መዝሙር 119:1-88

መዝሙር 119:1-88 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ብፁዓን ናቸው፤ መንገዳቸው ነቀፋ የሌለበት፣ በእግዚአብሔርም ሕግ የሚሄዱ፤ ብፁዓን ናቸው እግዚአብሔር ሕግ፤ ምስክርነቱን የሚጠብቁ፣ በፍጹምም ልብ የሚሹት፤ ዐመፅን አያደርጉም፤ ነገር ግን በመንገዱ ይሄዳሉ። ጠንቅቀን እንጠብቃት ዘንድ፣ አንተ ሥርዐትን አዝዘሃል። ሥርዐትህን እጠብቅ ዘንድ፣ ምነው መንገዴ ጽኑ በሆነልኝ ኖሮ! ወደ ትእዛዞችህ ስመለከት፣ በዚያ ጊዜ አላፍርም። የጽድቅ ፍርድህን ስማር፣ በቅን ልብ ምስጋና አቀርብልሃለሁ። ሥርዐትህን እጠብቃለሁ፤ ፈጽመህ አትተወኝ። ጕልማሳ መንገዱን እንዴት ያነጻል? በቃልህ መሠረት በመኖር ነው። በሙሉ ልቤ ፈለግሁህ፤ ከትእዛዞችህ ፈቀቅ እንዳልል አድርገኝ። አንተን እንዳልበድል፣ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ቡሩክ ነህ፤ ሥርዐትህን አስተምረኝ። ከአንደበትህ የሚወጣውን ደንብ ሁሉ፣ በከንፈሬ እናገራለሁ። ሰው በሀብቱ ብዛት ደስ እንደሚለው፣ ምስክርነትህን በመከተል ደስ ይለኛል። ድንጋጌህን አሰላስላለሁ፤ ልቤን በመንገድህ ላይ ጥያለሁ። በሥርዐትህ ደስ ይለኛል፤ ቃልህንም አልዘነጋም። ሕያው እንድሆን፣ ቃልህንም እንድጠብቅ፣ ለአገልጋይህ መልካም አድርግ። ከሕግህ ድንቅ ነገርን እንዳይ፣ ዐይኖቼን ክፈት። እኔ በምድር ላይ መጻተኛ ነኝ፤ ትእዛዞችህን ከእኔ አትሰውር። ዘወትር ደንብህን በመናፈቅ፣ ነፍሴ እጅግ ዛለች። ከትእዛዞችህ የሳቱትን፣ እብሪተኞችንና ርጉሞችን ትገሥጻለህ። ምስክርነትህን ጠብቄአለሁና፣ ስድብንና ንቀትን ከእኔ አርቅ። ገዦች ተቀምጠው ቢዶልቱብኝ እንኳ፣ አገልጋይህ ሥርዐትህን ያሰላስላል። ምስክርነትህ ለእኔ ደስታዬ ነው፤ መካሪዬም ነው። ነፍሴ ከዐፈር ተጣበቀች፤ እንደ ቃልህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ። ስለ መንገዴ ገልጬ ነገርሁህ፤ አንተም መለስህልኝ፤ ሥርዐትህን አስተምረኝ። የድንጋጌህን መንገድ እንዳስተውል አድርገኝ፤ እኔም ድንቅ ሥራህን አሰላስላለሁ። ነፍሴ በሐዘን ተዝለፈለፈች፤ እንደ ቃልህ አበርታኝ። የሽንገላን መንገድ ከእኔ አርቅ፤ ሕግህን በጸጋህ ስጠኝ። የእውነትን መንገድ መርጫለሁ፤ ሕግህንም ፊት ለፊቴ አድርጌአለሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ከምስክርነትህ ጋራ ተጣብቄአለሁ፤ አሳልፈህ ለውርደት አትስጠኝ። ልቤን