ሮሜ 2:17-29
ሮሜ 2:17-29 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አንተ አይሁዳዊ፥ በኦሪትህ የምታርፍ፥ በእግዚአብሔርም የምትመካ ከሆንህ፥ ፈቃዱን የምታውቅ፥ መልካሙንም የምትለይ፥ ኦሪትንም የተማርህ ከሆንህ፥ አንተ የዕውሮች መሪ፥ በጨለማም ላሉት ብርሃን እንደ ሆንህ በራስህ የምትታመን ከሆንህ፥ ሰነፎችን ልባሞች የምታደርግ፥ ሕፃናትን የምታስተምር፥ ጻድቅና የምትከብርበትን የኦሪትን ሕግ የምታውቅ የምትመስል፥ እንግዲህ ሌላውን የምታስተምር ራስህን እንዴት አታስተምርም? አትስረቁ ትላለህ፤ ነገር ግን አንተ ራስህ ትሰርቃለህ። አታመንዝሩ ትላለህ፤ ነገር ግን አንተ ራስህ ታመነዝራለህ፤ ወደ ጐልማሳ ሚስትም ትሄዳለህ፤ ጣዖትን ትጸየፋለህ፤ አንተ ግን ቤተ መቅደስን ትዘርፋለህ። በኦሪት ትመካለህ፤ ነገር ግን አንተ ራስህ ኦሪትን በመሻር እግዚአብሔርን ታቃልለዋለህ። እንደ ተጻፈም “እነሆ፥ በእናንተ ምክንያት አሕዛብ የእግዚአብሔርን ስም ይሰድባሉ።” ኦሪትንም ብትፈጽም ግዝረት ትጠቅምሃለች፤ ኦሪትን ባትፈጽም ግን ግዝረትህ አለመገዘር ትሆንብሃለች። አንተ ሳትገዘር ብትኖር፥ ኦሪትንም ብትጠብቅ አለመገዘርህ መገዘር ትሆንልሃለች። ተገዝረህ ኦሪትን ከምታፈርስ በተፈጥሮ ያገኘሃት አለመገዘርህ አብራህ ብትኖር ይሻልሃል፤ ኦሪትን ከምታፈርስ ከአንተ ከተገዘርኸው ያ ያልተገዘረው፥ ኦሪትን የሚፈጽመው ይሻላል። በውኑ ለሰው ይምሰል አይሁዳዊ መሆን ይገባልን? ለሰው ፊትስ ተብሎ ይገዘሩአልን? ዳሩ ግን አይሁዳዊነት በስውር ነው፤ መገዘርም በመንፈስ የልብ መገዘር እንጂ በኦሪት ሥርዐት አይደለም፤ ምስጋናውም ከእግዚአብሔር ነው እንጂ ከሰው አይደለም።
ሮሜ 2:17-29 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አንተ ይሁዲ ነኝ ካልህ፣ በሕግ የምትተማመንና ከእግዚአብሔር ጋራ ባለህ ግንኙነት የምትኵራራ፣ በሕግ በመመራትህም ፈቃዱን ዐውቀህ ፍጹም የሆነውን ለይተህ ከያዝህ፣ ለዕውሮች መሪ፣ በጨለማ ላሉትም ብርሃን መሆንህን ርግጠኛ ከሆንህ፣ በሕጉም ካገኘኸው ዕውቀትና እውነት የተነሣ አላዋቂ ለሆኑት መካሪ፣ ለሕፃናት አስተማሪ ከሆንህ፣ እንግዲህ አንተ ሌሎችን የምታስተምር፣ ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ፣ ትሰርቃለህን? አንተ ሰዎች ማመንዘር የለባቸውም የምትል፣ ታመነዝራለህን? አንተ ጣዖትን የምትጸየፍ፣ ቤተ መቅደስን ትመዘብራለህን? አንተ በሕግ የምትመካ፣ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታዋርዳለህን? ይህም “በእናንተ ምክንያት የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ ዘንድ ይሰደባል” ተብሎ እንደ ተጻፈው መሆኑ ነው። ሕግን የምትፈጽም ከሆነ ግዝረት ዋጋ አለው፤ ሕግን የምትተላለፍ ከሆነ ግን እንዳልተገረዝህ ሆነሃል። ያልተገረዙት ሕጉ የሚያዝዘውን የሚፈጽሙ ከሆነ፣ እንደ ተገረዙ አይቈጠሩምን? አንተ የተጻፈ ሕግ፣ ግዝረትም ቢኖርህ፣ ሕግ ተላላፊ በመሆንህ፣ በሥጋ ያልተገረዘው ለሕግ በመታዘዙ ይፈርድብሃል። አንድ ሰው ለይምሰል በውጫዊው ብቻ ይሁዲ ልሁን ቢል ይሁዲ አይሆንም፤ እውነተኛ ግዝረትም ውጫዊና ሥጋዊ ሥርዐት አይደለም። ዳሩ ግን አንድ ሰው ይሁዲ የሚሆነው በውስጣዊ ማንነቱ ይሁዲ ሆኖ ሲገኝ ነው። ግዝረትም ግዝረት የሚሆነው በተጻፈው ሕግ ሳይሆን፣ በመንፈስ የልብ ግዝረት ሲኖር ነው። እንዲህ ያለው ሰው ምስጋናው ከሰው ሳይሆን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።
