የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ራእይ 17:1-18

ራእይ 17:1-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ሰባቱንም ጽዋዎች ከያዙ ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ “ና፤ በብዙም ውሃዎች ላይ የተቀመጠችውን የታላቂቱን ጋለሞታ ፍርድ አሳይሃለሁ፤ የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ፤ በምድርም የሚኖሩ ከዝሙትዋ ወይን ጠጅ ሰከሩ፤” ብሎ ተናገረኝ። በመንፈስም ወደ በረሓ ወሰደኝ፤ የስድብም ስሞች በሞሉበት፥ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶችም ባሉበት በቀይ አውሬ ላይ አንዲት ሴት ተቀምጣ አየሁ። ሴቲቱም በቀይና በሐምራዊ ልብስ ተጐናጽፋ በወርቅና በከበሩ ድንጋዮች በዕንቈችም ተሸልማ ነበር፤ በእጅዋም የሚያስጸይፍ ነገር የዝሙትዋም ርኵሰት የሞላባትን የወርቅ ጽዋ ያዘች፤ በግምባርዋም ምስጢር የሆነ ስም “ታላቂቱ ባቢሎን፥ የጋለሞታዎችና የምድር ርኵሰት እናት” ተብሎ ተጻፈ። ሴቲቱም በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ አየኋት። ባየኋትም ጊዜ እጅግ ታላቅ ድንቅ አደነቅሁ። መልአኩም አለኝ “የምትደነቅ ስለ ምንድር ነው? የሴቲቱን ምስጢርና የሚሸከማትን፥ ሰባት ራሶችና ዐስር ቀንዶች ያሉትን የአውሬውን ምስጢር እኔ እነግርሃለሁ። ያየኸው አውሬ አስቀድሞ ነበረ፤ አሁንም የለም፤ ከጥልቁም ይወጣ ዘንድ አለው፤ ወደ ጥፋትም ይሄዳል፤ ስሞቻቸውም ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ በሕይወት መጽሐፍ ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ አውሬው አስቀድሞ እንደነበረ አሁንም እንደሌለ፥ ነገር ግን እንዳለ ሲያዩ ያደንቃሉ። ጥበብ ያለው አእምሮ በዚህ ነው። ሰባቱ ራሶች ሴቲቱ የተቀመጠችባቸው ሰባት ተራራዎች ናቸው፤ ሰባት ነገሥታት ደግሞ ናቸው፤ አምስቱ ወድቀዋል፤ አንዱም አለ፤ የቀረውም ገና አልመጣም፤ ሲመጣም፥ ጥቂት ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል። የነበረውና የሌለውም አውሬ ራሱ ደግሞ ስምንተኛው ነው፤ ከሰባቱም አንዱ ነው፤ ወደ ጥፋትም ይሄዳል። ያየሃቸውም ዐሥሩ ቀንዶች ገና መንግሥትን ያልተቀበሉ ዐሥር ነገሥታት ናቸው፤ ዳሩ ግን ከአውሬው ጋር ለአንድ ሰዓት እንደ ነገሥታት ሥልጣንን ይቀበላሉ። እነዚህ አንድ አሳብ አላቸው፤ ኀይላቸውንና ሥልጣናቸውንም ለአውሬው ይሰጣሉ። እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ እነርሱን ድል ይነሣል፤ ከእርሱም ጋር ያሉ የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ድል ይነሣሉ።” አለኝም “ጋለሞታይቱ የተቀመጠችባቸው ያየሃቸው ውሃዎች፥ ወገኖችና ብዙ ሰዎች አሕዛብም ቋንቋዎችም ናቸው። ያየሃቸውም ዐሥር ቀንዶችና አውሬው ጋለሞታይቱን ይጣላሉ፤ ባዶዋንና ራቁትዋንም ያደርጓታል፤ ሥጋዋንም ይበላሉ፤ በእሳትም ያቃጥሉአታል። እግዚአብሔር አሳቡን እንዲያደርጉ አንድንም አሳብ እንዲያደርጉ የእግዚአብሔርም ቃል እስኪፈጸም ድረስ መንግሥታቸውን ለአውሬው እንዲሰጡ በልባቸው አገብቶአልና። ያየሃትም ሴት በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ ታላቂቱ ከተማ ናት።”

