ከዚህ በኋላ ታላቅ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ ከክብሩም ነጸብራቅ የተነሣ ምድር በራች፤ እርሱም በብርቱ ድምፅ እንዲህ ብሎ ጮኸ፤ “ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች! ወደቀች! የአጋንንት መኖሪያ፣ የርኩሳን መናፍስት ሁሉ መጠጊያ፣ የርኩስና የአስጸያፊ ወፎች ሁሉ መጠለያ ሆነች። ሕዝቦች ሁሉ የዝሙቷን ቍጣ ወይን ጠጅ ጠጥተዋልና፤ የምድር ነገሥታት ከእርሷ ጋር አመንዝረዋል፤ የምድርም ነጋዴዎች ከብዙ ምቾቷ ኀይል የተነሣ በልጽገዋል።” ከዚያም ከሰማይ ሌላ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ “ሕዝቤ ሆይ፤ በኀጢአቷ እንዳትተባበሩ፤ ከመቅሠፍቷም እንዳትካፈሉ፤ ከእርሷ ውጡ፤ ኀጢአቷ እስከ ሰማይ ድረስ ተከምሯልና፤ እግዚአብሔርም ዐመፃዋን አስታውሷል። በሰጠችው መጠን ብድራቷን መልሱላት፤ ለሠራችው ሁሉ ዕጥፍ ክፈሏት፤ በቀላቀለችውም ጽዋ ዕጥፍ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት። ለራሷ ክብርና ምቾት የሰጠችውን ያህል፣ ሥቃይና ሐዘን ስጧት፤ በልቧም እንዲህ እያለች ትመካለች፤ ‘እንደ ንግሥት ተቀምጬአለሁ፤ መበለትም አይደለሁም፤ ከቶም አላዝንም፤’ ስለዚህ መቅሠፍቶቿ በአንድ ቀን ይመጡባታል፤ ሞት፣ ሐዘንና ራብ ይሆኑባታል፤ የሚፈርድባት ጌታ እግዚአብሔር ብርቱ ስለሆነ፣ በእሳት ትቃጠላለች። “ከእርሷ ጋር ያመነዘሩና በምቾት የኖሩ የምድር ነገሥታት፣ እርሷ ስትቃጠል የሚወጣውን ጢስ ሲያዩ ስለ እርሷ ያለቅሳሉ፤ ያዝናሉም። ሥቃይዋንም በመፍራት በሩቅ ቆመው እንዲህ ይላሉ፤ “ ‘አንቺ ታላቂቱ ከተማ ወዮልሽ! ወዮልሽ! አንቺ ባቢሎን ብርቱዪቱ ከተማ፣ ፍርድሽ በአንድ ሰዓት ውስጥ መጥቷል።’ “ጭነታቸውን ከእንግዲህ የሚገዛ ስለሌለ፣ የምድር ነጋዴዎችም ስለ እርሷ ያለቅሳሉ፤ ያዝናሉ፤ ጭነቱም፦ ወርቅ፣ ብር፣ የከበረ ድንጋይ፣ ዕንቍ፣ ከተልባ እግር የተሠራ ቀጭን ልብስ፣ ሐምራዊ ልብስ፣ ሐር ልብስ፣ ቀይ ልብስ፣ መልካም ሽታ ያለው ዕንጨት ሁሉ፣ ከዝሆን ጥርስ፣ ከውድ ዕንጨት፣ ከናስ፣ ከብረትና ከእብነ በረድ የተሠራ ዕቃ ሁሉ፣ ቀረፋ፣ ቅመም፣ ከርቤ፣ ቅባት፣ ዕጣን፣ የወይን ጠጅ፣ የወይራ ዘይት፣ የተሰለቀ ዱቄት፣ ስንዴ፣ ከብቶች፣ በጎች፣ ፈረሶች፣ ሠረገሎች፣ እንዲሁም ባሮችና የሰዎች ነፍሶች ነው። “እነርሱም፣ ‘የተመኘሽው ፍሬ ከአንቺ ርቋል፤ ብልጽግናሽና ክብርሽ ሁሉ ጠፍቷል፤ ዳግመኛም ተመልሶ አይመጣም’ ይላሉ። እነዚህን ነገሮች በመሸጥ በእርሷ የበለጸጉ ነጋዴዎች ሥቃይዋን ፈርተው በሩቅ ይቆማሉ፤ እነርሱም ያለቅሳሉ፤ ያዝናሉም፤ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንዲህ ይላሉ፤ “ ‘ቀጭን የተልባ እግር፣ ሐምራዊና ቀይ ልብስ የለበሰች፣ በወርቅ፣ በከበረ ድንጋይና በዕንቍም ያጌጠች፣ ታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! ያ ሁሉ ሀብት በአንድ ሰዓት ውስጥ ጠፋ።’ “የመርከብ አዛዦች ሁሉ፣ በመርከብ የሚጓዙ መንገደኞች ሁሉ፣ የመርከብ ሠራተኞችና ኑሯቸውን በባሕር ላይ የመሠረቱ ሁሉ በሩቅ ይቆማሉ። እርሷ ስትቃጠል የሚወጣውን ጢስ ሲያዩ፣ ‘እንደዚህች ያለ ታላቅ ከተማ ከቶ የት አለ?’ እያሉ ይጮኻሉ። በራሳቸውም ላይ አቧራ ነስንሰው እያለቀሱና እያዘኑ እንዲህ ብለው ጮኹ፤ “ ‘በባሕር ላይ መርከቦች ያላቸው ሁሉ፣ በእርሷም ሀብት የበለጸጉ፣ ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! በአንድ ሰዓት ውስጥ ጠፍታለች!’ “ሰማይ ሆይ፤ በእርሷ ላይ ሐሤት አድርግ! ቅዱሳን፣ ሐዋርያትና ነቢያትም ሐሤት አድርጉ! በእናንተ ላይ ባደረሰችው ነገር እግዚአብሔር ፈርዶባታልና።” ከዚያም አንድ ብርቱ መልአክ፣ ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ የሚመስል ድንጋይ አንሥቶ ወደ ባሕር ወረወረው፤ እንዲህም አለ፤ “ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን፣ እንዲህ ባለ ኀይል ትወረወራለች፤ ተመልሳም አትገኝም። የበገና ደርዳሪዎችና የሙዚቀኞች ድምፅ፣ የዋሽንትና የመለከት ነፊዎች ድምፅ፣ ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ አይሰማም፤ የእጅ ጥበብ ባለሙያ፣ ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ አይገኝም፤ የወፍጮ ድምፅም፣ ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ አይሰማም። የመብራት ብርሃን፣ ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ አይበራም፤ የሙሽራውና የሙሽራዪቱ ድምፅ፣ ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ አይሰማም፤ ነጋዴዎችሽ የዓለም ታላላቅ ሰዎች ነበሩ፤ በአስማትሽም ሕዝቦች ሁሉ ስተዋል። በእርሷም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን፣ በምድርም የተገደሉት ሁሉ ደም ተገኘ።”
ራእይ 18 ያንብቡ
ያዳምጡ ራእይ 18
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ራእይ 18:1-24
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos