ሕግህን እጅግ እወዳለሁ፤ ስለ እርሱ ቀኑን ሙሉ አስባለሁ። ትእዛዝህ መቼም ከአእምሮዬ ስለማይጠፋ፥ ከጠላቶቼ ሁሉ ይልቅ እኔን አስተዋይ ያደርገኛል። ሕግህን ዘወትር ስለማሰላስል፥ ከአስተማሪዎቼ ሁሉ የበለጠ ጥበብ አለኝ። ትእዛዞችህን ሁሉ ስለምፈጽም፥ ከሽማግሌዎች ሁሉ የበለጠ አስተዋይነት አለኝ። ለቃልህ መታዘዝ ስለምፈልግ፥ መጥፎ ጠባይን ሁሉ አስወግጄአለሁ። ያስተማርከኝ አንተ ስለ ሆንክ ከሕግህ ፈቀቅ አላልኩም። ቃልህ እንዴት ጣፋጭ ነው! ከማር ወለላ ይልቅ ይጣፍጣል። ከሕግህ ማስተዋልን አግኝቼአለሁ፤ ስለዚህ የሐሰት መንገድን ሁሉ እጠላለሁ። ቃልህ እንደ መብራት ይመራኛል፤ ለመንገዴም ብርሃን ነው። እውነተኛ ትእዛዞችህን ለመጠበቅ በመሐላ የገባሁትን ቃል አጸናለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! ሥቃዬ እጅግ ከባድ ስለ ሆነ በተስፋ ቃልህ መሠረት በሕይወት አኑረኝ። እግዚአብሔር ሆይ! የምስጋና ጸሎቴን ተቀበል፤ ትእዛዞችህንም አስተምረኝ። ሕይወቴ በአደጋ ላይ ቢሆንም እንኳ ሕግህን አልረሳም ክፉዎች ወጥመድ ዘረጉብኝ፤ እኔ ግን ከትእዛዞችህ ፈቀቅ አላልኩም። ሕግህ ዘለዓለማዊ ሀብቴ ነው፤ የልቤም ደስታ እርሱ ነው። እስከምሞትበት ቀን ድረስ ሕጎችህን ለመፈጸም ወስኜአለሁ፤ በፍጹም ልባቸው በአንተ የማይታመኑትን ወላዋዮች ሁሉ ጠላሁ፤ ሕግህን ግን ወደድኩ። አንተ ጋሻዬና መሸሸጊያዬ ነህ፤ በቃልህ ተስፋ አደርጋለሁ። እናንተ ክፉ አድራጊዎች ከእኔ ወዲያ ራቁ፤ እኔ የአምላኬን ትእዛዞች መጠበቅ እፈልጋለሁ። በሕይወት እኖር ዘንድ በተስፋ ቃልህ መሠረት አበርታኝ! ተስፋዬንም አታጨልምብኝ! እድን ዘንድ ደግፈኝ፤ ሁልጊዜም ሕጎችህን እፈጽማለሁ። ዕቅዳቸው ተንኰልና ሐሰት የሞላበት በመሆኑ፥ ከሕግህ የሚያፈነግጡትን ሁሉ ታስወግዳቸዋለህ። ክፉዎችን ሁሉ እንደ ቆሻሻ ነገር ታስወግዳቸዋለህ፤ ስለዚህ ሥርዓትህን እወዳለሁ። አንተን ከመፍራቴ የተነሣ ሰውነቴ ተንቀጠቀጠ፤ ፍርድህንም እጅግ ፈራሁት።
መጽሐፈ መዝሙር 119 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መዝሙር 119:97-120
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos