የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ራእይ 18:1-24

ራእይ 18:1-24 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከዚህ በኋላ ታላቅ ስልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ ከክብሩም የተነሣ ምድር በራች። በብርቱም ድምፅ “ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች! ወደቀች! የአጋንንትም ማደሪያ ሆነች፤ የርኵሳንም መናፍስት ሁሉ መጠጊያ የርኵሳንና የተጠሉም ወፎች ሁሉ መጠጊያ ሆነች፤ አሕዛብ ሁሉ ከዝሙትዋ ቍጣ ወይን ጠጅ የተነሣ ወድቀዋልና፤ የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ፤ የምድርም ነጋዴዎች ከቅምጥልነትዋ ኀይል የተነሣ ባለጠጋዎች ሆኑ፤” ብሎ ጮኸ። ከሰማይም ሌላ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ “ሕዝቤ ሆይ! በኀጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ፤ ኀጢአትዋ እስከ ሰማይ ድረስ ደርሶአልና፤ እግዚአብሔርም ዐመፃዋን አሰበ። እርስዋ እንደ ሰጠች መጠን ብድራት መልሱላት፤ እንደ ሥራዋም ሁለት እጥፍ ደርቡባት፤ በቀላቀለችው ጽዋ ሁለት እጥፍ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት፤ ራስዋን እንደ አከበረችና እንደ ተቀማጠለች ልክ ሥቃይና ሐዘን ስጡአት። በልብዋ ‘ንግሥት ሆኜ እቀመጣለሁ፤ ባልቴትም አልሆንም፤ ሐዘንም ከቶ አላይም፤’ ስላለች፥ ስለዚህ በአንድ ቀን ሞትና ሐዘን ራብም የሆኑ መቅሰፍቶችዋ ይመጣሉ፤ በእሳትም ትቃጠላለች፤ የሚፈርድባት እግዚአብሔር ብርቱ ነውና።” ከእርስዋም ጋር የሴሰኑና የተቀማጠሉ የምድር ነገሥታት የመቃጠልዋን ጢስ ሲያዩ ስለ እርስዋ እየጮሁ እያሉ ያለቅሳሉ፤ ሥቃይዋንም ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ቆመው “አንቺ ታላቂቱ ከተማ! ብርቱይቱ ከተማ ባቢሎን! ወዮልሽ! ወዮልሽ! በአንድ ሰዓት ፍርድሽ ደርሶአልና፤” እያሉ ይናገራሉ። የመርከባቸውንም ጭነት ከእንግዲህ ወዲህ የሚገዛ የለምና የምድር ነጋዴዎች ያለቅሱላታል፤ ያዝኑላትማል፤ ጭነትም ወርቅና ብር፥ የከበረም ድንጋይ ዕንቁም፥ ቀጭንም ተልባ እግር፥ ቀይም ሐር፥ ሐምራዊም ልብስ፥ የሚሸትም እንጨት ሁሉ፥ ከዝሆን ጥርስም የተሠራ ዕቃ ሁሉ፥ እጅግም ከከበረ እንጨት፥ ከናስም ከብረትም ከዕብነ በረድም የተሠራ ዕቃ ሁሉ፥ ቀረፋም፥ ቅመምም፥ የሚቃጠልም ሽቱ፥ ቅባትም፥ ዕጣንም፥ የወይን ጠጅም፥ ዘይትም፥ የተሰለቀ ዱቄትም፥ ስንዴም፥ ከብትም፥ በግም፥ ፈረስም፥ ሰረገላም፥ ባሪያዎችም፥ የሰዎችም ነፍሳት ነው። “ነፍስሽም የጎመጀችው ፍሬ ከአንቺ ዘንድ አልፎአል፤ የሚቀማጠልና የሚያጌጥም ነገር ሁሉ ጠፍቶብሻል፤ ሰዎችም ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ አያገኙአቸውም።” እነዚህን የነገዱ በእርስዋም ባለ ጠጋዎች የሆኑት እያለቀሱና እያዘኑ “በቀጭን ተልባ እግርና በቀይ ሐምራዊም ልብስ ለተጐናጸፈች በወርቅና በከበረ ድንጋይም በዕንቁም ለተሸለመች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! ይህን