አስፍተህልኛልና፣ በትእዛዞችህ መንገድ እሮጣለሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ የሥርዐትህን መንገድ አስተምረኝ፤ እኔም እስከ መጨረሻው እጠብቀዋለሁ። ሕግህን እንድጠብቅ፣ በፍጹም ልቤም እንድታዘዘው፣ ማስተዋልን ስጠኝ። በርሷ ደስ ይለኛልና፣ በትእዛዝህ መንገድ ምራኝ። ከራስ ጥቅም ይልቅ፣ ልቤን ወደ ምስክርነትህ አዘንብል። ከንቱ ነገር ከማየት ዐይኖቼን መልስ፤ በራስህ መንገድ እንደ ገና ሕያው አድርገኝ። ትፈራ ዘንድ፣ ለአገልጋይህ የገባኸውን ቃል ፈጽም። የምፈራውን መዋረድ ከእኔ አርቅ፤ ደንብህ መልካም ነውና። እነሆ፤ ድንጋጌህን ናፈቅሁ፤ በጽድቅህ ሕያው አድርገኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ ወደ እኔ ይምጣ፤ ማዳንህም እንደ ቃልህ ይላክልኝ። በቃልህ ታምኛለሁና፣ ለሚሰድቡኝ መልስ እሰጣለሁ። ሕግህን ተስፋ አድርጌአለሁና፣ የእውነትን ቃል ከአፌ ፈጽመህ አታርቅ። ከዘላለም እስከ ዘላለም፣ ሕግህን ዘወትር እጠብቃለሁ። ሥርዐትህን እሻለሁና፣ እንደ ልቤ ወዲያ ወዲህ እመላለሳለሁ። ምስክርነትህን በነገሥታት ፊት እናገራለሁ፤ ይህን በማድረግም ዕፍረት አይሰማኝም። እኔ እወድደዋለሁና፣ በትእዛዝህ ደስ ይለኛል። እጆቼን ወደምወዳቸው ትእዛዞችህ አነሣለሁ፤ ሥርዐትህንም አሰላስላለሁ። ለአገልጋይህ የገባኸውን ቃል ዐስብ፤ በዚያ ተስፋ ሰጥተኸዋልና። ቃልህ ሕያው ያደርገኛልና፣ ይህች በመከራዬ መጽናኛዬ ናት። እብሪተኞች እጅግ ተሣለቁብኝ፤ እኔ ግን ከሕግህ ንቅንቅ አልልም። እግዚአብሔር ሆይ፤ ከጥንት የነበረውን ድንጋጌህን አሰብሁ፤ በዚህም ተጽናናሁ። ሕግህን ከተዉ ክፉዎች የተነሣ፣ ቍጣ ወረረኝ። በእንግድነቴ አገር፣ ሥርዐትህ መዝሙሬ ናት። እግዚአብሔር ሆይ፤ ስምህን በሌሊት ዐስባለሁ፤ ሕግህንም እጠብቃለሁ። ሥርዐትህን እከተላለሁ፤ ይህችም ተግባሬ ሆነች። እግዚአብሔር ዕድል ፈንታዬ ነው፤ ቃልህን ለመታዘዝ ቈርጫለሁ። በፍጹም ልቤ ፊትህን ፈለግሁ፤ እንደ ቃልህ ቸርነትህን አሳየኝ። መንገዴን ቃኘሁ፤ አካሄዴንም ወደ ምስክርህ አቀናሁ። ትእዛዝህን ለመጠበቅ፣ ቸኰልሁ፤ አልዘገየሁምም። የክፉዎች ገመድ ተተበተበብኝ፤ እኔ ግን ሕግህን አልረሳሁም። ስለ ጻድቅ ሥርዐትህ፣ በእኩለ ሌሊት ላመሰግንህ እነሣለሁ። እኔ ለሚፈሩህ ሁሉ፣ ሥርዐትህንም ለሚጠብቁ ባልንጀራ ነኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ምድር በምሕረትህ ተሞላች፤ ሥርዐትህን አስተምረኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቃልህ፣ ለአገልጋይህ በጎ ውለሃል። በትእዛዞችህ አምናለሁና፣ በጎ ማስተዋልንና ዕውቀትን አስተምረኝ። እንዲያው ሳይቸግረኝ መንገድ ስቼ ሄድሁ፤ አሁን ግን ቃልህን እጠብቃለሁ። አንተ መልካም ነህ፤ የምታደርገው መልካም ነው፤ እንግዲህ ሥርዐትህን አስተምረኝ። እብሪተኞች ስሜን በሐሰት አጠፉ፤ እኔ ግን ትእዛዝህን በፍጹም ልብ እጠብቃለሁ። ልባቸው የሠባና የደነደነ ነው፤ እኔ ግን በሕግህ ደስ ይለኛል። ሥርዐትህን እማር ዘንድ፣ በመከራ ውስጥ ማለፌ መልካም ሆነልኝ። ከአእላፋት ብርና ወርቅ ይልቅ፣ ከአፍህ የሚወጣው ሕግ ይሻለኛል። እጆችህ ሠሩኝ፤ አበጃጁኝም፤ ትእዛዞችህን እንድማር ማስተዋልን ስጠኝ። ቃልህን ተስፋ አድርጌአለሁና፣ የሚፈሩህ እኔን አይተው ደስ ይበላቸው። እግዚአብሔር ሆይ፤ ፍርድህ የጽድቅ ፍርድ፣ ያስጨነቅኸኝም በታማኝነት እንደ ሆነ ዐወቅሁ። ለአገልጋይህ በገባኸው ቃል መሠረት፣ ምሕረትህ ለመጽናናት ትሁነኝ። ሕግህ ደስታዬ ነውና፣ በሕይወት እኖር ዘንድ ቸርነትህ ትምጣልኝ። እብሪተኞች ያለ ምክንያት በደል አድርሰውብኛልና ይፈሩ፤ እኔ ግን ትእዛዞችህን አሰላስላለሁ። አንተን የሚፈሩህ፣ ምስክርነትህንም የሚያውቁ ወደ እኔ ይመለሱ። እኔ እንዳላፍር፣ ልቤ በሥርዐትህ ፍጹም ይሁን። ነፍሴ ማዳንህን እጅግ ናፈቀች፤ ቃልህንም ተስፋ አደርጋለሁ። “መቼ ታጽናናኛለህ?” እያልሁ፣ ዐይኖቼ ቃልህን በመጠባበቅ ደከሙ። ጢስ የጠጣ የወይን አቍማዳ ብመስልም፣ ሥርዐትህን አልረሳሁም። የባሪያህ ዕድሜ ስንት ቢሆን ነው? ታዲያ፣ በሚያሳድዱኝ ላይ የምትፈርደው መቼ ይሆን? በሕግህ መሠረት የማይሄዱ እብሪተኞች ማጥመጃ ጕድጓድ ቈፈሩልኝ። ትእዛዞችህ ሁሉ አስተማማኝ ናቸው፤ ሰዎች ያለ ምክንያት አሳድደውኛልና ርዳኝ። ከምድር ላይ ሊያስወግዱኝ ጥቂት ቀራቸው፤ እኔ ግን ትእዛዞችህን አልተውሁም። እንደ ምሕረትህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ፤ እኔም የአፍህን ምስክርነት እጠብቃለሁ።

መዝሙር 119:1-88 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በአካሄዳቸው ነቀፋ የሌለባቸው፥ በእግዚአብሔር ሕግ መሠረት የሚኖሩ ሰዎች የተባረኩ ናቸው። ትእዛዞቹን የሚጠብቁ፥ በሙሉ ልባቸውም የሚፈልጉት፥ የተባረኩ ናቸው። የማይሳሳቱና በእግዚአብሔር መንገድ የሚሄዱ የተባረኩ ናቸው። እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ሕጎችህን