መዝሙረ ዳዊት 28:1-7

መዝሙረ ዳዊት 28:1-7 መቅካእኤ

አቤቱ፥ ወደ አንተ እጠራለሁ፥ ዝም ብትለኝ ወደ ጉድጓድ እንደሚወርዱት እንዳልመስል፥ አንተ ዓለቴ ሆይ፥ ዝም አትበለኝ። ወደ መቅደስህ ማደሪያ እጄን ባነሣሁ ጊዜ፥ ወደ አንተ የጮኽሁትን የልመናዬን ቃል ስማ። ከኃጥኣንና ከክፉ አድራጊዎች ጋር ነፍሴን አትውሰዳት፥ ክፋትም በልባቸው እያለ ከባልንጀራቸው ጋር ሰላም ከሚናገሩት ጋር አትጣለኝ። እንደ ሥራቸው እንደ አካሄዳቸውም ክፋት ስጣቸው፥ እንደ እጃቸውም ሥራ ስጣቸው፥ ፍዳቸውን ወደ ራሳቸው መልስ። ወደ ጌታ ሥራ ወደ እጆቹም አደራረግ አላሰቡምና ያፈርሳቸዋል እንጂ አይሠራቸውም። የልመናዬን ቃል ሰምቶኛልና ጌታ ይመስገን። ጌታ ኃይሌና ጋሻዬ ነው፥ ልቤ በእርሱ ታመነ እኔም ተረዳሁ፥ ልቤም ደስ ይለዋል፥ ፈቅጄም አመሰግነዋለሁ።