ራእይ 17:1-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ሰባቱን ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ እንዲህ አለኝ፤ “ና፤ በብዙ ውሆች ላይ የተቀመጠችውን የታላቂቱን አመንዝራ ፍርድ አሳይሃለሁ። የምድር ነገሥታት ከእርሷ ጋር አመነዘሩ፤ የምድር ነዋሪዎችም በዝሙቷ የወይን ጠጅ ሰከሩ።” ቀጥሎም መልአኩ በመንፈስ ወደ በረሓ ወሰደኝ፤ በዚያም አንዲት ሴት በስድብ ስሞች በተሞላ፣ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶች ባሉት ቀይ አውሬ ላይ ተቀምጣ አየሁ። ሴቲቱም ሐምራዊና ቀይ ልብስ ተጐናጽፋ ነበር፤ ደግሞም በወርቅ፣ በከበሩ ድንጋዮችና በዕንቈችም አጊጣ ነበር፤ በእጇም የሚያስጸይፍ ነገርና የዝሙቷ ርኩሰት የሞላበትን የወርቅ ጽዋ ይዛ ነበር። በግንባሯም ላይ እንዲህ የሚል የምስጢር ስም ተጽፎ ነበር፤ ታላቂቱ ባቢሎን፣ የአመንዝሮችና የምድር ርኩሰቶች እናት። ሴቲቱንም በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ አየኋት። ባየኋትም ጊዜ እጅግ ተደነቅሁ። ከዚያም መልአኩ እንዲህ አለኝ፤ የምትደነቀው ለምንድን ነው? የሴቲቱን፣ እርሷ የተቀመጠችበትንም፣ እንዲሁም ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶች ያሉትን የአውሬውን ምስጢር እነግርሃለሁ። ያየኸው አውሬ ቀደም ሲል ነበረ፤ አሁን ግን የለም፤ በኋላም ከጥልቁ ጕድጓድ ይወጣል፤ ወደ ጥፋቱም ይሄዳል። ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘ የምድር ነዋሪዎች አውሬው ቀድሞ የነበረ፣ አሁን ግን የሌለ፣ በኋላም የሚመጣ መሆኑን ሲያዩ ይደነቃሉ። “ይህም፣ ጥበብ ያለው አእምሮ ይጠይቃል። ሰባቱ ራሶች ሴቲቱ የምትቀመጥባቸው ሰባት ተራሮች ናቸው፤ እነርሱም ደግሞ ሰባት ነገሥታት ናቸው። አምስቱ ወድቀዋል፤ አንዱ አለ፤ ሌላውም ገና አልመጣም፤ ሲመጣ ግን ሊቈይ የሚገባው ለጥቂት ጊዜ ነው። ቀድሞ የነበረውና አሁን የሌለው አውሬ ስምንተኛው ንጉሥ ነው፤ እርሱም ከሰባቱ አንዱ ሲሆን ወደ ጥፋቱ ይሄዳል። “ያየሃቸው ዐሥሩ ቀንዶች ገና መንግሥትን ያልተቀበሉ፣ ዐሥር ነገሥታት ናቸው፤ ነገር ግን ከአውሬው ጋር ለአንድ ሰዓት እንዲነግሡ ሥልጣን ይቀበላሉ። አንድ ሐሳብም አላቸው፤ ኀይላቸውንና ሥልጣናቸውንም ለአውሬው ይሰጣሉ፤ እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉ ግን ድል ይነሣቸዋል፤ ምክንያቱም እርሱ የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ነው፤ ከእርሱ ጋር ያሉ የተጠሩት፣ የተመረጡትና የታመኑትም አብረው ድል ይነሣሉ።” መልአኩም እንዲህ አለኝ፤ “አመንዝራዪቱ ተቀምጣባቸው ያየሃቸው ውሆች፣ ወገኖች፣ ብዙ ሰዎች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች ናቸው። አውሬውና ያየሃቸው ዐሥሩ ቀንዶች አመንዝራዪቱን ይጠሏታል፤ ባዶዋንና ዕራቍቷን ያስቀሯታል። ሥጋዋን ይበላሉ፤ በእሳትም ያቃጥሏታል። የእግዚአብሔር ቃል እስኪፈጸም ድረስ ዕቅዱን እንዲፈጽሙ፣ ደግሞም በአንድ ሐሳብ እንዲስማሙና ሥልጣናቸውንም ለአውሬው እንዲሰጡ ይህን ሐሳብ በልባቸው ያኖረ እግዚአብሔር ነውና። ያየሃትም ሴት በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ ታላቂቱ ከተማ ናት።”

ራእይ 17:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ሰባቱንም ጽዋዎች ከያዙ ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ፦ ና በብዙም ውኃዎች ላይ የተቀመጠችውን የታላቂቱን ጋለሞታ ፍርድ አሳይሃለሁ፤ የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ በምድርም የሚኖሩ ከዝሙትዋ ወይን ጠጅ ሰከሩ ብሎ ተናገረኝ። በመንፈስም ወደ በረሀ ወሰደኝ፤ የስድብም ስሞች በሞሉበት፥ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶችም ባሉበት በቀይ አውሬ ላይ አንዲት ሴት ተቀምጣ አየሁ። ሴቲቱም በቀይና በሐምራዊ ልብስ ተጐናጽፋ በወርቅና በከበሩ ድንጋዮች በዕንቈችም ተሸልማ ነበር፥ በእጅዋም የሚያስጸይፍ ነገር የዝሙትዋም ርኵሰት የሞላባትን የወርቅ ጽዋ ያዘች፤ በግምባርዋም ምስጢር የሆነ ስም፦ ታላቂቱ ባቢሎን፥ የጋለሞታዎችና የምድር ርኵሰት እናት ተብሎ ተጻፈ። ሴቲቱም በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ አየኋት። ባየኋትም ጊዜ እጅግ ታላቅ ድንቅ አደነቅሁ። መልአኩም አለኝ፦ የምትደነቅ ስለ ምንድር ነው? የሴቲቱን ምስጢርና የሚሸከማትን፥ ሰባት ራሶችና አስር ቀንዶች ያሉትን የአውሬውን ምስጢር እኔ እነግርሃለሁ። ያየኸው አውሬ አስቀድሞ ነበረ፥ አሁንም የለም፥ ከጥልቁም ይወጣ ዘንድ አለው፥ ወደ ጥፋትም ይሄዳል፤ ስሞቻቸውም ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ በሕይወት መጽሐፍ ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ አውሬው አስቀድሞ እንደነበረ አሁንም እንደሌለ፥ ነገር ግን እንዳለ ሲያዩ ያደንቃሉ። ጥበብ ያለው አእምሮ በዚህ ነው። ሰባቱ ራሶች ሴቲቱ የተቀመጠችባቸው ሰባት ተራራዎች ናቸው፥ ሰባት ነገሥታት ደግሞ ናቸው፤ አምስቱ ወድቀዋል አንዱም አለ፥ የቀረውም ገና አልመጣም፤ ሲመጣም፥ ጥቂት ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል። የነበረውና የሌለውም አውሬ ራሱ ደግሞ ስምንተኛው ነው ከሰባቱም አንዱ ነው፥ ወደ ጥፋትም ይሄዳል። ያየሃቸውም አስሩ ቀንዶች ገና መንግሥትን ያልተቀበሉ አስር ነገሥታት ናቸው፥ ዳሩ ግን ከአውሬው ጋር ለአንድ ሰዓት እንደ ነገሥታት ሥልጣንን ይቀበላሉ። እነዚህ አንድ አሳብ አላቸው፥ ኃይላቸውንና ሥልጣናቸውንም ለአውሬው ይሰጣሉ። እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ እነርሱን ድል ይነሣል፥ ከእርሱም ጋር ያሉ የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ድል ይነሣሉ። አለኝም፦ ጋለሞታይቱ የተቀመጠችባቸው ያየሃቸው ውኃዎች፥ ወገኖችና ብዙ ሰዎች አሕዛብም ቋንቋዎችም ናቸው። ያየኃቸውም አስር ቀንዶችና አውሬው ጋለሞታይቱን ይጣላሉ፤ ባዶዋንና ራቁትዋንም ያደርጓታል፥ ሥጋዋንም ይበላሉ፥ በእሳትም ያቃጥሉአታል። እግዚአብሔር አሳቡን እንዲያደርጉ አንድንም አሳብ እንዲያደርጉ የእግዚአብሔርም ቃል እስኪፈጸም ድረስ መንግሥታቸውን ለአውሬው እንዲሰጡ በልባቸው አገብቶአልና። ያየሃትም ሴት በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ ታላቂቱ ከተማ ናት።