ሮሜ 2:17-29 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አንተ ግን አይሁዳዊ ብትባል በሕግም ብትደገፍ በእግዚአብሔርም ብትመካ፥ ፈቃዱንም ብታውቅ ከሕግም ተምረህ የሚሻለውን ፈትነህ ብትወድ፤ በሕግም የእውቀትና የእውነት መልክ ስላለህ፥ የዕውሮች መሪ፥ በጨለማም ላሉ ብርሃን፥ የሰነፎችም አስተማሪ፥ የሕፃናትም መምህር እንደ ሆንህ በራስህ ብትታመን፤ እንግዲህ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህን? አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን? ጣዖትን የምትጸየፍ ቤተ መቅደስን ትዘርፋለህን? በሕግ የምትመካ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታሳፍራለህን? በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባልና ተብሎ እንደ ተጻፈ። ሕግን ብታደርግ መገረዝስ ይጠቅማል፤ ሕግን ተላላፊ ብትሆን ግን መገረዝህ አለ መገረዝ ሆኖአል። እንግዲህ ያልተገረዘ ሰው የሕግን ሥርዓት ቢጠብቅ አለመገረዙ እንደ መገረዝ ሆኖ አይቈጠርለትምን? ከፍጥረቱም ያልተገረዘ ሕግን የሚፈጽም ሰው የሕግ መጽሐፍና መገረዝ ሳለህ ሕግን በምትተላለፈው በአንተ ይፈርድብሃል። በግልጥ አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ አይደለምና፥ በግልጥ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም መገረዝ አይደለምና፤ ዳሩ ግን በስውር አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ ነው፥ መገረዝም በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በመጽሐፍ አይደለም፤ የእርሱ ምስጋና ከእግዚአብሔር ነው እንጂ ከሰው አይደለም።
ሮሜ 2:17-29 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እነሆ፥ አንተ “አይሁዳዊ ነኝ” ትላለህ፤ በሕግ ትደገፋለህ፤ የእግዚአብሔር በመሆንህም ትመካለህ። አንተ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ታውቃለህ፤ ሕግን ስለ ተማርክ መልካም ማድረግን ታውቃለህ። “አንተ ለዕውሮች መሪ ነኝ፤ በጨለማ ላሉትም ብርሃን ነኝ፤ ያልተማሩትን አሠለጥናለሁ፤ ሕፃናትን አስተምራለሁ” ትላለህ፤ እንዲሁም “በሕግ የዕውቀትና የእውነት ምልአት አለኝ” ትላለህ። ሌሎችን የምታስተምር ስትሆን ታዲያ ራስህን ለምን አታስተምርም? አትስረቁ ትላለህ፤ አንተ ግን ትሰርቃለህ፤ አታመንዝሩ ትላለህ፤ አንተ ግን ታመነዝራለህ፤ አንተ ጣዖቶችን