የሚያህል ታላቅ ባለ ጠግነት በአንድ ሰዓት ጠፍቶአልና፤” እያሉ ስቃይዋን ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ይቆማሉ። የመርከብም መሪ ሁሉ በመርከብም ወደ ማናቸውም ስፍራ የሚሄድ ሁሉ መርከበኞችም ከባሕርም የሚጠቀሙ ሁሉ በሩቅ ቆሙ፤ የመቃጠልዋንም ጢስ ባዩ ጊዜ “ታላቂቱን ከተማ የምትመስላት ምን ከተማ ነበረች?” እያሉ ጮኹ። በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነስንሰው እያለቀሱና እያዘኑ “በባሕር መርከቦች ያሉአቸውን ሁሉ ከባለ ጠግነትዋ የተነሣ ባለ ጠጋዎች ላደረገች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! በአንድ ሰዓት ጠፍታለችና፤” እያሉ ጮኹ። “ሰማይ ሆይ! ቅዱሳን ሐዋርያት ነቢያትም ሆይ! በእርስዋ ላይ ደስ ይበላችሁ፤ እግዚአብሔር ፈርዶላችኋልና።” አንድም ብርቱ መልአክ ትልቅን ወፍጮ የሚመስልን ድንጋይ አንሥቶ እንዲህ ሲል ወደ ባሕር ወረወረው “ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን እንዲህ ተገፍታ ትወድቃለች፤ ከእንግዲህም ወዲህ ከቶ አትገኝም። በገና የሚመቱና የሚዘምሩም ድምፅ እንቢልታንና መለከትንም የሚነፉ ድምፅ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፤ የእጅ ጥበብም ሁሉ አንድ ብልሃተኛ እንኳ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይገኝም፤ የወፍጮ ድምጽም ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፤ የመብራትም ብርሃን ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይበራም፤ የሙሽራና የሙሽራይቱም ድምጽ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፤ ነጋዴዎችሽ የምድር መኳንንት ነበሩና፤ በአስማትሽም አሕዛብ ሁሉ ስተዋልና።” በእርስዋም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን ደም በምድርም የታረዱ ሁሉ ደም ተገኘባት።

ራእይ 18:1-24 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዚህ በኋላ ታላቅ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ ከክብሩም ነጸብራቅ የተነሣ ምድር በራች፤ እርሱም በብርቱ ድምፅ እንዲህ ብሎ ጮኸ፤ “ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች! ወደቀች! የአጋንንት መኖሪያ፣ የርኩሳን መናፍስት ሁሉ መጠጊያ፣ የርኩስና የአስጸያፊ ወፎች ሁሉ መጠለያ ሆነች። ሕዝቦች ሁሉ የዝሙቷን ቍጣ ወይን ጠጅ ጠጥተዋልና፤ የምድር ነገሥታት ከእርሷ ጋር አመንዝረዋል፤ የምድርም ነጋዴዎች ከብዙ ምቾቷ ኀይል የተነሣ በልጽገዋል።” ከዚያም ከሰማይ ሌላ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ “ሕዝቤ ሆይ፤ በኀጢአቷ እንዳትተባበሩ፤ ከመቅሠፍቷም እንዳትካፈሉ፤ ከእርሷ ውጡ፤ ኀጢአቷ እስከ ሰማይ ድረስ ተከምሯልና፤ እግዚአብሔርም ዐመፃዋን አስታውሷል። በሰጠችው መጠን ብድራቷን መልሱላት፤ ለሠራችው ሁሉ ዕጥፍ ክፈሏት፤ በቀላቀለችውም ጽዋ ዕጥፍ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት። ለራሷ ክብርና ምቾት የሰጠችውን ያህል፣ ሥቃይና ሐዘን ስጧት፤ በልቧም እንዲህ እያለች ትመካለች፤ ‘እንደ ንግሥት ተቀምጬአለሁ፤ መበለትም አይደለሁም፤ ከቶም አላዝንም፤’ ስለዚህ መቅሠፍቶቿ በአንድ ቀን ይመጡባታል፤ ሞት፣ ሐዘንና ራብ ይሆኑባታል፤ የሚፈርድባት ጌታ እግዚአብሔር ብርቱ ስለሆነ፣ በእሳት ትቃጠላለች። “ከእርሷ ጋር ያመነዘሩና በምቾት የኖሩ የምድር ነገሥታት፣ እርሷ ስትቃጠል የሚወጣውን ጢስ ሲያዩ ስለ እርሷ ያለቅሳሉ፤ ያዝናሉም። ሥቃይዋንም በመፍራት በሩቅ ቆመው እንዲህ ይላሉ፤ “ ‘አንቺ ታላቂቱ ከተማ ወዮልሽ! ወዮልሽ! አንቺ ባቢሎን ብርቱዪቱ ከተማ፣ ፍርድሽ በአንድ ሰዓት ውስጥ መጥቷል።’ “ጭነታቸውን ከእንግዲህ የሚገዛ ስለሌለ፣ የምድር ነጋዴዎችም ስለ እርሷ ያለቅሳሉ፤ ያዝናሉ፤ ጭነቱም፦ ወርቅ፣ ብር፣ የከበረ ድንጋይ፣ ዕንቍ፣ ከተልባ እግር የተሠራ ቀጭን ልብስ፣ ሐምራዊ ልብስ፣ ሐር ልብስ፣ ቀይ ልብስ፣ መልካም ሽታ ያለው ዕንጨት ሁሉ፣ ከዝሆን ጥርስ፣ ከውድ ዕንጨት፣ ከናስ፣ ከብረትና ከእብነ በረድ የተሠራ ዕቃ ሁሉ፣ ቀረፋ፣ ቅመም፣ ከርቤ፣ ቅባት፣ ዕጣን፣ የወይን ጠጅ፣ የወይራ ዘይት፣ የተሰለቀ ዱቄት፣ ስንዴ፣ ከብቶች፣ በጎች፣ ፈረሶች፣ ሠረገሎች፣ እንዲሁም ባሮችና የሰዎች ነፍሶች ነው። “እነርሱም፣ ‘የተመኘሽው ፍሬ ከአንቺ ርቋል፤ ብልጽግናሽና ክብርሽ ሁሉ ጠፍቷል፤ ዳግመኛም ተመልሶ አይመጣም’ ይላሉ። እነዚህን ነገሮች በመሸጥ በእርሷ የበለጸጉ ነጋዴዎች ሥቃይዋን ፈርተው በሩቅ ይቆማሉ፤ እነርሱም ያለቅሳሉ፤ ያዝናሉም፤ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንዲህ ይላሉ፤ “ ‘ቀጭን የተልባ እግር፣ ሐምራዊና ቀይ ልብስ የለበሰች፣ በወርቅ፣ በከበረ ድንጋይና በዕንቍም ያጌጠች፣ ታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! ያ ሁሉ ሀብት በአንድ ሰዓት ውስጥ ጠፋ።’ “የመርከብ አዛዦች ሁሉ፣ በመርከብ የሚጓዙ መንገደኞች ሁሉ፣ የመርከብ ሠራተኞችና ኑሯቸውን በባሕር ላይ የመሠረቱ ሁሉ በሩቅ ይቆማሉ። እርሷ ስትቃጠል የሚወጣውን ጢስ ሲያዩ፣ ‘እንደዚህች ያለ ታላቅ ከተማ ከቶ የት አለ?’ እያሉ ይጮኻሉ። በራሳቸውም ላይ አቧራ ነስንሰው እያለቀሱና እያዘኑ እንዲህ ብለው ጮኹ፤ “ ‘በባሕር ላይ መርከቦች ያላቸው ሁሉ፣ በእርሷም ሀብት የበለጸጉ፣ ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! በአንድ ሰዓት ውስጥ ጠፍታለች!’ “ሰማይ ሆይ፤ በእርሷ ላይ ሐሤት አድርግ! ቅዱሳን፣ ሐዋርያትና ነቢያትም ሐሤት አድርጉ! በእናንተ ላይ ባደረሰችው ነገር እግዚአብሔር ፈርዶባታልና።” ከዚያም አንድ ብርቱ መልአክ፣ ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ የሚመስል ድንጋይ አንሥቶ ወደ ባሕር ወረወረው፤ እንዲህም አለ፤ “ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን፣ እንዲህ ባለ ኀይል ትወረወራለች፤ ተመልሳም አትገኝም። የበገና ደርዳሪዎችና የሙዚቀኞች ድምፅ፣ የዋሽንትና የመለከት ነፊዎች ድምፅ፣ ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ አይሰማም፤ የእጅ ጥበብ ባለሙያ፣ ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ አይገኝም፤ የወፍጮ ድምፅም፣ ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ አይሰማም። የመብራት ብርሃን፣ ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ አይበራም፤ የሙሽራውና የሙሽራዪቱ ድምፅ፣ ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ አይሰማም፤ ነጋዴዎችሽ የዓለም ታላላቅ ሰዎች ነበሩ፤ በአስማትሽም ሕዝቦች ሁሉ ስተዋል። በእርሷም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን፣ በምድርም የተገደሉት ሁሉ ደም ተገኘ።”

ራእይ 18:1-24 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ከዚህ በኋላ ታላቅ ስልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፥ ከክብሩም የተነሣ ምድር በራች። በብርቱም ድምፅ፦ ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች፥ ወደቀች፥ የአጋንንትም ማደሪያ ሆነች፥ የርኵሳንም መናፍስት ሁሉ መጠጊያ የርኵሳንና የተጠሉም ወፎች ሁሉ መጠጊያ ሆነች፤ አሕዛብ ሁሉ ከዝሙትዋ ቍጣ ወይን ጠጅ የተነሳ ወድቀዋልና፥ የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ የምድርም ነጋዴዎች ከቅምጥልነትዋ ኃይል የተነሳ ባለ ጠጋዎች ሆኑ ብሎ ጮኸ። ከሰማይም ሌላ ድምፅ ሰማሁ እንዲህ ሲል፦ ሕዝቤ ሆይ፥ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ፤ ኃጢአትዋ እስከ ሰማይ ድረስ ደርሶአልና፥ እግዚአብሔርም ዓመፃዋን አሰበ። እርስዋ እንደ ሰጠች መጠን ብድራት መልሱላት፥ እንደ ሥራዋም ሁለት እጥፍ ደርቡባት፤ በቀላቀለችው ጽዋ ሁለት እጥፍ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት፤ ራስዋን እንደ አከበረችና እንደ ተቀማጠለች ልክ ሥቃይና ኀዘን ስጡአት። በልብዋ፦ ንግሥት ሆኜ እቀመጣለሁ ባልቴትም አልሆንም ኀዘንም ከቶ አላይም ስላለች፥ ስለዚህ በአንድ ቀን ሞትና ኀዘን ራብም የሆኑ መቅሰፍቶችዋ ይመጣሉ፥ በእሳትም ትቃጠላለች፤ የሚፈርድባት እግዚአብሔር ብርቱ ነውና። ከእርስዋም ጋር የሴሰኑና የተቀማጠሉ የምድር ነገሥታት የመቃጠልዋን ጢስ ሲያዩ ስለ እርስዋ ዋይ ዋይ እያሉ ያለቅሳሉ፤ ሥቃይዋንም ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ቆመው፦ አንቺ ታላቂቱ ከተማ፥ ብርቱይቱ ከተማ ባቢሎን፥ ወዮልሽ፥ ወዮልሽ፥ በአንድ ሰዓት ፍርድሽ ደርሶአልና እያሉ ይናገራሉ። የመርከባቸውንም ጭነት ከእንግዲህ ወዲህ የሚገዛ የለምና የምድር ነጋዴዎች ያለቅሱላታል ያዝኑላትማል፤ ጭነትም ወርቅና ብር የከበረም ድንጋይ ዕንቁም፥ ቀጭንም ተልባ እግር ቀይም ሐርም ሐምራዊም ልብስ የሚሸትም እንጨት ሁሉ፥ ከዝሆን ጥርስም የተሰራ ዕቃ ሁሉ፥ እጅግም ከከበረ እንጨት ከናስም ከብረትም ከዕብነ በረድም የተሰራ ዕቃ ሁሉ፥ ቀረፋም ቅመምም የሚቃጠልም ሽቱ ቅባትም ዕጣንም የወይን ጠጅም ዘይትም የተሰለቀ ዱቄትም ስንዴም ከብትም በግም ፈረስም ሰረገላም ባሪያዎችም