣ “አንድ ቀስትና ፍላጾች አምጣ” አለው፤ እርሱም አመጣ፤ 16የእስራኤልንም ንጉሥ፣ “ቀስቱን በእጅህ ያዘው” አለው፤ ቀስቱን በያዘውም ጊዜ ኤልሳዕ እጆቹን በንጉሡ እጆች ላይ አኖረ።
17ቀጥሎም፣ “የምሥራቁን መስኮት ክፈት” አለው፤ ከፈተውም፤ ኤልሳዕም፣ “በል አስፈንጥረው” አለው፤ አስፈነጠረውም፤ ከዚያም፣ “የእግዚአብሔር የድል ቀስት! ሶርያ ድል የምትሆንበት ቀስት!” አለ። ኤልሳዕም እንደ ገና “ሶርያውያንንም አፌቅ ላይ ፈጽመህ ድል ታደርጋቸዋለህ” አለው።
18ቀጥሎም፣ “በል ቀስቶቹን ውሰድ” አለው፤ የእስራኤልም ንጉሥ ወሰደ። ኤልሳዕም፣ “መሬቱን ውጋ” አለው፤ እርሱም ሦስት ጊዜ ወግቶ አቆመ። 19የእግዚአብሔርም ሰው ተቈጣውና፣ “መሬቱን ዐምስት ወይም ስድስት ጊዜ መውጋት ነበረብህ፤ እንዲህ ብታደርግ ኖሮ ሶርያን ታሸንፍና ፈጽመህ ትደመስሳት ነበር፤ አሁን ግን የምታሸንፈው ሦስት ጊዜ ብቻ ነው” አለው።
20ኤልሳዕ ሞተ፤ ቀበሩትም።
በዚህም ጊዜ ሞዓባውያን አደጋ ጣዮች በየዓመቱ በጸደይ ወራት ወደ እስራኤል ምድር እየሰረጉ ይገቡ ነበር። 21አንድ ጊዜ እስራኤላውያን ሰው ሞቶ ሲቀብሩ፣ አንድ የአደጋ ጣይ ቡድን በድንገት አዩ፤ ስለዚህ የሞተውን ሰው ሬሳ ኤልሳዕ መቃብር ውስጥ ጣሉት፤ ሬሳው የኤልሳዕን ዐፅም እንደ ነካም ወዲያውኑ ሰውየው ድኖ በእግሩ ቆመ።
22በኢዮአካዝ ዘመነ መንግሥት ሁሉ፣ የሶርያ ንጉሥ አዛሄል፣ እስራኤልን ያስጨንቃቸው ነበር። 23እግዚአብሔር ግን ራራላቸው፤ ዐዘነላቸው፤ ፊቱን መለሰላቸው፤ ይህም ከአብርሃም፣ ከይሥሐቅና ከያዕቆብ ጋራ ስለ ገባው ኪዳን ሲል ነው፤ እስከ ዛሬ ድረስ ሊያጠፋቸው አልፈለገም፤ ከፊቱም አላስወገዳቸውም።
24የሶርያ ንጉሥ አዛሄል ሞተ፤ ልጁ ቤን ሃዳድም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ። 25ከዚያም የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ፣ አዛሄል ከአባቱ ከኢዮአካዝ እጅ በጦርነት የወሰዳቸውን ከተሞች ከአዛሄል ልጅ ከቤን ሃዳድ አስመልሶ ያዘ። ዮአስ ሦስት ጊዜ ድል አደረገው፤ የእስራኤልንም ከተሞች በዚህ ሁኔታ መልሶ ያዘ።
Currently Selected:
2 ነገሥት 13: NASV
Highlight
Share
Copy

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.