ትጸየፋለህ፤ ቤተ መቅደሶቻቸውን ግን ትዘርፋለህ። አንተ በእግዚአብሔር ሕግ ትመካለህ፤ ነገር ግን ሕጉን በማፍረስ እግዚአብሔርን ትንቃለህ። ይህም፥ “በእናንተ በአይሁድ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ ዘንድ ይሰደባል” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። መገረዝ በእርግጥ የሚጠቅምህ ሕግን ብትፈጽም ነው፤ ሕግን የምታፈርስ ከሆነ ግን መገረዝህ እንደ አለመገረዝ ይቈጠራል። ስለዚህ ያልተገረዘው የአሕዛብ ወገን የሕግን ትእዛዝ የሚፈጽም ከሆነ አለመገረዙ እንደ መገረዝ ይቈጠርለት የለምን? አንተ የተጻፈ ሕግ እያለህና የተገረዝክም ሆነህ ሕግን ብታፈርስ በሥጋ ያልተገረዘ ሆኖ ሕግን የሚፈጽም የአሕዛብ ወገን ይፈርድብሃል። እንግዲህ በስም ብቻ አይሁዳዊ የሆነ እውነተኛ አይሁዳዊ አይደለም፤ እንዲሁም በውጭ የሚታይ የሥጋ መገረዝ እውነተኛ መገረዝ አይደለም። እውነተኛ አይሁዳዊ በውስጥ አይሁዳዊ የሆነ ነው፤ እውነተኛ መገረዝ በእግዚአብሔር መንፈስ የሚሆን የልብ መገረዝ ነው እንጂ በሕግ በተጻፈው መሠረት የሥጋ መገረዝ አይደለም። እንዲህ ዐይነቱም ሰው ምስጋናን የሚቀበለው ከእግዚአብሔር ነው እንጂ ከሰው አይደለም።
ሮሜ 2:17-29 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አንተ ግን አይሁዳዊ ነኝ ካልህ በሕግም ከተደገፍክ በእግዚአብሔርም ከተመካህ፥ ፈቃዱንም ካወቅህ፥ ሕግም ስለተማርህ የሚሻለውን ከወሰድህ፥ ለዓይነ ስውሮች መሪ፥ በጨለማ ላሉትም ብርሃን እንደሆንህ በራስህ የምትተማመን ከሆነ፥ የሞኞች አስተማሪ፥ የሕፃናት መምህር ነኝ ካልህ፥ በሕግም የእውቀትና የእውነት አርአያ ካለህ፥ ስለዚህ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ እየሰበክ ትሰርቃለህን? አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን? ጣዖቶችን የምትጠላ ቤተ መቅደሶችን ትዘርፋለህን? በሕግ የምትመካ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታዋርዳለህን? ይህም “በእናንተ ምክንያት የእግዚአብሔር ስም በሕዝቦች መካከል ይሰደባልና” ተብሎ እንደተጻፈው ነው። ሕግን የምትፈጽም ከሆነ መገረዝ ይጠቅማል፤ ሕግን የምትተላለፍ ከሆነ ግን መገረዝህ እንደ አለመገረዝ ሆኖአል። ስለዚህ ያልተገረዘው የሕግን ሥርዓት ከጠበቀ አለመገረዙ እንደ መገረዝ ሆኖ አይቆጠርለትምን? ከፍጥረቱ ያልተገረዘው፥ ሕግንም የሚጠብቀው፥ የሕግ መጽሐፍና መገረዝ እያለህ ሕግን በምትተላለፈው በአንተ ላይ ይፈርድብሃል። በስም አይሁዳዊ ሆኖ የሚታይ አይሁዳዊ አይደለምና፤ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም መገረዝ አይደለምና፤ ነገር ግን በስውር አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ ነው፤ መገረዝም በመንፈስ የሆነ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በፊደል አይደለም፤ ምስጋናውም ከእግዚአብሔር ነው እንጂ ከሰው አይደለም።