የሰዎችም ነፍሳት ነው። ነፍስሽም የጎመጀችው ፍሬ ከአንቺ ዘንድ አልፎአል፥ የሚቀማጠልና የሚያጌጥም ነገር ሁሉ ጠፍቶብሻል፥ ሰዎችም ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ አያገኙአቸውም። እነዚህን የነገዱ በእርስዋም ባለ ጠጋዎች የሆኑት እያለቀሱና እያዘኑ፦ በቀጭን ተልባ እግርና በቀይ ሐምራዊም ልብስ ለተጐናጸፈች በወርቅና በከበረ ድንጋይም በዕንቁም ለተሸለመች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት፥ ወዮላት፥ ይህን የሚያህል ታላቅ ባለ ጠግነት በአንድ ሰዓት ጠፍቶአልና እያሉ ስቃይዋን ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ይቆማሉ። የመርከብም መሪ ሁሉ በመርከብም ወደ ማናቸውም ስፍራ የሚሄድ ሁሉ መርከበኞችም ከባሕርም የሚጠቀሙ ሁሉ በሩቅ ቆሙ፥ የመቃጠልዋንም ጢስ ባዩ ጊዜ፦ ታላቂቱን ከተማ የምትመስላት ምን ከተማ ነበረች? እያሉ ጮኹ። በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነስንሰው እያለቀሱና እያዘኑ፦ በባሕር መርከቦች ያሉአቸውን ሁሉ ከባለ ጠግነትዋ የተነሣ ባለ ጠጋዎች ላደረገች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት፥ ወዮላት፥ በአንድ ሰዓት ጠፍታለችና እያሉ ጮኹ። ሰማይ ሆይ፥ ቅዱሳን ሐዋርያት ነቢያትም ሆይ፥ በእርስዋ ላይ ደስ ይበላችሁ፥ እግዚአብሔር ፈርዶላችኋልና። አንድም ብርቱ መልአክ ትልቅን ወፍጮ የሚመስልን ድንጋይ አንስቶ ወደ ባሕር ወረወረው እንዲህ ሲል፦ ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን እንዲህ ተገፍታ ትወድቃለች ከእንግዲህም ወዲህ ከቶ አትገኝም። በገና የሚመቱና የሚዘምሩም ድምፅ እንቢልታንና መለከትንም የሚነፉ ድምፅ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፥ የእጅ ጥበብም ሁሉ አንድ ብልሃተኛ እንኳ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይገኝም፥ የወፍጮ ድምጽም ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፥ የመብራትም ብርሃን ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይበራም፥ የሙሽራና የሙሽራይቱም ድምጽ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፤ ነጋዴዎችሽ የምድር መኳንንት ነበሩና፥ በአስማትሽም አሕዛብ ሁሉ ስተዋልና። በእርስዋም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን ደም በምድርም የታረዱ ሁሉ ደም ተገኘባት።

ራእይ 18:1-24 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከዚህ በኋላ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ ከክብሩ ነጸብራቅ የተነሣ ምድር በራች፤ ከፍ ባለ ድምፅም እንዲህ ሲል ጮኸ፤ “ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች! ወደቀች! የአጋንንት መኖሪያ ሆነች! የርኩሳን መናፍስት ማደሪያ ሆነች! የሚያጸይፉና የሚያስጠሉ ወፎች መጠለያ ሆነች! የሚያሰክረውን