ራእይ 17:1-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ሰባቱን ጽዋዎች ይዘው ከነበሩት ከሰባቱ መላእክት አንዱ ወደ እኔ መጥቶ እንዲህ አለኝ፦ “ና! በብዙ ውሃዎች ላይ በተቀመጠችው በታላቂቱ አመንዝራ ሴት ላይ የሚደርሰውን ፍርድ አሳይሃለሁ፤ የምድር ነገሥታት ከእርስዋ ጋር አመንዝረዋል፤ የምድር ኗሪዎችም በአመንዝራነትዋ የወይን ጠጅ ሰክረዋል።” ከዚህ በኋላ መልአኩ በመንፈስ ወደ በረሓ ወሰደኝ፤ በሁለንተናው የስድብ ስሞች በተጻፉት፥ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶች ባሉት በቀይ አውሬ ላይ የተቀመጠች አንዲት ሴት አየሁ። ሴቲቱ ሐምራዊና ቀይ ልብስ ለብሳ ነበር፤ በወርቅና በከበረ ድንጋይ በዕንቆችም አሸብርቃ ነበር፤ በእጅዋም የሚያጸይፍ ነገርና የአመንዝራነትዋ ርኲሰት የሞላበትን የወርቅ ጽዋ ይዛ ነበር። በግንባርዋም ላይ “የአመንዝሮችና የምድር ርኲሰቶች እናት፥ ታላቂቱ ባቢሎን” የሚል ምሥጢር ስም ተጽፎ ነበር። ያቺ ሴት በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ሰማዕታት ደም ሰክራ አየኋት፤ ባየኋትም ጊዜ እጅግ በጣም ተደነቅሁ። መልአኩ ግን እንዲህ አለኝ፤ “ስለምን ትደነቃለህ? የሴቲቱን ምሥጢርና እርስዋ የተቀመጠችበትን፥ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶች ያሉትን፥ የአውሬውን ምሥጢር እገልጥልሃለሁ፤ ያየኸው አውሬ ቀድሞ ነበር፤ አሁን የለም፤ በኋላ ከጥልቁ ጒድጓድ ይወጣል፤ ወደ ጥፋቱም ይሄዳል፤ ዓለም ሲፈጠር ጀምሮ ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ያልተጻፉ የምድር ኗሪዎች፥ አውሬው ቀድሞ የነበረ፥ አሁን የሌለ፥ በኋላ የሚመጣ መሆኑን ሲያዩ ይደነቃሉ። “ጥበብ ያለው አእምሮ የሚፈለገው እዚህ ላይ ነው፤ ሰባቱ ራሶች፥ ሴቲቱ የተቀመጠችባቸው ሰባት ተራራዎች ናቸው፤ እንዲሁም ሰባት ነገሥታት ናቸው፤ አምስቱ ወድቀዋል፤ አንዱ አሁን አለ፤ ሌላው ገና አልመጣም፤ እርሱ ሲመጣ ለጥቂት ጊዜ ብቻ መቈየት አለበት። ስምንተኛው ንጉሥ ቀድሞ የነበረውና አሁን የሌለው አውሬ ነው፤ እርሱ ከሰባቱ አንዱ ነው፤ ወደ ጥፋትም ይሄዳል። “ያየሃቸው ዐሥሩ ቀንዶች ገና ያልነገሡ ዐሥር ነገሥታት ናቸው፤ ነገር ግን ለአንዲት ሰዓት ከአውሬው ጋር እንዲነግሡ የመንገሥ ሥልጣን ያገኛሉ። እነዚህ ዐሥር ነገሥታት አንድ ሐሳብ አላቸው፤ እነርሱ ኀይላቸውንና ሥልጣናቸውን ለአውሬው ያስረክባሉ፤ እነርሱ በበጉ ላይ ጦርነት ይከፍታሉ፤ ነገር ግን በጉ የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ ድል ይነሣቸዋል፤ ከእርሱ ጋር ያሉት የተጠሩ የተመረጡና የታመኑ ናቸው።” መልአኩም እንዲህ አለኝ፤ “አመንዝራይቱ ተቀምጣባቸው ያየሃቸው ውሃዎች፥ ሕዝቦችና፥ ሰዎች፥ ወገኖችና የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ናቸው፤ አውሬውና ያየሃቸው ዐሥር ቀንዶች አመንዝራይቱን ይጠላሉ፤ ወደ ጥፋት ያደርሱአታል፤ ራቁትዋን ያስቀሩአታል፤ ሥጋዋን ይበላሉ፤ በእሳትም ያቃጥሏታል፤ ዕቅዱን እንዲፈጽሙ ይህን ሐሳብ በልባቸው ያኖረ እግዚአብሔር ነው፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል እስኪፈጸም እነርሱ በአንድ ሐሳብ ይስማማሉ፤ የመንገሥ ሥልጣናቸውንም ለአውሬው ያስረክባሉ። “ያየሃትም ሴት በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ ታላቂቱ ከተማ ናት።”

