መዝሙር 89:1-11
መዝሙር 89:1-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አቤቱ፥ አንተ ለልጅ ልጅ ሁሉ መጠጊያ ሆንህልን። ተራሮች ሳይወለዱ፥ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ፥ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ መቼም መች አንተ ነህ። ሰውን ወደ ኀሣር አትመልሰው፤ የሰው ልጆች ሆይ፥ ተመለሱ ትላለህ፤ ሺህ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትናንት ቀን፥ እንደ ሌሊትም ሰዓት ነውና። ዘመኖች በፊትህ የተናቁ ናቸው፥ በማለዳም እንደ ሣር ያልፋል። ማልዶ ይበቅላል ያልፋልም፥ በሠርክም ጠውልጎና ደርቆ ይወድቃል። እኛ በቍጣህ አልቀናልና፥ በመቅሠፍትህም ደንግጠናልና። ኀጢአታችንን በፊትህ አስቀመጥህ፥ ዓለማችንም በፊትህ ብርሃን ነው። ዘመናችን ሁሉ አልፎአልና፥ እኛም በመቅሠፍትህ አልቀናልና፤ ዘመኖቻችንም እንደ ሸረሪት ድር ይሆናሉ። የዘመኖቻችንም ዕድሜ ሰባ ዓመት ነው፥ ቢበዛም ሰማንያ ዓመት ነው፤ ከእነዚህ ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው፤ የዋህነት ከእኛ አልፋለችና፥ እኛም ተገሥጸናልና። የመቅሠፍትህን ኀይል ማን ያውቃል? ከቍጣህ ግርማ የተነሣ አለቁ።
መዝሙር 89:1-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለ እግዚአብሔር ምሕረት ለዘለላለም እዘምራለሁ፤ በአፌም ታማኝነትህን ከትውልድ እስከ ትውልድ እገልጻለሁ። ምሕረትህን ለዘላለም እንደምትመሠርት፣ ታማኝነትህንም በሰማይ እንደምታጸና እናገራለሁ። አንተም እንዲህ ብለሃል፤ “ከመረጥሁት ጋር ኪዳን ገብቻለሁ፤ ለባሪያዬ ለዳዊት ምያለሁ፤ ‘ዘርህን ለዘላለም እተክላለሁ፤ ዙፋንህንም ከትውልድ እስከ ትውልድ አጸናለሁ።’ ” ሴላ እግዚአብሔር ሆይ፤ ሰማያት ድንቅ ሥራህን፣ ታማኝነትህንም በቅዱሳን ጉባኤ መካከል ያወድሳሉ፤ በላይ በሰማያት ከእግዚአብሔር ጋር ማን ሊስተካከል ይችላል? ከሰማያውያን ፍጥረታትስ መካከል ማን እግዚአብሔርን ይመስለዋል? እግዚአብሔር በቅዱሳን ጉባኤ መካከል በጣም የሚፈራ፣ በዙሪያውም ካሉት ሁሉ በላይ እጅግ የሚከበር ነው። የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ኀያል ነህ፤ ታማኝነትህም ከብቦሃል። የባሕርን ቍጣ ትቈጣጠራለህ፤ ሞገዱም ሲነሣ ጸጥ ታደርገዋለህ። አንተ ረዓብን የተሰየፈ ያህል አደቀቅኸው፤ በብርቱ ክንድህም ጠላቶችህን በተንሃቸው። ሰማያት የአንተ ናቸው፤ ምድርም የአንተ ናት፤ ዓለምንና በውስጧ ያለውን ሁሉ አንተ መሠረትህ።
መዝሙር 89:1-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሆይ! ስለ ዘለዓለማዊው ፍቅርህ ዘወትር እዘምራለሁ፤ እውነተኛነትህንም ለትውልድ ሁሉ እገልጣለሁ። ፍቅርህ ለዘለዓለም እንደሚጸናና ታማኝነትህን እንደ ሰማይ እንደሚመሠረት እናገራለሁ። አንተ አስቀድመህ፦ “ከመረጥኩት ሰው ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ፤ ለአገልጋዬ ለዳዊት የተስፋ ቃል ሰጠሁት” ብለህ ነበር፤ የሰጠኸውም የተስፋ ቃል “ዘርህ ለዘለዓለም ይነግሣል፤ ትውልድህንም ለዘለዓለም አጸናዋለሁ” የሚል ነው። እግዚአብሔር ሆይ! ሰማያት ድንቅ ሥራዎችህን ያመስግኑ የሰማያዊው የቅዱሳን ጉባኤም ታማኝነትህን ከፍ ከፍ ያድርጉ። በሰማይ እግዚአብሔርን የሚመስል የለም፤ ከሰማይ መላእክትም መካከል ከእግዚአብሔር ጋር የሚስተካከል የለም። በሰማያዊው የቅዱሳን ጉባኤ መካከል እግዚአብሔር የተፈራ ነው፤ በዙሪያውም ካሉት ሁሉ ታላቅና አስፈሪ ነው። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! እንደ አንተ ያለ ኀያል ማነው! አንተ በሁሉ ነገር ታማኝ ነህ። አንተ የባሕሩን መናወጥ በሥልጣንህ ታዛለህ፤ ማዕበሉንም ጸጥ ታደርጋለህ። ረዓብ የተባለውን አውሬ ቀጥቅጠህ ገደልከው፤ በታላቁ ኀይልህ ጠላቶችህን በታተንካቸው። ሰማይና ምድር የአንተ ናቸው፤ ዓለምንና በውስጡ ያሉትን ሁሉ የፈጠርክ አንተ ነህ።
መዝሙር 89:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ ጽኑ ፍቅርህን ለዘለዓለም እዘምራለሁ፥ እውነትህንም በአፌ ለልጅ ልጅ እናገራለሁ። እንዲህ ብለሃልና፦ ጽኑ ፍቅርህ ለዘለዓለም ይመሠረታል፥ እውነትህም በሰማይ ይጸናል። ከመረጥሁት ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ፥ ለአገልጋዬም ለዳዊት ማልሁ፦ ዘርህን ለዘለዓለም አዘጋጃለሁ፥ ዙፋንህንም ለልጅ ልጅ እመሠርታለሁ። አቤቱ፥ ሰማያት ድንቅ ሥራህን ታማኝነትህንም፥ በቅዱሳን ማኅበር፥ ያመሰግናሉ። ጌታን በደመናት የሚተካከለው ማን ነው? ከአማልክትስ ልጆች ጌታን ማን ይመስለዋል? በቅዱሳን ምክር እግዚአብሔር ክቡር ነው፥ በዙሪያው ባሉት ሁሉ ላይ ታላቅና ግሩም ነው። አቤቱ የሠራዊት አምላክ፥ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? አቤቱ፥ አንተ ብርቱ ነህ፥ እውነትህም ይከብብሃል። የባሕርን ኃይል አንተ ትገዛለህ፥ የሞገዱንም መናወጥ አንተ ዝም ታሰኘዋለህ። አንተ ረዓብን እንደ ተገደለ አዋረድኸው፥ በኃያሉ ክንድህ ጠላቶችህን በተንሃቸው።