መዝሙረ ዳዊት 119:73-96

መዝሙረ ዳዊት 119:73-96 መቅካእኤ

እጆችህ ሠሩኝ አበጃጁኝም፥ እንዳስተውል አድርገኝ፥ ትእዛዛትህንም እማራለሁ። በቃልህ ታምኛለሁና የሚፈሩህ እኔን አይተው ደስ ይላቸዋል። አቤቱ፥ ፍርድህ ጽድቅ እንደ ሆነች፥ በእውነትህም እንዳስቸገርኸኝ አወቅሁ። ምሕረትህ ለመጽናናቴ ትሁነኝ፥ እንደ ቃልህም ለባርያህ ይሁነው። ሕግህ ተድላዬ ናትና ቸርነትህ ትምጣልኝ፥ በሕይወትም ልኑር። ትዕቢተኞች በዓመፅ ጠምመውብኛልና ይፈሩ፥ እኔ ግን ትእዛዝህን አሰላስላለሁ። የሚፈሩህና ምስክሮችህን የሚያውቁ ወደ እኔ ይመለሱ። እንዳላፍር ልቤ በሥርዓትህ የቀና ይሁን። ነፍሴ መድኃኒትህን ናፈቀች፥ በቃልህም ታመንሁ። መቼ ታጽናናኛለህ እያልሁ ዐይኖቼ ስለ ቃልህ ፈዘዙ። በጢስ ውስጥ እንዳለ አቁማዳ ሆኛለሁና፥ ሥርዓትህን ግን አልረሳሁም። የባርያህ ዘመኖች ስንት ናቸው? በሚያሳድዱኝስ ላይ መቼ ትፈርድልኛለህ? ኃጢአተኞች ጉድጓድ ቆፈሩልኝ፥ አቤቱ፥ እንደ ሕግህ ግን አይደለም። ትእዛዛትህ ሁሉ እውነት ናቸው፥ በዓመፅ አሳድደውኛል፥ እርዳኝ። ከምድር ሊያጠፉኝ ጥቂት ቀርቶአቸው ነበር፥ እኔ ግን ትእዛዛትህን አልተውሁም። እንደ ምሕረትህ ሕያው አድርገኝ፥ የአፍህንም ምስክር እጠብቃለሁ። አቤቱ፥ ቃልህ በሰማይ ለዘለዓለም ይኖራል። እውነትህ ለልጅ ልጅ ናት፥ ምድርን መሠረትሃት እርሷም ትኖራለች። ሁሉም ባርያዎችህ ናቸውና ቀኑ በትእዛዝህ ይኖራል። ሕግህ ተድላዬ ባይሆን፥ ቀድሞ በጉስቁልናዬ በጠፋሁ ነበር። በእርሱ ሕያው አድርገኸኛልና ፍርድህን ለዘለዓለም አልረሳም። እኔ የአንተ ነኝ፥ ፍርድህን ፈልጌአለሁና አድነኝ። ኃጢአተኞች ያጠፉኝ ዘንድ ጠበቁኝ፥ ምስክርህን ግን መረመርሁ። የሥራን ሁሉ ፍጻሜ አየሁ፥ ትእዛዝህ ግን እጅግ ሰፊ ነው።