ወደ ሮሜ ሰዎች 2:17-29

ወደ ሮሜ ሰዎች 2:17-29 መቅካእኤ

አንተ ግን አይሁዳዊ ነኝ ካልህ በሕግም ከተደገፍክ በእግዚአብሔርም ከተመካህ፥ ፈቃዱንም ካወቅህ፥ ሕግም ስለተማርህ የሚሻለውን ከወሰድህ፥ ለዓይነ ስውሮች መሪ፥ በጨለማ ላሉትም ብርሃን እንደሆንህ በራስህ የምትተማመን ከሆነ፥ የሞኞች አስተማሪ፥ የሕፃናት መምህር ነኝ ካልህ፥ በሕግም የእውቀትና የእውነት አርአያ ካለህ፥ ስለዚህ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ እየሰበክ ትሰርቃለህን? አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን? ጣዖቶችን የምትጠላ ቤተ መቅደሶችን ትዘርፋለህን? በሕግ የምትመካ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታዋርዳለህን? ይህም “በእናንተ ምክንያት የእግዚአብሔር ስም በሕዝቦች መካከል ይሰደባልና” ተብሎ እንደተጻፈው ነው። ሕግን የምትፈጽም ከሆነ መገረዝ ይጠቅማል፤ ሕግን የምትተላለፍ ከሆነ ግን መገረዝህ እንደ አለመገረዝ ሆኖአል። ስለዚህ ያልተገረዘው የሕግን ሥርዓት ከጠበቀ አለመገረዙ እንደ መገረዝ ሆኖ አይቆጠርለትምን? ከፍጥረቱ ያልተገረዘው፥ ሕግንም የሚጠብቀው፥ የሕግ መጽሐፍና መገረዝ እያለህ ሕግን በምትተላለፈው በአንተ ላይ ይፈርድብሃል። በስም አይሁዳዊ ሆኖ የሚታይ አይሁዳዊ አይደለምና፤ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም መገረዝ አይደለምና፤ ነገር ግን በስውር አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ ነው፤ መገረዝም በመንፈስ የሆነ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በፊደል አይደለም፤ ምስጋናውም ከእግዚአብሔር ነው እንጂ ከሰው አይደለም።