መዝሙር 28:1-7
መዝሙር 28:1-7 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የአማልክት ልጆች ሆይ፥ ለእግዚአብሔር አምጡ፥ የጊደሮችን ጥጃ ለእግዚአብሔር አምጡ። ክብርንና ምስጋናን ለእግዚአብሔር አምጡ፥ የስሙን ክብር ለእግዚአብሔር አምጡ፥ በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ። የእግዚአብሔር ቃል በውኆች ላይ ነው። የክብር አምላክ አንጐደጐደ፥ እግዚአብሔር በብዙ ውኆች ላይ ነው። የእግዚአብሔር ቃል በኀይል ነው፤ የእግዚአብሔር ቃል በታላቅ ክብር ነው። የእግዚአብሔር ቃል ዝግባን ይሰብራል፤ እግዚአብሔር የሊባኖስን ዝግባ ይቀጠቅጣል። እንደ ሊባኖስ ላም ያከሳዋል። ተወዳጅ ግን አንድ ቀንድ እንዳለው ርኤም ልጅ ነው። የእግዚአብሔር ቃል የእሳቱን ነበልባል ይቈርጣል።
መዝሙር 28:1-7 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ እጣራለሁ፤ ዐለቴ ሆይ፤ ሰምተህ እንዳልሰማ አትሁንብኝ፤ አንተ ዝም ካልኸኝ፤ ወደ ጕድጓድ እንደሚወርዱ እሆናለሁ። ለርዳታ በጮኽሁ ጊዜ፣ ወደ ቅዱስ ማደሪያህ፣ እጆቼን በዘረጋሁ ጊዜ፣ የልመናዬን ቃል ስማ። በልባቸው ተንኰል እያለ፣ ከባልንጀሮቻቸው ጋራ በሰላም ከሚናገሩ፣ ከክፉ አድራጊዎችና ከዐመፃ ሰዎች ጋራ ጐትተህ አትውሰደኝ። እንደ ሥራቸው፣ እንደ ክፉ ተግባራቸው ክፈላቸው፤ እንደ እጃቸው ሥራ ስጣቸው፤ አጸፋውን መልስላቸው። ለእግዚአብሔር ሥራ ግድ ስለሌላቸው፣ ለእጆቹም ተግባራት ስፍራ ስላልሰጡ፣ እርሱ ያፈርሳቸዋል፤ መልሶም አይገነባቸውም። የልመናዬን ቃል ሰምቷልና፣ እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን። እግዚአብሔር ብርታቴና ጋሻዬ ነው፤ ልቤ በርሱ ይታመናል፤ እርሱም ዐግዞኛል፤ ልቤ ሐሤት አደረገ፤ በዝማሬም አመሰግነዋለሁ።
መዝሙር 28:1-7 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
መከታዬ እግዚአብሔር ሆይ! ወደ አንተ ስጣራ ጩኸቴን ስማ! አንተ ካልሰማኸኝ ግን ወደ መቃብር ከሚወርዱት እንደ አንዱ መሆኔ ነው። ወደ ተቀደሰው ቤተ መቅደስህ እጄን አንሥቼ ለእርዳታ በምጮኽበት ጊዜ እባክህ ጸሎቴን ስማኝ። የክፋትን ሥራ ከሚሠሩ ክፉ ሰዎች ጋር አትውሰደኝ፤ እነርሱ ከጐረቤቶቻቸው ጋር በሰላም ይነጋገራሉ፤ በልባቸው ግን ተንኰል አለ። ስለ ፈጸሙት በደል ተገቢ ዋጋቸውን ክፈላቸው፤ በእጃቸው ስለ ፈጸሙት ክፉ ሥራ ፍረድባቸው፤ ተገቢ ቅጣታቸውንም ስጣቸው። እነርሱ ለእግዚአብሔር አድራጎትና ለእጁ ሥራ ትኲረት ስለማይሰጡ እርሱ ይሰባብራቸዋል፤ እንደገናም አይገነባቸውም። የልመናዬን ድምፅ ስለ ሰማኝ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን። እግዚአብሔር ኀይሌና ጋሻዬ ነው፤ ስለሚረዳኝና ደስ ስለሚያሰኘኝም በእርሱ እተማመናለሁ፤ በመዝሙሮቼም አመሰግነዋለሁ።
መዝሙር 28:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ ወደ አንተ እጠራለሁ፥ ዝም ብትለኝ ወደ ጉድጓድ እንደሚወርዱት እንዳልመስል፥ አንተ ዓለቴ ሆይ፥ ዝም አትበለኝ። ወደ መቅደስህ ማደሪያ እጄን ባነሣሁ ጊዜ፥ ወደ አንተ የጮኽሁትን የልመናዬን ቃል ስማ። ከኃጥኣንና ከክፉ አድራጊዎች ጋር ነፍሴን አትውሰዳት፥ ክፋትም በልባቸው እያለ ከባልንጀራቸው ጋር ሰላም ከሚናገሩት ጋር አትጣለኝ። እንደ ሥራቸው እንደ አካሄዳቸውም ክፋት ስጣቸው፥ እንደ እጃቸውም ሥራ ስጣቸው፥ ፍዳቸውን ወደ ራሳቸው መልስ። ወደ ጌታ ሥራ ወደ እጆቹም አደራረግ አላሰቡምና ያፈርሳቸዋል እንጂ አይሠራቸውም። የልመናዬን ቃል ሰምቶኛልና ጌታ ይመስገን። ጌታ ኃይሌና ጋሻዬ ነው፥ ልቤ በእርሱ ታመነ እኔም ተረዳሁ፥ ልቤም ደስ ይለዋል፥ ፈቅጄም አመሰግነዋለሁ።