ሰጥተኸናል፤ በታማኝነት እንድንታዘዛቸውም ነግረኸናል፤ ድንጋጌህን በመጠበቅ ታማኝ ለመሆን በብርቱ እመኛለሁ። ትእዛዞችህን ሁሉ በጥንቃቄ ከአስተዋልኩ ኀፍረት ከቶ አይደርስብኝም። የሕግህን ፍጹምነት ባወቅሁ መጠን በንጹሕ ልብ አመሰግንሃለሁ። ሕግህን ስለምፈጽም ፈጽሞ አትተወኝ። ወጣቶች ሕይወታቸውን በንጽሕና መጠበቅ የሚችሉት ትእዛዞችህን በመፈጸም ነው። አንተን በሙሉ ልቤ ስለምፈልግህ ትእዛዞችህን እንዳላፈርስ ጠብቀኝ። አንተን እንዳልበድል ቃልህን በልቤ አኖራለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! አመሰግንሃለሁ፤ የአንተን ሕግ አስተምረኝ። አንተ የሰጠኸውን ሕግ ሁሉ መላልሼ አነባለሁ። የአንተን ትእዛዝ መፈጸም ብዙ ሀብት የማግኘትን ያኽል ያስደስተኛል። ሥርዓትህን አጠናለሁ፤ በምትመራኝ መንገድ ላይም አተኲራለሁ። በሕግህ ደስ ይለኛል፤ ቃልህንም አልረሳም። በሕይወት እንድኖርና የቃልህን ትምህርት እንድጠብቅ ለእኔ ለአገልጋይህ መልካም ነገር አድርግልኝ። በሕግህ ውስጥ ያለውን አስደናቂ እውነት ማየት እንድችል ዐይኖቼን ክፈትልኝ። እኔ በምድር ላይ በእንግድነት የምኖረው ለጥቂት ጊዜ ነው፤ ስለዚህ ትእዛዞችህን አትሰውርብኝ። ነፍሴ ሥርዓትህን ለማግኘት ሁልጊዜ በመናፈቅ ተጨነቀች። የተረገሙትንና ከትእዛዞችህ የሚያፈነግጡትን ትዕቢተኞች ትገሥጻለህ። እኔ ሕግህን ስለ ጠበቅሁ ስድባቸውንና ንቀታቸውን ከእኔ አርቅልኝ። መሪዎች ተሰብስበው በእኔ ላይ ቢዶልቱም እንኳ እኔ አገልጋይህ ግን ሕግህን አሰላስላለሁ። ትእዛዞችህ ያስደስቱኛል፤ መካሪዎቼም እነርሱ ናቸው። ተሸንፌ ትቢያ ላይ ወድቄአለሁ፤ በሰጠኸኝ የተስፋ ቃል መሠረት ሕይወቴን አድስልኝ። አድራጎቴን ሁሉ ተናዘዝኩ፤ አንተም ሰማኸኝ፤ እንግዲህ ሕግህን አስተምረኝ። ሕግህን እንዳስተውል እርዳኝ፤ እኔም ድንቅ ሥራህን አሰላስላለሁ። ሐዘን በርትቶብኛል፤ በሰጠኸኝ የተስፋ ቃል መሠረት ኀይሌን አድስልኝ። ሐሰትን ከእኔ አርቅልኝ፤ በቸርነትህም ሕግህን አስተምረኝ። ታማኝ ለመሆንና ሕግህን ለመጠበቅ ወስኜአለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! በሕግህ ጸንቼአለሁ፤ እባክህ አታሳፍረኝ። ብዙ ማስተዋልን ስለ ሰጠኸኝ፤ ትእዛዞችህን በትጋት እፈጽማለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! የሕግህን ትርጒም አስተምረኝ፤ እኔም ዘወትር እከተለዋለሁ። ሕግህን ግለጥልኝ፤ እኔም