መዝሙር 91:1-8
መዝሙር 91:1-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል፥ ልዑል ሆይ፥ ለስምህም መዘመር፤ በማለዳ ምሕረትህን፥ በሌሊትም እውነትህን መናገር፥ ዐሥር አውታር ባለው በበገና፥ ከምስጋና ጋርም በመሰንቆ። አቤቱ፥ በሥራህ ደስ አሰኝተኸኛልና፤ በእጆችህም ሥራ ደስ ይለኛልና። አቤቱ፥ ሥራህ እጅግ ትልቅ ነው፥ አሳብህም እጅግ ጥልቅ ነው። ሰነፍ ሰው አያውቅም፥ ልብ የሌለውም ይህን አያስተውለውም። ኃጥኣን እንደ ሣር በበቀሉ ጊዜ፥ ዐመፃን የሚያደርጉም ሁሉ በለመለሙ ጊዜ፥ ለዘለዓለም ዓለም እንደሚጠፉ ነው። አቤቱ፥ አንተ ግን ለዘለዓለም ልዑል ነህ፤
መዝሙር 91:1-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በልዑል መጠጊያ የሚኖር፣ በሁሉን ቻይ አምላክ ጥላ ሥር ያድራል። እግዚአብሔርን፣ “መጠጊያዬ፣ ምሽጌ፣ የምታመንብህ አምላኬ” እለዋለሁ። እርሱ ከዐዳኝ ወጥመድ፣ ከአሰቃቂ ቸነፈር ያድንሃልና። በላባዎቹ ይጋርድሃል፤ በክንፎቹ ሥር መሸሸጊያ ታገኛለህ፤ ታማኝነቱ ጋሻና መከታ ይሆንሃል። የሌሊትን አስደንጋጭነት፣ በቀን የሚወረወረውንም ፍላጻ አትፈራም፤ በጨለማ የሚያደባ ቸነፈር፣ በቀትር ረፍራፊውም አያሠጋህም። በአጠገብህ ሺሕ፣ በቀኝህም ዐሥር ሺሕ ይወድቃል፤ ወደ አንተ ግን አይቀርብም። በዐይንህ ብቻ ትመለከታለህ፤ የክፉዎችንም መቀጣት ታያለህ።
መዝሙር 91:1-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
መጠለያ በመፈለግ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ፥ ሁሉን የሚችለውን አምላክ መጠጊያ የሚያደርግ፥ እግዚአብሔርን “አንተ መከታዬና መጠጊያዬ ነህ፤ አንተ የምተማመንብህ አምላኬ ነህ” ይለዋል። እግዚአብሔር ከተሰወሩ ወጥመዶችና ለሞት ከሚያደርሱ በሽታዎች ይጠብቅሃል። በጥበቃው ሥር ያደርግሃል። እርሱ ስለሚንከባከብህ በሰላም ትኖራለህ፤ የእርሱ ታማኝነት እንደ ጋሻ ወይም እንደ ከተማ ቅጽር ይሆንልሃል። “በሌሊት ሽብር ይደርስብኛል፤ በቀን ፍላጻ ይወረወርብኛል” ብለህ አትፈራም። በጨለማ ከሚመጣ ተላላፊ በሽታና በቀትር ከሚወርድ መቅሠፍት አትሰጋም። አንድ ሺህ በአጠገብህ፥ ዐሥር ሺህ በስተቀኝህ ይወድቃሉ፤ አንተ ግን ከቶ አትጐዳም። ክፉዎች ሲቀጡ በዐይንህ ታያለህ።
መዝሙር 91:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል። ጌታን፦ “አንተ መጠጊያዬና መሸሸጊያዬ ነህ እለዋለሁ”፥ የምታመንበት አምላኬ ነውና። እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ ከሚያስደነግጥም ነገር ያድንሃልና። በላባዎቹ ይጋርድሃል፥ ከክንፎቹም በታች ትጠለላለህ፥ ታማኝነቱ እንደ ጋሻና እንደ ቅጥር ይከብብሃል። ከሌሊት ሽብር፥ በቀን ከሚበርር ፍላጻ፥ በጨለማ ከሚጓዝ መቅሰፍት፥ በቀትር ከሚደመስስ አደጋ አትፈራም። በአጠገብህ ሺህ በቀኝህም ዐሥር ሺህ ይወድቃሉ፥ ወደ አንተ የሚጠጋ የለም። በዐይኖችህ ብቻ ትመለከታለህ፥ የኃጥኣንንም ቅጣት ታያለህ።