መዝሙር 94:1-11
መዝሙር 94:1-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኑ፥ በእግዚአብሔር ደስ ይበለን፤ ለአምላካችንና ለመድኀኒታችንም እልል እንበል፥ በእምነት ወደ ፊቱ እንድረስ፥ በዝማሬም ለእርሱ እልል እንበል፤ አምላካችን እግዚአብሔር ታላቅ ነውና፥ በአማልክትም ሁሉ ላይ ታላቅ ንጉሥ ነውና። እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥላቸውምና፤ የምድር ዳርቻዎችም ሁሉ በእጁ ውስጥ ናቸውና፥ ረዣዥም ተራሮች የእርሱ ናቸውና። ባሕር የእርሱ ናትና፥ እርሱም ፈጥሯታልና። የብስንም በእጁ ፈጥሯታልና። ኑ፥ እንስገድ ለእርሱም እንገዛ፤ በእርሱ በፈጠረን በእግዚአብሔር ፊት እናልቅስ፤ እርሱ አምላካችን ነውና፥ እኛ ግን ሕዝቡ የማሰማርያውም በጎች ነን። በምድረ በዳ እንደ ተፈታተኑትና እንዳስቈጡት ጊዜ፥ ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ ልባችሁን አታጽኑ። የተፈታተኑኝ አባቶቻችሁ ፈተኑኝ፥ ሥራዬንም አዩ። “ይችን ትውልድ አርባ ዓመታት ተቈጥቻት ነበር፥ ሁልጊዜ ልባቸው ይስታል፥ እነርሱም መንገዴን አላወቁም” አልሁ። ወደ ዕረፍቴም እንዳይገቡ በቍጣዬ ማልሁ።
መዝሙር 94:1-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የበቀል አምላክ፣ አንተ እግዚአብሔር ሆይ፤ የበቀል አምላክ ሆይ፤ ደምቀህ ተገለጥ። አንተ የምድር ዳኛ ሆይ፤ ተነሥ፤ ለትዕቢተኞች የእጃቸውን ስጣቸው። ክፉዎች እስከ መቼ እግዚአብሔር ሆይ፤ ክፉዎች እስከ መቼ ይፈነጫሉ? የእብሪት ቃላት ያዥጐደጕዳሉ፤ ክፉ አድራጊዎች ሁሉ ጕራ ይነዛሉ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ሕዝብህን አደቀቁ፤ ርስትህንም አስጨነቁ። መበለቲቱንና መጻተኛውን ገደሉ፤ የድኻ አደጉንም ነፍስ አጠፉ። እነርሱም “እግዚአብሔር አያይም፤ የያዕቆብም አምላክ አያስተውልም” አሉ። እናንተ በሕዝቡ መካከል ያላችሁ ደነዞች፤ ልብ በሉ፤ እናንተ ሞኞች፤ ጥበበኞች የምትሆኑት መቼ ነው? ጆሮን የተከለው እርሱ አይሰማምን? ዐይንንስ የሠራ እርሱ አያይምን? ሕዝቦችን በተግሣጽ ወደ መንገድ የሚመልስ፣ ዕውቀትንስ ለሰው ልጆች የሚያስተምር አይቀጣምን? እግዚአብሔር የሰው ሐሳብ ከንቱ እንደ ሆነ ያውቃል።
መዝሙር 94:1-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሆይ! አንተ በቀልን የምትመልስ አምላክ ነህ፤ ስለዚህ ፍርድህን ግለጥ! አንተ የዓለም ፈራጅ ነህ፤ ስለዚህ ተነሥ፤ ለትዕቢተኞች የሚገባቸውን ቅጣት ስጣቸው። ክፉዎች የሚታበዩት እስከ መቼ ነው? እግዚአብሔር ሆይ! ኧረ እስከ መቼ ነው? ክፉ አድራጊዎች ሁሉ በድንፋታና በትዕቢታዊ ንግግሮች የተሞሉ ናቸው። እግዚአብሔር ሆይ! ሕዝብህን ያደቃሉ፤ የአንተን ወገኖች ይጨቊናሉ። ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶችና አባትና እናት የሌላቸውን ልጆች ይገድላሉ፤ በምድራችን የሚኖሩትንም መጻተኞች ያጠፋሉ። ይህንንም ሁሉ እያደረጉ “እግዚአብሔር አያየንም፤ የእስራኤል አምላክ አይመለከተንም” ይላሉ። ከሕዝብ መካከል እናንተ አላዋቂዎች ይህን አስተውሉ፤ እናንተ ሞኞች ሆይ! አስተዋዮች የምትሆኑት መቼ ነው? ጆሮን የፈጠረ አምላክ አይሰማምን? ዐይንንስ የፈጠረ አምላክ አያይምን? ሕዝቦችን የሚገሥጸው አይቀጣምን የሰውን ዘር የሚያስተምረው ዕውቀት የለውምን? እግዚአብሔር የሰዎችን ሁሉ ሐሳብና፥ ከንቱነታቸውን ያውቃል።
መዝሙር 94:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እግዚአብሔር የበቀል አምላክ ነው። የበቀል አምላክ ተገለጠ። የምድር ፈራጅ ሆይ፥ ተነሥ፥ ለትዕቢተኞች ፍዳቸውን ክፈላቸው። አቤቱ፥ ክፉዎች እስከ መቼ? ክፉዎች እስከ መቼ ይኮራሉ? ይደነፋሉ፥፥ ክፉ አድራጊዎች ይታበያሉ። አቤቱ፥ ሕዝብህን ረገጡ፥ ርስትህንም ጨቆኑ። መበለቲቱንና ስደተኛውን አረዱ፥ ወላጅ አልባውንም ገደሉ። ጌታ አያይም፥ የያዕቆብ አምላክ አያስተውልም አሉ። የሕዝብ ደንቆሮች ሆይ፥ አስተውሉ፥ ሞኞችስ መቼ ጠቢብ ትሆናላችሁ? ጆሮን የተከለው አይሰማምን? ዓይንን የሠራው አያይምን? አሕዛብንስ የሚገሥጸው፥ ለሰውም እውቀት የሚያስተምረው እርሱ አይቀጣምን? የሰዎች ሐሳብ ከንቱ እንደሆነ ጌታ ያውቃል።