መዝሙር 119:73-96
መዝሙር 119:73-96 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እጆችህ ሠሩኝ፤ አበጃጁኝም፤ ትእዛዞችህን እንድማር ማስተዋልን ስጠኝ። ቃልህን ተስፋ አድርጌአለሁና፣ የሚፈሩህ እኔን አይተው ደስ ይበላቸው። እግዚአብሔር ሆይ፤ ፍርድህ የጽድቅ ፍርድ፣ ያስጨነቅኸኝም በታማኝነት እንደ ሆነ ዐወቅሁ። ለአገልጋይህ በገባኸው ቃል መሠረት፣ ምሕረትህ ለመጽናናት ትሁነኝ። ሕግህ ደስታዬ ነውና፣ በሕይወት እኖር ዘንድ ቸርነትህ ትምጣልኝ። እብሪተኞች ያለ ምክንያት በደል አድርሰውብኛልና ይፈሩ፤ እኔ ግን ትእዛዞችህን አሰላስላለሁ። አንተን የሚፈሩህ፣ ምስክርነትህንም የሚያውቁ ወደ እኔ ይመለሱ። እኔ እንዳላፍር፣ ልቤ በሥርዐትህ ፍጹም ይሁን። ነፍሴ ማዳንህን እጅግ ናፈቀች፤ ቃልህንም ተስፋ አደርጋለሁ። “መቼ ታጽናናኛለህ?” እያልሁ፣ ዐይኖቼ ቃልህን በመጠባበቅ ደከሙ። ጢስ የጠጣ የወይን አቍማዳ ብመስልም፣ ሥርዐትህን አልረሳሁም። የባሪያህ ዕድሜ ስንት ቢሆን ነው? ታዲያ፣ በሚያሳድዱኝ ላይ የምትፈርደው መቼ ይሆን? በሕግህ መሠረት የማይሄዱ እብሪተኞች ማጥመጃ ጕድጓድ ቈፈሩልኝ። ትእዛዞችህ ሁሉ አስተማማኝ ናቸው፤ ሰዎች ያለ ምክንያት አሳድደውኛልና ርዳኝ። ከምድር ላይ ሊያስወግዱኝ ጥቂት ቀራቸው፤ እኔ ግን ትእዛዞችህን አልተውሁም። እንደ ምሕረትህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ፤ እኔም የአፍህን ምስክርነት እጠብቃለሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ቃልህ በሰማይ፣ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። ታማኝነትህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ሁሉ ይኖራል፤ ምድርን መሠረትሃት፤ እርሷም ጸንታ ትኖራለች። ሁሉም አገልጋይህ ነውና፣ በሕግህ መሠረት እስከ ዛሬ ድረስ ጸንተው ይኖራሉ። ሕግህ ደስታዬ ባይሆን ኖሮ፣ በመከራዬ ወቅት በጠፋሁ ነበር። በርሱ ሕያው አድርገኸኛልና፣ ትእዛዝህን ከቶ አልረሳም። እኔ የአንተ ነኝ፤ እባክህ አድነኝ፤ ሕግህንም ፈልጌአለሁና። ክፉዎች ሊያጠፉኝ አድብተዋል፤ እኔ ግን ምስክርነትህን አሰላስላለሁ። ለፍጹምነት ሁሉ ዳርቻ እንዳለው አየሁ፤ ትእዛዝህ ግን እጅግ ሰፊ ነው።
መዝሙር 119:73-96 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እጆችህ ሠሩኝ፤ አበጃጁኝም፤ ትእዛዞችህን እማር ዘንድ አስተዋይነትን ስጠኝ። በተስፋ ቃልህ ስለምታመን አንተን የሚያከብሩ ሁሉ እኔን በሚያዩበት ጊዜ ደስ ይበላቸው። እግዚአብሔር ሆይ! ፍርድህ እውነተኛ እንደ ሆነ ዐውቃለሁ፤ የቀጣኸኝም እውነተኛ በመሆንህ ነው። ለእኔ ለአገልጋይህ በሰጠኸው የተስፋ ቃል መሠረት ዘለዓለማዊው ፍቅርህ ያጽናናኝ። በሕግህ ደስ ስለሚለኝ ሕያው ሆኜ ለመኖር እችል ዘንድ ርኅራኄ አድርግልኝ። በሐሰት ያለምክንያት የሚከሱኝ ትዕቢተኞች ይዋረዱ፤ እኔ ግን ሕግህን አሰላስላለሁ። አንተን የሚፈሩ ትእዛዞችህን ያውቁ ዘንድ ወደ እኔ ይምጡ። ኀፍረት እንዳይደርስብኝ ሕግህን በትክክል እንድፈጽም