መዝሙር 55:1-23
መዝሙር 55:1-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ ጸሎቴን ስማ፤ ልመናዬን ቸል አትበል፤ ወደ እኔ ተመልከት፤ መልስልኝም። በውስጤ ታውኬአለሁ፤ ተናውጬአለሁም፤ በጠላት ድምፅ ተሸበርሁ፤ በክፉዎች ድንፋታ ደነገጥሁ፤ መከራ አምጥተውብኛልና፤ በቍጣም ተነሣሥተው ጠላት ሆነውብኛል። ልቤ በውስጤ ተጨነቀብኝ፤ የሞት ድንጋጤም በላዬ መጣ። ፍርሀትና እንቅጥቃጤ መጣብኝ፤ ሽብርም ዋጠኝ። እኔም እንዲህ አልሁ፤ “ምነው የርግብ ክንፍ በኖረኝ! በርሬ በሄድሁና ባረፍሁ ነበር፤ እነሆ፤ ኰብልዬ በራቅሁ፣ በምድረ በዳም በሰነበትሁ ነበር፤ ሴላ ከዐውሎ ነፋስና ከውሽንፍር ሸሽቼ፣ ወደ መጠለያዬ ፈጥኜ በደረስሁ ነበር።” ጌታ ሆይ፤ ግፍንና ሁከትን በከተማዪቱ ውስጥ አይቼአለሁና፣ ግራ አጋባቸው፤ ቋንቋቸውንም ደበላልቅ። ቀንና ሌሊት ቅጥሯ ላይ ወጥተው ይዞሯታል፤ ተንኰልና መከራ በውስጧ አለ። ጥፋት በመካከሏ ይገኛል፤ ግፍና አታላይነትም ከጐዳናዋ አይጠፋም። የሚዘልፈኝ ጠላት አይደለምና፤ ቢሆንማ ኖሮ በታገሥሁት ነበር፤ የሚጠላኝ፣ ራሱንም ቀና ቀና ያደረገብኝ ባላንጣ አይደለም፤ ቢሆንማ ከርሱ በተሸሸግሁ ነበር። ነገር ግን አድራጊው አንተ ነህ፤ እኩያዬ፣ ባልንጀራዬና ወዳጄ፤ በእግዚአብሔር ቤት ዐብረን በሕዝብ መካከል ተመላለስን፤ ደስ የሚል ፍቅር በአንድነት ነበረን። ሞት ሳይታሰብ ድንገት ይምጣባቸው፤ በሕይወት ሳሉ ወደ ሲኦል ይውረዱ፤ ክፋት በመካከላቸው ዐድራለችና። እኔ ግን ወደ እግዚአብሔር እጣራለሁ፤ እግዚአብሔርም ያድነኛል። በማታ፣ በጧትና በቀትር፣ እጮኻለሁ፤ እቃትታለሁም፤ እርሱም ድምፄን ይሰማል። በተቃውሞ የተነሡብኝ ብዙዎች ናቸውና፣ ከተቃጣብኝ ጦርነት፣ ነፍሴን በሰላም ይቤዣታል። አካሄዳቸውን አልቀየሩምና፣ እግዚአብሔርንም አልፈሩትምና፣ ከጥንት ጀምሮ በዙፋኑ ላይ ያለ አምላክ፣ ሴላ ሰምቶ ያዋርዳቸዋል። ባልንጀራዬ የምለው ሰው እጁን በወዳጆቹ ላይ ሰነዘረ፤ ቃል ኪዳኑንም አፈረሰ። አፉ ከቅቤ ይልቅ የለዘበ ነው፤ በልቡ ግን ጦርነት አለ፤ ቃሉ ከዘይት ይልቅ የለሰለሰ ነው፤ ይሁን እንጂ የተመዘዘ ሰይፍ ነው። የከበደህን ነገር በእግዚአብሔር ላይ ጣል፤ እርሱ ደግፎ ይይዝሃል፤ የጻድቁንም መናወጥ ከቶ አይፈቅድም። አንተ ግን፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ ክፉዎችን ወደ ጥፋት ጕድጓድ ታወርዳቸዋለህ፤ ደም የተጠሙ ሰዎችና አታላዮች፣ የዘመናቸውን እኩሌታ አይኖሩም።
