የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መዝሙር 91

91
እግዚአብሔር ጠባቂያችን ነው
1መጠለያ በመፈለግ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ፥
ሁሉን የሚችለውን አምላክ መጠጊያ የሚያደርግ፥
2እግዚአብሔርን “አንተ መከታዬና መጠጊያዬ ነህ፤
አንተ የምተማመንብህ አምላኬ ነህ” ይለዋል።
3እግዚአብሔር ከተሰወሩ ወጥመዶችና
ለሞት ከሚያደርሱ በሽታዎች ይጠብቅሃል።
4በጥበቃው ሥር ያደርግሃል።
እርሱ ስለሚንከባከብህ በሰላም ትኖራለህ፤
የእርሱ ታማኝነት እንደ ጋሻ ወይም እንደ ከተማ ቅጽር ይሆንልሃል።
5“በሌሊት ሽብር ይደርስብኛል፤
በቀን ፍላጻ ይወረወርብኛል” ብለህ አትፈራም።
6በጨለማ ከሚመጣ ተላላፊ በሽታና
በቀትር ከሚወርድ መቅሠፍት አትሰጋም።
7አንድ ሺህ በአጠገብህ፥
ዐሥር ሺህ በስተቀኝህ ይወድቃሉ፤
አንተ ግን ከቶ አትጐዳም።
8ክፉዎች ሲቀጡ በዐይንህ ታያለህ።
9አንተ እግዚአብሔርን መከታህ፥
ልዑል አምላክንም ጠባቂህ አድርገሃል።
10ስለዚህ ብርቱ አደጋ አይደርስብህም፤
መቅሠፍትም ወደ ቤትህ አይጠጋም።
11ይህም የሚሆነው በምትሄድበት ሁሉ እንዲጠብቁህ
እግዚአብሔር መላእክቱን ስለሚያዛቸው ነው። #ማቴ. 4፥6፤ ሉቃ. 4፥10።
12እግሮችህ ድንጋይ አደናቅፎአቸው እንዳይጐዱ
መላእክቱ በእጆቻቸው ይደግፉሃል። #ማቴ. 4፥6፤ ሉቃ. 4፥11።
13አንበሳንና እባብን ትረግጣለህ፤
በአስፈሪው አንበሳና በመርዛሙ እባብ ላይ ትራመዳለህ። #ሉቃ. 10፥19።
14እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ስለሚወደኝ ከጠላቶቹ እጅ አስጥለዋለሁ፤
ስሜንም ስለሚያውቅ እጠብቀዋለሁ።
15በሚጠራኝም ጊዜ እሰማዋለሁ፤
በመከራው ጊዜ ከእርሱ ጋር እሆናለሁ፤
አድነዋለሁ፤ አከብረዋለሁም።
16ዕድሜ እንዲጠግብ አደርገዋለሁ፤
አዳኝነቴንም አሳየዋለሁ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