የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙር 119:97-120

መዝሙር 119:97-120 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

አቤቱ፤ ሕግህን ምንኛ ወደድሁ! ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ። ትእዛዞችህ ምን ጊዜም ስለማይለዩኝ፣ ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረጉኝ። ምስክርነትህን አሰላስላለሁና፣ ከአስተማሪዎቼ ሁሉ የላቀ አስተዋይ ልብ አገኘሁ። መመሪያህን ተከትዬ እሄዳለሁና፣ ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋይ ሆንሁ። ቃልህን እጠብቅ ዘንድ፣ እግሬን ከክፉ መንገድ ሁሉ ከለከልሁ። አንተው ራስህ አስተምረኸኛልና፣ ከድንጋጌህ ዘወር አላልሁም። ቃልህ ለምላሴ ምንኛ ጣፋጭ ነው! ለአፌም ከማር ወለላ ይልቅ ጣዕም አለው። ከመመሪያህ ማስተዋልን አገኘሁ፤ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ሁሉ ጠላሁ። ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው። የጽድቅ ሕግህን ለመጠበቅ፤ ምያለሁ፤ ይህንኑ አጸናለሁ። እጅግ ተቸግሬአለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቃልህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ በከንፈሬ ያቀረብሁትን የበጎ ፈቃድ ስጦታ ተቀበል፤ ሕግህንም አስተምረኝ። ነፍሴ ዘወትር አደጋ ላይ ናት፤ ሕግህን ግን አልረሳሁም። ክፉዎች ወጥመድ ዘረጉብኝ፤ እኔ ግን መመሪያህን አልተላለፍሁም። ምስክርነትህ የዘላለም ውርሴ ናት፤ ልቤ በዚህ ሐሤት ያደርጋልና። ትእዛዝህን ለዘላለም፣ እስከ ወዲያኛው ለመፈጸም፣ ልቤን ወደዚያው አዘነበልሁ። መንታ ልብ ያላቸውን ጠላሁ፤ ሕግህን ግን ወደድሁ። አንተ መጠጊያዬና ጋሻዬ ነህ፤ ቃልህን በተስፋ እጠብቃለሁ። የአምላኬን ትእዛዞች እጠብቅ ዘንድ፣ እናንተ ክፉ አድራጊዎች ከእኔ ራቁ። እንደ ቃልህ ደግፈኝ፤ እኔም ሕያው እሆናለሁ፤ ተስፋዬም መና ቀርቶ አልፈር። ያለ ሥጋት እቀመጥ ዘንድ ደግፈህ ያዘኝ፤ ሥርዐትህንም ዘወትር እመለከታለሁ። መሠሪነታቸው በከንቱ ነውና፣ ከሥርዐትህ ውጭ የሚሄዱትን ሁሉ ወዲያ አስወገድሃቸው። የምድርን ክፉዎች ሁሉ እንደ ጥራጊ አስወገድሃቸው፤ ስለዚህ ምስክርህን ወደድሁ። ሥጋዬ አንተን በመፍራት ይንቀጠቀጣል፤ ፍርድህንም እፈራለሁ።