መዝሙር 55:1-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አምላክ ሆይ! ጸሎቴን ስማ፤ ልመናዬንም ቸል አትበል! የልቤ ጭንቀት ሰላም ስላልሰጠኝ እባክህ፥ አድምጠህ መልስ ስጠኝ። ከጠላቶቼ ዛቻ የተነሣ ፈርቼአለሁ፤ በክፉዎችም ጭቈና ደቅቄአለሁ፤ እነርሱ መከራን ያመጡብኛል፤ በቊጣና በጥላቻ ይመለከቱኛል። ልቤ በውስጤ አስጨንቆኛል፤ የሞት ፍርሀትም ወደቀብኝ። ፍርሀትና ድንጋጤ ይዞኛል፤ መላ ሰውነቴም ተሸብሮአል። እንደ ርግብ ክንፎች ቢኖሩኝ ዕረፍት ወደማገኝበት ስፍራ በርሬ መሄድን በወደድኩ ነበር። ወደ ሩቅ ስፍራ ተጒዤ መኖሪያዬን በበረሓ ባደረግሁ ነበር። ከዚህ ከደረሰብኝ ዐውሎ ነፋስና ሞገድ መጠለያ ስፍራ ለማግኘት ፈጥኜ በሄድኩ ነበር። እግዚአብሔር ሆይ! በከተማይቱ ውስጥ ዐመፅንና ብጥብጥን ስላየሁ፥ የክፉዎችን ምክር አጥፋ፤ ዕቅዳቸውንም ደምስስ! ችግርና ጥፋት የሞላባት ነች። ክፉዎችም ቀንና ሌሊት በቅጽሮችዋ ይዞራሉ። በከተማዋ ውስጥ ጥፋት አለ፤ አደባባዮችዋም በጭቈናና በአታላይነት የተሞሉ ናቸው። የሚሰድበኝ ጠላት አይደለም፤ ጠላት ቢሆንማ ኖሮ በታገሥኩ ነበር። የሚታበይብኝም ባለጋራ አይደለም፤ ባለጋራ ቢሆንማ ኖሮ ከፊቱ በተሰወርኩ ነበር። ይህን ሁሉ የምታደርግብኝ አንተ ግን ከእኔ ከራሴ የማልለይህ፥ ጓደኛዬ፥ የቅርብ ወዳጄ ነህ። በቤተ መቅደስ ከሕዝቡ ሁሉ ጋር አብረን ስንሄድ በመልካም ንግግሮች እንደሰት ነበር። ልባቸው የክፋት ማደሪያ ስለ ሆነ በጠላቶቼ ላይ ድንገተኛ ሞት ይምጣባቸው! በሕይወት ሳሉ ወደ ሙታን ዓለም ይውረዱ! እኔ ግን ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር እጣራለሁ፤ እርሱም ያድነኛል። ዘወትር ጠዋት፥ እኩለ ቀንና ማታ፥ ችግሬንና ሐዘኔን ለእርሱ አስታውቃለሁ፤ እርሱም ድምፄን ይሰማል። እጅግ ከበዙ ጠላቶቼ ጋር ከማደርገው ጦርነት በሰላም ይመልሰኛል። እነርሱ ስለማይለወጡና አምላክን ስለማይፈሩ ለዘለዓለም በዙፋኑ ላይ ያለው አምላክ የእኔን ጸሎት ሰምቶ ያዋርዳቸዋል። ጓደኛዬ ወዳጆቹን አጠቃቸው፤ ቃል ኪዳኑንም አፈረሰ። ንግግሩ እንደ ቅቤ የለዘበ ነው፤ በልቡ የሚያስበው ግን ጦርነትን ነበር አንደበቱ ከዘይት ይበልጥ የለሰለሰ ነው፤ ነገር ግን እንደ ተመዘዘ ሰይፍ ነው። ችግርህን ሁሉ ለእግዚአብሔር አቅርብ፤ እርሱም በእንክብካቤ ይጠብቅሃል፤ እግዚአብሔር ደጋግ ሰዎችን ከቶ ለችግር አሳልፎ አይሰጣቸውም። አምላክ ሆይ! አንተ ግን ክፉዎችን ወደ ጥልቅ ጒድጓድ ትጥላቸዋለህ፤ እነዚያ ነፍሰ ገዳዮችና ከዳተኞች ግማሽ ዕድሜአቸውን እንኳ አይኖሩም፤ እኔ ግን በአንተ እተማመናለሁ።
መዝሙር 55:1-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ ጸሎቴን አድምጥ፥ ልመናዬንም ቸል አትበል። ተመልከተኝ መልስም ስጠኝ፥ በኀዘኔ ተቅበዘበዝሁ ተናወጥሁም፥ ከጠላት ድምፅ ከዓመፀኛም ግፍ የተነሣ፥ ዓመፃን በላዬ ጥለውብኛልና፥ በቁጣም ጠልተውኛልና። ልቤ በላዬ ተናወጠብኝ፥ የሞት ድንጋጤም ወደቀብኝ። ፍርሃትና እንቅጥቅጥ መጡብኝ፥ መዘግነን ሸፈነኝ። በርሬ ዐርፍ ዘንድ እንደ ርግብ ክንፍን ማን በሰጠኝ! እነሆ፥ ኰብልዬ በራቅሁ በምድረ በዳም በተቀመጥሁ፥ ከዐውሎና ከብርቱ ንፋስ ሸሽቼ በፈጠንሁ አልሁ። አቤቱ፥ ግፍንና ጠብን በከተማ ውስጥ አይቼአለሁና አስጥማቸው አንደበታቸውንም ቁረጥ። በቀንና በሌሊት በቅጥርዋ ይከብቡአታል፥ በደልና ሁከት በመካከልዋ ነው፥ በውስጧ ጥፋት አለ፤ ተንኰልና ሽንገላ ከአደባባይዋ አይርቁም። ጠላትስ ቢሰድበኝ፥ በታገሥሁ ነበር፥ የሚጠላኝም ራሱን በላዬ ከፍ ከፍ ቢያደርግ፥ ከእርሱ በተሸሸግሁ ነበር። አንተ ግን፥ እኩያዬ ሰው፥ ባልንጀራዬና የልቤ ወዳጅ፥ መብልን ከእኔ ጋር በአንድነት ያጣፈጥህ፥ በአንድ ልብ በእግዚአብሔር ቤት ተራመድን። ሞት ይምጣባቸው፥ በሕይወት ሳሉ ወደ ሲኦል ይውረዱ፥ ክፋት በማደሪያቸውና በመካከላቸው ነውና። እኔ ግን ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፥ ጌታም ያድነኛል። በማታና በጥዋት በቀትርም አቤቱታ አቀርባለሁ እጮኽማለሁ፥ ቃሌንም ይሰማኛል። በእኔ ላይ ብዙ ነበሩና ከተቃጣብኝ ጦርነት ነፍሴን በሰላም ያድናታል። አይለወጡምና፥ እግዚአብሔርንም አልፈሩትምና ከጥንት ጀምሮ የነበረ እግዚአብሔር ሰምቶ ያጐሰቁላቸዋል። ወዳጄ ከእርሱ ጋር ሰላም በነበሩት ላይ እጁን ዘረጋ፥ ኪዳኑንም አፈረሰ። አፉ ከቅቤ ይልቅ ለዘበ፥ በልቡ ውስጥ ግን ጦርነት ነበረ፥ ቃሎቹም ከዘይት ይልቅ ለሰለሱ፥ ነገር ግን እንደ ተመዘዘ ሰይፍ ናቸው። ሸክምህን በጌታ ላይ ጣል፥ እርሱም ይደግፍሃል፥ ለጻድቁም ለዘለዓለም ሁከትን አይሰጠውም።