መጽሐፈ መዝሙር 92
92
የምስጋና መዝሙር
1ልዑል እግዚአብሔር ሆይ!
አንተን ማመስገንና
የምስጋና መዝሙር ለአንተ ማቅረብ መልካም ነው።
2ስለ ዘለዓለማዊው ፍቅርህ በየማለዳው መናገር፥
ስለ ታማኝነትህ በየሌሊቱ ማውራት፥
እንዴት መልካም ነው?
3ባለ አውታር በሆኑት የሙዚቃ መሣሪያዎችና በበገና ቅኝት
አንተን ማመስገን እንዴት መልካም ነው?
4እግዚአብሔር ሆይ፥ የአንተ ታላላቅ ሥራዎች ደስ ያሰኙኛል፤
አንተ ስላደረግኻቸውም ነገሮች በደስታ እዘምራለሁ።
5እግዚአብሔር ሆይ! ሥራህ እንዴት ታላቅ ነው!
ሐሳብህስ እንዴት ጥልቅ ነው!
6ይህ ነገር የማይገባው አላዋቂ ለሆነ ሰው ነው፤
ሞኝ ሰውም ቢሆን አይገባውም።
7ክፉዎች እንደ ሣር ቶሎ ቢያድጉም፥
ክፉ አድራጊዎች ቢበለጽጉም፥
እነርሱ ለዘለዓለሙ ይጠፋሉ።
8አንተ ግን እግዚአብሔር ሆይ!
ለዘለዓለም የሁሉ በላይ ነህ።
9እግዚአብሔር ሆይ! ጠላቶችህ ይጠፋሉ፤
ክፉ አድራጊዎችም ሁሉ ይበተናሉ።
10አንተ እንደ ጐሽ ቀንድ ከፍ አደረግኸኝ፤
በትኲስ ዘይትም ቀባኸኝ።
11የጠላቶቼን መሸነፍ አየሁ፤
የአስጨናቂዎቼንም ውድቀት ሰማሁ።
12ደጋግ ሰዎች እንደ ዘንባባ ዛፍ ይለመልማሉ፤
እንደ ሊባኖስ ዛፍም ያድጋሉ።
13በእግዚአብሔር ቤት ተተክለው
በቤተ መቅደስ አደባባይ ውስጥ ተመችቶአቸው ይኖራሉ።
14በእርጅና ዘመናቸው እንኳ ባለማቋረጥ እንደሚያፈሩ፥
ዘወትርም አረንጓዴ እንደ ሆኑ ዛፎች ይሆናሉ።
15ይህም የሚያረጋግጠው እግዚአብሔር ትክክለኛ መሆኑንና
ጠባቂዬ በሆነው አምላክ ዘንድ እንከን ያለመኖሩን ነው።
Currently Selected:
መጽሐፈ መዝሙር 92: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997