ማሕልየ መሓልይ 7:6-13
ማሕልየ መሓልይ 7:6-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በራስሽ ላይ ያለው ጠጕርሽ እንደ ቀርሜሎስ ተራራ ነው፤ የጠጕርሽም ሹርባ እንደ ሐምራዊ ሐር ነው፥ ንጉሡም በሹርባው ታስሯል። ወዳጄ ሆይ፥ እንዴት የተዋብሽ ነሽ! እንዴትስ ደስ ታሰኛለሽ! ደስታሽንም እወድደዋለሁ። ይህ ቁመትሽ የዘንባባ ዛፍ ይመስላል፥ ጡቶችሽም የወይን ዘለላ ይመስላሉ። ወደ ዘንባባው ዛፍ እወጣለሁ ጫፉንም እይዛለሁ አልሁ፤ ጡቶችሽ እንደ ወይን ዘለላ ናቸው፥ የአፍንጫሽም ሽታ እንደ እንኮይ ነው። ጕሮሮሽም ለልጅ ወንድሜ እየጣፈጠ እንደሚገባ፥ ለከንፈሮችና ለምላሴ እንደሚስማማ እንደ ማለፊያ የወይን ጠጅ ነው። እኔ የልጅ ወንድሜ ነኝ፥ የእርሱም መመለሻው ወደ እኔ ነው። ልጅ ወንድሜ ሆይ፥ ና፥ ወደ መስክ እንውጣ፥ በመንደሮችም እንደር። ወደ ወይኑ ቦታ ማልደን እንሂድ፤ ወይኑ አብቦ፥ አበባውም ፍሬ አንዠርግጎ ሮማኑም አፍርቶ እንደ ሆነ እንይ፤ በዚያ ጡቶቼን እሰጥሃለሁ።
ማሕልየ መሓልይ 7:6-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንዴት ውብ ነሽ! እንዴትስ ደስ የምትይ ነሽ! ፍቅሬ ሆይ፤ የምታስደስቺ ነሽ። ቁመናሽ እንደ ዘንባባ ዛፍ መለል ያለ ነው፤ ጡቶችሽም የፍሬውን ዘለላ ይመስላሉ። እኔም፣ “የዘንባባውን ዛፍ እወጣለሁ፤ ዘለላዎቹንም እይዛለሁ” አልሁ። ጡቶችሽ የወይን ዘለላ፣ የእስትንፋስሽም መዐዛ እንደ እንኮይ ፍሬ ይሁኑ፤ ከናፍሮችሽም እንደ ማለፊያ የወይን ጠጅ ይጣፍጡ። የወይን ጠጁ በቀስታ እየተንቈረቈረ፣ ወደ ውዴ ከንፈሮችና ጥርሶች ይውረድ። እኔ የውዴ ነኝ፤ የእርሱም ምኞት እኔው ነኝ። ውዴ ሆይ፤ ና ወደ ገጠር እንሂድ፤ ወደ መንደርም ገብተን እንደር፤ ማልደን ወደ ወይኑ ተክል ቦታ እንሂድ፣ ወይኑ እንቡጥ አውጥቶ፣ አበባው ፈክቶ፣ ሮማኑ አፍርቶ እንደ ሆነ እንይ፤ በዚያም ራሴን በፍቅር እሰጥሃለሁ። ትርንጐዎች መዐዛቸውን ሰጡ፤ አዲስ የተቀጠፈውም ሆነ የበሰለው፣ ጣፋጩ ፍሬ ሁሉ በደጃፋችን አለ፤ ውዴ ሆይ፤ ለአንተ አስቀምጬልሃለሁ።
ማሕልየ መሓልይ 7:6-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ራስሽ እንደ ቀርሜሎስ ተራራ በላይሽ ነው፥ የራስሽም ጠጕር እንደ ሐምራዊ ሐር ነው፥ ንጉሡ በሹርባው ታስሮአል። ወዳጄ ሆይ፥ እንዴት የተዋብሽ ነሽ! እንዴትስ ደስ ታሰኛለሽ! ይህ ቍመትሽ የዘንባባ ዛፍ ይመስላል፥ ጡቶችሽም የወይን ዘለላ ይመስላሉ። ወደ ዘንባባው ዛፍ እወጣለሁ ጫፎችዋንም እይዛለሁ አልሁ፥ ጡቶችሽ እንደ ወይን ዘለላ የአፍንጫሽም ሽቱ እንደ እንኮይ ናቸው። ጕሮሮሽ ለወዳጄ እየጣፈጠ እንደሚገባ፥ የተኙትን ከንፈሮች ይናገሩ ዘንድ እንደሚያደርግ፥ እንደ ማለፊያ የወይን ጠጅ ነው። እኔ የውዴ ነኝ፥ የእርሱም ምኞት ወደ እኔ ነው። ውዴ ሆይ፥ ና፥ ወደ መስክ እንውጣ በመንደሮችም እንደር። ወደ ወይኑ ቦታ ማልደን እንሂድ፥ ወይኑ አብቦ አበባውም ፍሬ አንዠርግጎ ሮማኑም አፍርቶ እንደ ሆነ እንይ፥ በዚያ ውዴን እሰጥሃለሁ።
ማሕልየ መሓልይ 7:6-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ውዴ ሆይ! እንዴት ያማርሽ ነሽ? እንዴትስ ውብ ነሽ? ፍቅርሽ እንዴት ያስደስታል? ቁመናሽ የዘንባባ ዛፍ ይመስላል፤ ጡቶችሽም ዘለላውን ይመስላሉ። በዘንባባው ዛፍ ላይ ወጥቼ ፍሬውን መልቀም እወዳለሁ፤ ጡቶችሽ እንደ ወይን ዘለላ ዕቅፍ ይሁኑ፤ የእስትንፋስሽ መዓዛ እንደ ፖም ፍሬ ሽታ ነው። የአፍሽም መዓዛ እንደ መልካም ወይን ጠጅ ነው። እንግዲያውስ መልካሙ የወይን ጠጅ በውዴ ከንፈሮችና ጥርሶች መካከል እየተንቆረቆረ በዝግታ ይውረድ። እኔ የውዴ ነኝ፤ የእርሱም ምኞት ወደ እኔ ነው። ውዴ ሆይ! ና፤ ከከተማ ወጥተን ወደ ገጠር እንሂድ፤ ሌሊቱን በዚያ እናሳልፍ። ማልደንም ወደ ወይኑ ተክል ቦታ እንሂድ፤ የወይኑ አበባ ፈክቶ እንደ ሆነ፥ ሮማኑም አብቦ እንደ ሆነ እንይ፤ በዚያም ፍቅሬን እገልጥልሃለሁ። የእንኰይ ፍሬ መዓዛና እንዲሁም ደስ የሚያሰኙ ልዩ ልዩ ፍራፍሬዎች ደጃችንን ሞልተውታል። ውዴ ሆይ! ከነዚህም ፍሬዎች የበሰሉትንና አዲስ የተቀጠፉትን ለአንተ አኑሬልሃለሁ።
ማሕልየ መሓልይ 7:6-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ፍቅር ሆይ፥ እንዴት የተዋብሽ ነሽ! እንዴትስ ደስ ታሰኛለሽ! በተድላ ይህ ቁመትሽ የዘንባባ ዛፍ ይመስላል፥ ጡቶችሽም አስካሉን ይመስላሉ። ወደ ዘንባባው ዛፍ እወጣለሁ ጫፎችዋንም እይዛለሁ አልሁ፥ ጡቶችሽ እንደ ወይን ዘለላ የአፍንጫሽም ሽቱ እንደ እንኮይ ናቸው። አፍሽ ለወዳጄ እየጣፈጠ እንደሚገባ፥ የተኙትን ከንፈሮች ይናገሩ ዘንድ እንደሚያደርግ፥ እንደ ማለፊያ የወይን ጠጅ ነው። እኔ የውዴ ነኝ፥ የእርሱም ምኞት ወደ እኔ ነው። ውዴ ሆይ፥ ና፥ ወደ መስክ እንውጣ በመንደሮችም እንደር። ወደ ወይኑ ቦታ ማልደን እንሂድ፥ ወይኑ አብቦ አበባውም ፍሬ አንዠርግጎ ሮማኑም አፍርቶ እንደሆነ እንይ፥ በዚያ ፍቅሬን እሰጥሃለሁ። ትርንጎዎች መዓዛን ሰጡ፥ መልካሞች ፍሬዎች ሁሉ፥ አሮጌው ከአዲሱ ጋር፥ በደጃችን አሉ፥ ውዴ ሆይ፥ ሁሉን ለአንተ ጠበቅሁልህ።