እርዳኝ። የአንተን አዳኝነት በሙሉ ልቤ እመኛለሁ። እምነቴን በቃልህ ላይ አድርጌአለሁ። “መቼ ታጽናናኝ ይሆን?” ብዬ የተስፋ ቃልህን በመጠባበቅ ዐይኖቼ ደከሙ። ጢስ በሚጤስበት ቤት ተሰቅሎ እንደ ተጨማደደ የወይን ጠጅ አቊማዳ ከጥቅም ውጪ ሆኜአለሁ፤ ይህም ሁሉ ሆኖ ሕግህን አልረሳሁም። እኔ አገልጋይህ እስከ መቼ ልቈይ? የሚያሳድዱኝንስ የምትቀጣቸው መቼ ነው? ሕግህን የማይጠብቁ ትዕቢተኞች እኔን ለማጥመድ ጒድጓድ ቆፍረዋል። ትእዛዞችህ ሁሉ የጸኑ ናቸው፤ ያለ ምክንያት ስለሚያሳድዱኝ እርዳኝ! እነርሱ ሊገድሉኝ ጥቂት ቀርቶአቸው ነበር፤ እኔ ግን ትእዛዞችህን ችላ አላልኩም። ሕግህን እጠብቅ ዘንድ በዘለዓለማዊ ፍቅርህ ሕይወትን ስጠኝ። እግዚአብሔር ሆይ! ቃልህ ዘለዓለማዊ ነው፤ በሰማይም ጸንቶ ይኖራል። ቃልህ በዘመናት ሁሉ ጸንቶ ይኖራል፤ ምድርን መሠረትካት፤ ጸንታም ትኖራለች። ፍጥረቶች ሁሉ አገልጋዮችህ ስለ ሆኑ ትእዛዞችህ እስከ ዛሬ ጸንተው ቈይተዋል። ሕግህ የደስታዬ ምንጭ ባይሆን ኖሮ ከሥቃዬ የተነሣ በሞትኩ ነበር። በሕግህ አማካይነት በሕይወት እንድኖር ጠብቀኸኛልና ሕግህን ከቶ አልረሳም። እኔ የአንተ ስለ ሆንኩ አድነኝ! ትእዛዞችህንም ለማክበር እፈልጋለሁ። ክፉዎች እኔን ለመግደል ያደባሉ፤ እኔ ግን ሕግህን አሰላስላለሁ። የሁሉም ነገር ፍጹምነት ወሰን አለው፤ የትእዛዞችህ ፍጹምነት ግን ወሰን የለውም።
መዝሙር 119:73-96 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እጆችህ ሠሩኝ አበጃጁኝም፥ እንዳስተውል አድርገኝ፥ ትእዛዛትህንም እማራለሁ። በቃልህ ታምኛለሁና የሚፈሩህ እኔን አይተው ደስ ይላቸዋል። አቤቱ፥ ፍርድህ ጽድቅ እንደ ሆነች፥ በእውነትህም እንዳስቸገርኸኝ አወቅሁ። ምሕረትህ ለመጽናናቴ ትሁነኝ፥ እንደ ቃልህም ለባርያህ ይሁነው። ሕግህ ተድላዬ ናትና ቸርነትህ ትምጣልኝ፥ በሕይወትም ልኑር። ትዕቢተኞች በዓመፅ ጠምመውብኛልና ይፈሩ፥ እኔ ግን ትእዛዝህን አሰላስላለሁ። የሚፈሩህና ምስክሮችህን የሚያውቁ ወደ እኔ ይመለሱ። እንዳላፍር ልቤ በሥርዓትህ የቀና ይሁን። ነፍሴ መድኃኒትህን ናፈቀች፥ በቃልህም ታመንሁ። መቼ ታጽናናኛለህ እያልሁ ዐይኖቼ ስለ ቃልህ ፈዘዙ። በጢስ ውስጥ እንዳለ አቁማዳ ሆኛለሁና፥ ሥርዓትህን ግን አልረሳሁም። የባርያህ ዘመኖች ስንት ናቸው? በሚያሳድዱኝስ ላይ መቼ ትፈርድልኛለህ? ኃጢአተኞች ጉድጓድ ቆፈሩልኝ፥ አቤቱ፥ እንደ ሕግህ ግን አይደለም። ትእዛዛትህ ሁሉ እውነት ናቸው፥ በዓመፅ አሳድደውኛል፥ እርዳኝ። ከምድር ሊያጠፉኝ ጥቂት ቀርቶአቸው ነበር፥ እኔ ግን ትእዛዛትህን አልተውሁም። እንደ ምሕረትህ ሕያው አድርገኝ፥ የአፍህንም ምስክር እጠብቃለሁ። አቤቱ፥ ቃልህ በሰማይ ለዘለዓለም ይኖራል። እውነትህ ለልጅ ልጅ ናት፥ ምድርን መሠረትሃት እርሷም ትኖራለች። ሁሉም ባርያዎችህ ናቸውና ቀኑ በትእዛዝህ ይኖራል። ሕግህ ተድላዬ ባይሆን፥ ቀድሞ በጉስቁልናዬ በጠፋሁ ነበር። በእርሱ ሕያው አድርገኸኛልና ፍርድህን ለዘለዓለም አልረሳም። እኔ የአንተ ነኝ፥ ፍርድህን ፈልጌአለሁና አድነኝ። ኃጢአተኞች ያጠፉኝ ዘንድ ጠበቁኝ፥ ምስክርህን ግን መረመርሁ። የሥራን ሁሉ ፍጻሜ አየሁ፥ ትእዛዝህ ግን እጅግ ሰፊ ነው።