መዝሙር 119:97-120 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ሕግህን እጅግ እወዳለሁ፤ ስለ እርሱ ቀኑን ሙሉ አስባለሁ። ትእዛዝህ መቼም ከአእምሮዬ ስለማይጠፋ፥ ከጠላቶቼ ሁሉ ይልቅ እኔን አስተዋይ ያደርገኛል። ሕግህን ዘወትር ስለማሰላስል፥ ከአስተማሪዎቼ ሁሉ የበለጠ ጥበብ አለኝ። ትእዛዞችህን ሁሉ ስለምፈጽም፥ ከሽማግሌዎች ሁሉ የበለጠ አስተዋይነት አለኝ። ለቃልህ መታዘዝ ስለምፈልግ፥ መጥፎ ጠባይን ሁሉ አስወግጄአለሁ። ያስተማርከኝ አንተ ስለ ሆንክ ከሕግህ ፈቀቅ አላልኩም። ቃልህ እንዴት ጣፋጭ ነው! ከማር ወለላ ይልቅ ይጣፍጣል። ከሕግህ ማስተዋልን አግኝቼአለሁ፤ ስለዚህ የሐሰት መንገድን ሁሉ እጠላለሁ። ቃልህ እንደ መብራት ይመራኛል፤ ለመንገዴም ብርሃን ነው። እውነተኛ ትእዛዞችህን ለመጠበቅ በመሐላ የገባሁትን ቃል አጸናለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! ሥቃዬ እጅግ ከባድ ስለ ሆነ በተስፋ ቃልህ መሠረት በሕይወት አኑረኝ። እግዚአብሔር ሆይ! የምስጋና ጸሎቴን ተቀበል፤ ትእዛዞችህንም አስተምረኝ። ሕይወቴ በአደጋ ላይ ቢሆንም እንኳ ሕግህን አልረሳም ክፉዎች ወጥመድ ዘረጉብኝ፤ እኔ ግን ከትእዛዞችህ ፈቀቅ አላልኩም። ሕግህ ዘለዓለማዊ ሀብቴ ነው፤ የልቤም ደስታ እርሱ ነው። እስከምሞትበት ቀን ድረስ ሕጎችህን ለመፈጸም ወስኜአለሁ፤ በፍጹም ልባቸው በአንተ የማይታመኑትን ወላዋዮች ሁሉ ጠላሁ፤ ሕግህን ግን ወደድኩ። አንተ ጋሻዬና መሸሸጊያዬ ነህ፤ በቃልህ ተስፋ አደርጋለሁ። እናንተ ክፉ አድራጊዎች ከእኔ ወዲያ ራቁ፤ እኔ የአምላኬን ትእዛዞች መጠበቅ እፈልጋለሁ። በሕይወት እኖር ዘንድ በተስፋ ቃልህ መሠረት አበርታኝ! ተስፋዬንም አታጨልምብኝ! እድን ዘንድ ደግፈኝ፤ ሁልጊዜም ሕጎችህን እፈጽማለሁ። ዕቅዳቸው ተንኰልና ሐሰት የሞላበት በመሆኑ፥ ከሕግህ የሚያፈነግጡትን ሁሉ ታስወግዳቸዋለህ። ክፉዎችን ሁሉ እንደ ቆሻሻ ነገር ታስወግዳቸዋለህ፤ ስለዚህ ሥርዓትህን እወዳለሁ። አንተን ከመፍራቴ የተነሣ ሰውነቴ ተንቀጠቀጠ፤ ፍርድህንም እጅግ ፈራሁት።

መዝሙር 119:97-120 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

አቤቱ፥ ሕግህን እንደምን እጅግ ወደድሁ! ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው። ለዘለዓለም ለእኔ ነውና ትእዛዝህ ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረገኝ። ምስክርህ ትዝታዬ ነውና ካስተማሩኝ ሁሉ ይልቅ አስተዋልሁ። ትእዛዝህን ፈልጌአለሁና ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋልሁ። ቃልህን እጠብቅ ዘንድ ከክፉ መንገድ ሁሉ እግሬን ከለከልሁ። አስተምረኸኛልና ከፍርድህ አልራቅሁም። ቃልህ ለጉሮሮዬ ጣፋጭ ነው፥ ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ። ከትእዛዝህ የተነሣ አስተዋልሁ፥ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ጠላሁ። ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው። የጽድቅህን ፍርድ እጠብቅ ዘንድ ማልሁ፥ አጸናሁም። እጅግ ተቸገርሁ፥ አቤቱ፥ እንደ ቃልህ ሕያው አድርገኝ። አቤቱ፥ ከአፌ የሚወጣውን ቃል ውደድ፥ ፍርድህንም አስተምረኝ። ነፍሴ ሁልጊዜ በእጅህ ውስጥ ናት፥ ሕግህን ግን አልረሳሁም። ኃጢአተኞች ወጥመድን ዘረጉብኝ፥ ከትእዛዝህ ግን አልሳትሁም። የልቤ ደስታ ነውና ምስክርህን ለዘለዓለም ወረስሁ። ለዘለዓለም ለፍጻሜውም ትእዛዝህን አደርግ ዘንድ ልቤን አዘነበልሁ። ዓመፀኞችን ጠላሁ፥ ሕግን ግን ወደድሁ። አንተ ረዳቴና መጠጊያዬ ነህ፥ በቃልህም ተማመንሁ። እናንተ ኃጢአተኞች፥ ከእኔ ራቁ፥ የአምላኬንም ትእዛዝ ልፈልግ። እንደ ቃልህ ደግፈኝ፥ ሕያውም እሆናለሁ፥ ከተስፋዬም አልፈር። እርዳኝ እድናለሁም፥ ሁልጊዜም ሥርዓትህን እመረምራለሁ። ምኞታቸው ዓመፃ ነውና ከሥርዓትህ የሚርቁትን ሁሉ አጐሳቈልሃቸው። የምድርን ኃጢአተኞች ሁሉ እንደ ርኩሰት አጠፋሃቸው፥ ስለዚህ ምስክርህን ወደድሁ። ሥጋዬ አንተን ከመፍራት የተነሣ ደነገጠ፥ ከፍርድህ የተነሣ ፈርቻለሁ።