ወደ ሮሜ ሰዎች 2
2
የእግዚአብሔር ትክክለኛ ፍርድ
1 #
ማቴ. 7፥1፤ ሉቃ. 6፥37። ስለዚህ አንተ የምትፈርድ ሰው ሆይ! የምታመካኘው የለህም፤ በሌላው ላይ በምትፈርድበት ነገር በራስህ ላይ ትፈርዳለህ፤ ፈራጅ የሆንከው አንተ ያንኑ ታደርጋለህና። 2እንደዚህ በሚያደርጉት ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ እውነተኛ እንደሆነ እናውቃለን። 3አንተም እንደዚህ በሚያደርጉ ላይ የምትፈርድ ያንንም የምታደርግ ሰው ሆይ! ከእግዚአብሔር ፍርድ የምታመልጥ ይመስልሃልን? 4#ጥበ. 11፥23።ወይስ የቸርነቱን፥ የቻይነቱን፥ የታጋሽነቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን? የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሓ ሊመራህ እንደሆነ አታውቅምን? 5ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሓ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቁጣ ቀን በራስህ ላይ ቁጣን ታከማቻለህ። 6#መዝ. 62፥12፤ ምሳ. 24፥12።እርሱ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ይሰጠዋል፤ 7በመልካም ሥራ በመጽናት ምስጋናንና ክብርን የማይጠፋንም ሕይወት ለሚፈልጉ የዘለዓለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል፤ 8በራስ ወዳዶች፥ ለእውነት በማይታዘዙት ነገር ግን ለዐመፃ በሚታዘዙት ላይ ቁጣና መቅሠፍት ይመጣባቸዋል። 9ክፉ በሚያደርግ ሰው ሁሉ ላይ፥ አስቀድሞ በአይሁዳዊ ከዚያም በግሪካዊ መከራና ጭንቀት ይሆንበታል፤ 10ነገር ግን መልካምን ለሚሠራ ሁሉ አስቀድሞ አይሁዳዊ ከዚያም ግሪካዊ ምስጋና፥ ክብርና ሰላም ይሆንለታል። 11#ዘዳ. 10፥17።በእግዚአብሔር ዘንድ ማዳላት የለምና።
12ሕግ ሳይኖራቸው ኃጢአት የሠሩ ሁሉ ያለ ሕግ ደግሞ ይጠፋሉና፤ ሕግ እያላቸው ኃጢአት የሠሩ ሁሉ በሕግ ይፈረድባቸዋል፤ 13በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚፈፅሙት ይጸድቃሉ እንጂ ሕግን የሚሰሙት አይጸድቁምና። 14ሕግ የሌላቸው አሕዛብ፥ ሕግ የሚያዘውን ነገር በተፈጥሮአቸው ሲያደርጉ፥ እነዚያ ሕግ ባይኖራቸውም ለራሳቸው ሕግ ናቸውና፥ 15ሕሊናቸው ሲመሰክርላቸው፥ እርስ በእርሳቸው ሐሳባቸው ሲካሰስ ወይም ሲከላከል፥ በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ። 16ይህም እኔ በወንጌል እንዳስተማርሁት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር የሰዎችን የተሰወሩ ነገሮች በሚፈርድበት ቀን ይሆናል።
አይሁድና የሙሴ ሕግ
17አንተ ግን አይሁዳዊ ነኝ ካልህ በሕግም ከተደገፍክ በእግዚአብሔርም ከተመካህ፥ 18ፈቃዱንም ካወቅህ፥ ሕግም ስለተማርህ የሚሻለውን ከወሰድህ፥ 19ለዓይነ ስውሮች መሪ፥ በጨለማ ላሉትም ብርሃን እንደሆንህ በራስህ የምትተማመን ከሆነ፥ 20የሞኞች አስተማሪ፥ የሕፃናት መምህር ነኝ ካልህ፥ በሕግም የእውቀትና የእውነት አርአያ ካለህ፥ 21ስለዚህ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ እየሰበክ ትሰርቃለህን? 22አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን? ጣዖቶችን የምትጠላ ቤተ መቅደሶችን ትዘርፋለህን? 23በሕግ የምትመካ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታዋርዳለህን? 24#ኢሳ. 52፥5።ይህም “በእናንተ ምክንያት የእግዚአብሔር ስም በሕዝቦች መካከል ይሰደባልና” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።
25ሕግን የምትፈጽም ከሆነ መገረዝ ይጠቅማል፤ ሕግን የምትተላለፍ ከሆነ ግን መገረዝህ እንደ አለመገረዝ ሆኖአል። 26ስለዚህ ያልተገረዘው የሕግን ሥርዓት ከጠበቀ አለመገረዙ እንደ መገረዝ ሆኖ አይቆጠርለትምን? 27ከፍጥረቱ ያልተገረዘው፥ ሕግንም የሚጠብቀው፥ የሕግ መጽሐፍና መገረዝ እያለህ ሕግን በምትተላለፈው በአንተ ላይ ይፈርድብሃል። 28በስም አይሁዳዊ ሆኖ የሚታይ አይሁዳዊ አይደለምና፤ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም መገረዝ አይደለምና፤ 29#ዘዳ. 30፥6።ነገር ግን በስውር አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ ነው፤ መገረዝም በመንፈስ የሆነ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በፊደል አይደለም፤ ምስጋናውም ከእግዚአብሔር ነው እንጂ ከሰው አይደለም።
Currently Selected:
ወደ ሮሜ ሰዎች 2: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