ራእይ 17:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ሰባቱንም ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ “ና፤ በብዙም ውሃዎች ላይ የተቀመጠችውን የታላቂቱን አመንዝራ ሴት ፍርድ አሳይሃለሁ፤ የምድርም ነገሥታት ከእርሷ ጋር ሴሰኑ፤ በምድርም የሚኖሩ በዝሙትዋ ወይን ጠጅ ሰከሩ፤” ብሎ ተናገረኝ። በመንፈስም ወደ በረሓ ወሰደኝ፤ የስድብም ስሞች በሞሉበት፥ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶችም ባሉት በቀይ አውሬ ላይ አንዲት ሴት ተቀምጣ አየሁ። ሴቲቱም ሐምራዊና ቀይ ልብስ ለብሳ በወርቅና በከበሩ ድንጋዮች በዕንቈችም ተሸልማ ነበር፤ በእጅዋም የሚያስጸይፍ ነገርና የዝሙትዋ ርኩሰት የሞላባትን የወርቅ ጽዋ ይዛ ነበር በግምባርዋም “ታላቂቱ ባቢሎን፥ የአመንዝሮችና የምድር ርኩሰት እናት” የሚል ምስጢራዊ የሆነ ስም ተጻፈ። ሴቲቱም በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ አየኋት። ባየኋትም ጊዜ በእጅጉ ተደነቅሁ። መልአኩም እንዲህ አለኝ፦ “ለምንድን ነው የምትደነቀው? የሴቲቱን ምስጢርና የሚሸከማትን፥ ሰባት ራሶችና ዐስር ቀንዶች ያሉትን የአውሬውን ምስጢር እኔ እነግርሃለሁ። ያየኸው አውሬ አስቀድሞ ነበረ፤ አሁን ግን የለም፤ ከጥልቁም ሊወጣ ነው፤ ወደ ጥፋትም ይሄዳል፤ ስሞቻቸውም ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ በሕይወት መጽሐፍ ያልተጻፉ የምድር ኗሪዎች አውሬው አስቀድሞ እንደ ነበረ አሁን ደግሞ እንደሌለ፥ ነገር ግን ተመልሶ እንደሚመጣ ሲያዩ ይደነቃሉ። ጥበብ ያለው አእምሮ የሚያስፈልገው እዚህ ላይ ነው። ሰባቱ ራሶች ሴቲቱ የተቀመጠችባቸው ሰባት ተራራዎች ናቸው፤ ሰባትም ነገሥታት ናቸው፤ አምስቱ ወድቀዋል፤ አንዱም አለ፤ የቀረውም ገና አልመጣም፤ ሲመጣም፥ ጥቂት ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል። የነበረውና የሌለውም አውሬ ራሱ ደግሞ ስምንተኛው ነው፤ ከሰባቱም አንዱ ነው፤ ወደ ጥፋትም ይሄዳል። ያየሃቸውም ዐሥሩ ቀንዶች ገና ያልነገሡ ዐሥር ነገሥታት ናቸው፤ ዳሩ ግን ከአውሬው ጋር ለአንድ ሰዓት ያህል እንደ ነገሥታት ሥልጣንን ይቀበላሉ። እነዚህ አንድ እቅድ አላቸው፤ ኀይላቸውንና ሥልጣናቸውንም ለአውሬው ይሰጣሉ። እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ እነርሱን ድል ይነሣል፤ ከእርሱም ጋር ያሉት የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ናቸው።” እንዲህም አለኝ “አመንዝራይቱ የተቀመጠችባቸው ያየሃቸው ውሃዎች፥ ወገኖችና ብዙ ሰዎች፥ አሕዛብም፥ ቋንቋዎችም ናቸው። ያየሃቸውም ዐሥር ቀንዶችና አውሬው አመንዝራይቱን ይጠላሉ፤ ይበዘብዟታል፥ ራቁትዋንም ያደርጓታል፤ ሥጋዋንም ይበላሉ፤ በእሳትም ያቃጥሉአታል። የእግዚአብሔርም ቃል እስኪፈጸም ድረስ ዕቅዱን በአንድ ልብ እንዲያደርጉና መንግሥታቸውንም ለአውሬው እንዲሰጡ እግዚአብሔር በልባቸው አሳድሮአልና። ያየሃትም ሴት በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ ታላቂቱ ከተማ ናት።”