የአመንዝራነትዋን ወይን ጠጅ ለሕዝቦች ሁሉ አጠጥታለች፤ የምድር ነገሥታት ከእርስዋ ጋር አመንዝረዋል፤ የምድር ነጋዴዎችም ከብዙ ምቾትዋ የተነሣ ሀብታሞች ሆነዋል።” ሌላ ድምፅም ከሰማይ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ “ሕዝቤ ሆይ! በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ፤ የመቅሠፍትዋም ተካፋዮች እንዳትሆኑ፤ ከእርስዋ ውጡ! የኃጢአትዋ ክምር እስከ ሰማይ ደርሶአል፤ እግዚአብሔር በደሎችዋን አስታውሶአል፤ በሰጠችው መጠን ስጥዋት፤ ባደረገችውም ሥራ እጥፍ ክፈልዋት፤ እርስዋ ልዩ ልዩ መጠጦችን በቀላቀለችበት ጽዋ ውስጥ እጥፍ ኀይለኛ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት፤ እርስዋ ለራስዋ ክብርንና ምቾትን የሰጠችውን ያኽል ሥቃይና ሐዘን ስጡአት፤ እርስዋ በልብዋ ‘እንደ ንግሥት ተቀምጬአለሁ፤ መበለትም አይደለሁም፤ ሐዘንም ከቶ አይደርስብኝም’ በማለት ትመካለች። ስለዚህ መቅሠፍቶችዋ ሁሉ በአንድ ቀን ይደርሱባታል፤ ሞትና ሐዘን ራብም ይደርሱባታል፤ በእሳትም ትቃጠላለች፤ በእርስዋ ላይ የሚፈርድባት ጌታ አምላክ ብርቱ ነው።” ከእርስዋ ጋር ያመነዘሩና በምቾት የኖሩ የምድር ነገሥታት እርስዋ ስትቃጠል የሚወጣውን ጢስ ሲያዩ ስለ እርስዋ እየጮኹ ያለቅሳሉ፤ ሥቃይዋንም በመፍራት በሩቅ ቆመው “አንቺ ታላቂቱ ከተማ፥ አንቺ ብርቱይቱ ከተማ ባቢሎን ሆይ! ፍርድሽ በአንድ ሰዓት ውስጥ ስለ መጣ፥ ወዮልሽ! ወዮልሽ!” ይላሉ። የመርከባቸውን ጭነት ከእንግዲህ የሚገዛ ስለሌለ የምድር ነጋዴዎችም ያለቅሱላታል፤ ያዝኑላታልም፤ በመርከባቸው የተጫነውም ወርቅ፥ ብር፥ የከበረ ድንጋይ፥ ዕንቊ፥ ቀጭን ልብስ፥ ሐምራዊ ልብስ፥ ሐር ልብስ፥ ቀይ ልብስና መልካም መዓዛ ያለው እንጨት ሁሉ፥ ከዝኆን ጥርስ፥ ውድ ከሆነ እንጨት፥ ከነሐስ፥ ከብረትና ከእብነበረድ የተሠራ ዕቃ ሁሉ፥ ቀረፋ፥ ቅመም፥ የሚሸት እንጨት፥ ከርቤ፥ ዕጣን፥ ወይን ጠጅ፥ የወይራ ዘይት፥ ዱቄት፥ ስንዴ፥ ከብቶች፥ በጎች፥ ፈረሶች፥ ሠረገላዎች፥ ባርያዎችና ሌሎችም ሰዎች ናቸው። ነጋዴዎቹም “አንቺ የተመኘሻቸው መልካም ነገሮች ሁሉ ከአንቺ ርቀው ሄደዋል፤ ሀብትሽም ጌጣ ጌጥሽም ሁሉ ጠፍቶአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ እነዚህን ሁሉ ከቶ አታገኚአቸውም!” ይሉአታል። እነዚህን ነገሮች ሁሉ እየገዙ ሀብታሞች የሆኑ ነጋዴዎች ሥቃይዋን በመፍራት በሩቅ ይቆማሉ፤ እያለቀሱና እያዘኑም፥ “ቀጭን ልብስና ሐምራዊ ልብስ ቀይ ልብስም ትለብስ የነበረች፥ በወርቅና በከበረ ድንጋይ በዕንቊም ታሸበርቅ የነበረች፤ ታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! ያን ያኽል ሀብት በአንድ ሰዓት ጠፋ!” ይላሉ። የመርከብ አዛዦች ሁሉ፥ በመርከብ የሚጓዙ ሰዎች ሁሉ፥ በመርከብ ላይ የሚሠሩ ሁሉ፥ በባሕር ላይ የሚነግዱ ሁሉ በሩቅ ይቆማሉ፤ እርስዋ ስትቃጠል የሚወጣውን ጢስ ባዩ ጊዜ “ይህችን ታላቅ ከተማ የሚመስል ከቶ ሌላ ከተማ ነበረን?” እያሉ ጮኹ። በራሳቸው ላይ አቧራ ነሰነሱ፤ እያለቀሱና እያዘኑም እንዲህ እያሉ ይጮኻሉ፤ “በባሕር ላይ መርከቦች ያላቸው ሁሉ በእርስዋ ሀብት ሀብታሞች የሆኑ፥ ያቺ ታላቅ ከተማ በአንድ ሰዓት ውስጥ ስለ ወደመች ወዮላት! ወዮላት!” ሰማይ ሆይ! በእርስዋ ደስ ይበልህ! እግዚአብሔር ስለ እናንተ በእርስዋ ላይ ስለ ፈረደባት እናንተ ቅዱሳንና ሐዋርያት ነቢያትም ደስ ይበላችሁ! ከዚህ በኋላ አንድ ብርቱ መልአክ ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ የሚያኽል አንድ ድንጋይ አንሥቶ እንዲህ ሲል ወደ ባሕር ወረወረው፤ “ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን እንዲህ በኀይል ተገፍታ ትወድቃለች፤ ከእንግዲህ ወዲህም ከቶ አትገኝም፤ የበገና ደርዳሪዎችና የሙዚቀኞች ድምፅ፥ የዋሽንት ነፊዎችና የእምቢልታ ነፊዎች ድምፅ፥ ዳግመኛ በአንቺ አይሰማም፤ ማንኛውንም ዐይነት የእጅ ጥበብ የሚሠራ ብልኀተኛ ሰው ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ አይገኝም፤ የወፍጮም ድምፅ ከእንግዲህ በአንቺ አይሰማም። የመብራት ብርሃን ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ አያበራም፤ የሙሽራውና የሙሽራይቱ ድምፅ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ አይሰማም፤ ነጋዴዎችሽ የዓለም ታላላቅ ሰዎች ነበሩ፤ በአስማትሽ ሕዝቦችን ሁሉ አሳስተሻል። “በእርስዋ ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን፥ በምድር ላይ የተገደሉ ሰዎች ሁሉ ደም ተገኝቶአል።”

ራእይ 18:1-24 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከዚህ በኋላ ታላቅ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ ከክብሩም የተነሣ ምድር በራች። በብርቱም ድምፅ “ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች! ወደቀች! የአጋንንትም ማደሪያ ሆነች፤ የርኩሳንም መናፍስት ሁሉ መጠጊያ የርኩሳንና የተጠሉም ወፎች ሁሉ መጠጊያ ሆነች፤ አሕዛብ ሁሉ ከዝሙትዋ ቁጣ ወይን ጠጅ ጠጥተዋልና፤ የምድርም ነገሥታት ከእርሷ ጋር ሴስነዋልና፤ የምድርም ነጋዴዎች ከቅምጥልነትዋ ኃይል የተነሣ ሀብታሞች ሆነዋልና፤” ብሎ ጮኸ። ከሰማይም ሌላ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ “ሕዝቤ ሆይ! በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርሷ ዘንድ ውጡ፤ ኃጢአትዋ እስከ ሰማይ ድረስ ደርሶአልና፤ እግዚአብሔርም ዐመፃዋን አስታወሰ። እርሷ በሰጠችው መጠን መልሱላት፤ እንደ ሥራዋም ሁለት እጥፍ ደርቡባት፤ በቀላቀለችው ጽዋ ሁለት እጥፍ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት፤ ራስዋን በአከበረችበትና በተቀማጠለችበት ልክ ሥቃይንና ኀዘንን ስጡአት። በልብዋ ‘ንግሥት ሆኜ እቀመጣለሁ፤ መበለትም አልሆንም፤ ኀዘንም ከቶ አላይም፤’ ስላለች፥ ስለዚህም ሞትና ኀዘን፥ ራብም የሆኑት መቅሰፍቶችዋ በአንድ ቀን ይመጣሉ፤ በእሳትም ትቃጠላለች፤ የሚፈርድባት ጌታ እግዚአብሔር ብርቱ ነውና።” ከእርሷም ጋር የሴሰኑና የተቀማጠሉ የምድር ነገሥታት የመቃጠልዋን ጢስ ሲያዩ ስለ እርሷ እየጮሁ ያለቅሳሉ፤ ሥቃይዋንም ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ቆመው “አንቺ ታላቂቱ ከተማ! ብርቱይቱ ከተማ ባቢሎን! ወዮልሽ! ወዮልሽ! በአንድ ሰዓት ውስጥ ፍርድሽ ይፈጸማልና፤” እያሉ ይናገራሉ። የመርከባቸውንም ጭነት ከእንግዲህ ወዲህ የሚገዛ የለምና የምድር ነጋዴዎች ያለቅሱላታል፤ ያዝኑላትማል፤ ጭነቱም ወርቅና ብር፥ የከበረም ድንጋይ ዕንቁም፥ ቀጭንም ተልባ እግር፥ ቀይም ሐር፥ ሐምራዊም ልብስ፥ መልካም መዐዛ ያለውም እንጨት ሁሉ፥ ከዝሆን ጥርስም የተሠራ ዕቃ ሁሉ፥ እጅግም ከከበረ እንጨት፥ ከነሐስም ከብረትም ከዕብነ በረድም የተሠራ ዕቃ ሁሉ፥ ቀረፋም፥ ቅመምም፥ የሚቃጠልም ሽቱ፥ ቅባትም፥ ዕጣንም፥ የወይን ጠጅም፥ የወይራ ዘይትም፥ ምርጥ ዱቄትም፥ ስንዴም፥ ከብትም፥ በግም፥ ፈረስም፥ ሠረገላም፥ ባርያዎችም፥ የሰዎችም ነፍሳት ነው። “ነፍስሽም የጎመጀችለት ፍሬ ከአንቺ ተለይቶ ሄዶአል፤ የድሎትና የጌጥ ነገር ሁሉ ጠፍቶብሻል፤ ከእንግዲህ ወዲህም ከቶ አይገኙም።” እነዚህን የነገዱ በእርሷም ሀብታም የሆኑት እያለቀሱና እያዘኑ “በቀጭን ተልባ እግርና በቀይ ሐምራዊም ልብስ ለተጐናጸፈች በወርቅና በከበረ ድንጋይም በዕንቁም ለተሸለመች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! ይላሉ። ይህን የሚያህል ታላቅ ሀብት በአንድ ሰዓት ጠፍቶአልና፤” የመርከብም መሪ ሁሉ በመርከብም ወደ ማናቸውም ስፍራ የሚሄድ ሁሉ መርከበኞችም ከባሕርም የሚጠቀሙ ሁሉ በሩቅ ቆሙ፤ የመቃጠልዋንም ጢስ ባዩ ጊዜ “ታላቂቱን ከተማ የምትመስል ሌላ ከተማ ነበረችን?” እያሉ ጮኹ። በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነስንሰው እያለቀሱና እያዘኑ “በባሕር መርከቦች ያሉአቸውን ሁሉ ከሀብቷ የተነሣ ሀብታም ላደረገች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! በአንድ ሰዓት ጠፍታለችና፤” እያሉ ጮኹ። “ሰማይ ሆይ! ቅዱሳን፥ ሐዋርያትና ነቢያት ሆይ! ስለተፈረደባት በእርሷ ላይ ደስ ይበላችሁ፤ እግዚአብሔር ፈርዶላችኋልና።” አንድም ብርቱ መልአክ ትልቅን ወፍጮ የሚመስልን ድንጋይ አንሥቶ እንዲህ ሲል ወደ ባሕር ወረወረው “ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን እንዲህ ተገፍታ ትወድቃለች፤ ከእንግዲህም ወዲህ ከቶ አትገኝም። ከእንግዲህ ወዲህ በገና የሚመቱና የሚዘምሩ ሰዎች ድምፅ፥ እንቢልታንና መለከትንም የሚነፉ ሰዎች ድምፅ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፤ የማንኛውም ዕደ ጥበብ ብልሃተኛ ሰው ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይገኝም፤ የወፍጮ ድምጽም ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፤ የመብራትም ብርሃን ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይበራም፤ የሙሽራውና የሙሽራይቱም ድምጽ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፤ ነጋዴዎችሽ የምድር መኳንንት ነበሩና፤ በአስማትሽም አሕዛብ ሁሉ ስተዋልና።” በእርሷም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን ደም፥ በምድርም የታረዱ ሁሉ ደም ተገኘባት።