የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማሕልየ መሓልይ 7

7
1አንቺ የልዑል ልጅ ሆይ፤
ነጠላ ጫማ የተጫሙ እግሮችሽ፣
እንዴት ያምራሉ!
ሞገስን የተጐናጸፉ ዳሌዎችሽ፣
ብልኅ አንጥረኛ የተጠበባቸውን የዕንሐብል ይመስላሉ።
2ዕንብርትሽ ጥሩ የወይን ጠጅ እንደማይጐድልበት፣
እንደ ክብ ጽዋ ነው፤
ወገብሽ ዙሪያውን በውብ አበባ የታሰረ፣
የስንዴ ክምር ይመስላል።
3ሁለት ጡቶችሽ፣
መንታ የዋሊያ ግልገሎችን ይመስላሉ።
4ዐንገትሽ በዝኆን ጥርስ እንዳጌጠ መጠበቂያ ማማ ነው፤
ዐይኖችሽ በባትረቢ በር አጠገብ እንዳሉት፣
እንደ ሐሴቦን ኵሬዎች ናቸው፤
አፍንጫሽ ወደ ደማስቆ አቅጣጫ እንደሚመለከት፣
እንደ ሊባኖስ መጠበቂያ ማማ ነው።
5የራስሽ ቅርጽ እንደ ቀርሜሎስ ተራራ አክሊል ሆኖልሻል፤
ጠጕርሽ የሐር ጕንጕን የመሰለ ነው፤
ንጉሡም በሹሩባሽ ታስሮ ተይዟል።
6እንዴት ውብ ነሽ! እንዴትስ ደስ የምትይ ነሽ!
ፍቅሬ ሆይ፤ የምታስደስቺ ነሽ።
7ቁመናሽ እንደ ዘንባባ ዛፍ መለል ያለ ነው፤
ጡቶችሽም የፍሬውን ዘለላ ይመስላሉ።
8እኔም፣ “የዘንባባውን ዛፍ እወጣለሁ፤
ዘለላዎቹንም እይዛለሁ” አልሁ።
ጡቶችሽ የወይን ዘለላ፣
የእስትንፋስሽም መዐዛ እንደ እንኮይ ፍሬ ይሁኑ፤
9ከናፍሮችሽም እንደ ማለፊያ የወይን ጠጅ ይጣፍጡ።
ሙሽራዪቱ
የወይን ጠጁ በቀስታ እየተንቈረቈረ፣
ወደ ውዴ ከንፈሮችና ጥርሶች ይውረድ።#7፥9 ሰብዓ ሊቃናት፣ አቍሚላ፣ ቨልጌትና ሱርስት እንዲሁ ሲሆኑ፣ ዕብራይስጡ ግን ወደ ተኙ ሰዎች ከንፈሮች ይላል
10እኔ የውዴ ነኝ፤
የእርሱም ምኞት እኔው ነኝ።
11ውዴ ሆይ፤ ና ወደ ገጠር እንሂድ፤
ወደ መንደርም#7፥11 ወይም ወደ ሄና ቍጥቋጦች ገብተን እንደር፤
12ማልደን ወደ ወይኑ ተክል ቦታ እንሂድ፣
ወይኑ እንቡጥ አውጥቶ፣
አበባው ፈክቶ፣
ሮማኑ አፍርቶ እንደ ሆነ እንይ፤
በዚያም ራሴን በፍቅር እሰጥሃለሁ።
13ትርንጐዎች መዐዛቸውን ሰጡ፤
አዲስ የተቀጠፈውም ሆነ የበሰለው፣
ጣፋጩ ፍሬ ሁሉ በደጃፋችን አለ፤
ውዴ ሆይ፤ ለአንተ አስቀምጬልሃለሁ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