አከብረዋለሁ፤ በሙሉ ልቤም እጠብቀዋለሁ። ትእዛዞችህ ስለሚያስደስቱኝ እንድፈጽማቸው እርዳኝ። ሀብት ለማግኘት ከመስገብገብ ይልቅ ሕግህን የመፈጸም ፍላጎት እንዲኖረኝ አድርግ። ወደ ከንቱ ነገር ከማዘንበል ጠብቀኝ፤ በቃልህ መሠረት ሕይወቴን አድስልኝ። ለእኔ ለአገልጋይህና ለሚፈሩህ ሁሉ የሰጠኸውን የተስፋ ቃል ፈጽም። ፍርድህ ትክክል ስለ ሆነ ከምፈራው ውርደት ጠብቀኝ። ትእዛዞችህን መጠበቅ እመኛለሁ፤ አንተ እውነተኛ ስለ ሆንክ ሕይወቴን አድስልኝ። እግዚአብሔር ሆይ! ዘለዓለማዊ ፍቅርህ ወደ እኔ ይድረስ፤ በተስፋ ቃልህም መሠረት አድነኝ። በቃልህ ስለምተማመን ለሚሰድቡኝ ሁሉ መልስ መስጠት እችላለሁ። ተስፋ የማደርገው የአንተን ፍርድ ስለ ሆነ ዘወትር እውነት እንድናገር እርዳኝ። ሕግህን ባለማቋረጥ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም እፈጽማለሁ። ትእዛዝህን መፈጸም ስለምወድ በፍጹም ነጻነት እኖራለሁ። ትእዛዞችህን በነገሥታት ፊት እናገራለሁ፤ ከቶም አላፍርም። በትእዛዞችህ የምደሰተው እነርሱን ስለምወዳቸው ነው። የምወዳቸውን ትእዛዞችህን አከብራለሁ፤ ስለ ሥርዓትህም በተመስጦ አሰላስላለሁ። ተስፋ የማደርገው በእርሱ ላይ ስለ ሆነ ለእኔ ለአገልጋይህ የሰጠኸውን የተስፋ ቃል አስብ። የተስፋ ቃልህ ሕይወቴን ስላደሰልኝ፥ በመከራዬ ጊዜ እንኳ እጽናናለሁ። ትዕቢተኞች ዘወትር ያፌዙብኛል፤ እኔ ግን ከትእዛዞችህ አልርቅም። እግዚአብሔር ሆይ! መጽናናትን የሚሰጠኝ ስለ ሆነ ከጥንት ጀምሮ የነበረውን ሕግህን አስታውሳለሁ። ክፉ ሰዎች ሕግህን ሲተላለፉ በማየቴ በብርቱ ተቈጣሁ። በምኖርበት ቦታ ሁሉ ሕጎችህ የመዝሙሬ አዝማቾች ናቸው። እግዚአብሔር ሆይ! በሌሊት ስምህን አስታውሳለሁ፤ በሕግህም ጸንቼ እኖራለሁ። ትእዛዞችህን ዘወትር ስለማከብር፥ በረከትን አገኘሁ። እግዚአብሔር ሆይ! እኔ የምፈልገው አንተን ብቻ ነው፤ ሕግህንም ለመጠበቅ ቃል እገባለሁ። በተስፋ ቃልህ መሠረት ምሕረት እንድታደርግልኝ ከልብ እለምንሃለሁ። አካሄዴን መርምሬ የተረዳሁት ስለ ሆነ ሥርዓትህን ለመከተል ቃል እገባለሁ። ያለ ማመንታት ትእዛዞችህን ለመፈጸም እተጋለሁ። ክፉዎች ወጥመድ ቢዘረጉብኝም እኔ ግን ሕግህን አልረሳም። ስለ ትክክለኛ ፍርድህ አንተን ለማመስገን በእኩለ ሌሊት እነሣለሁ። አንተን የሚፈሩትንና ሕግህን የሚያከብሩትን ሁሉ እወዳቸዋለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! ምድር በዘለዓለማዊው ፍቅርህ የተሞላች ናት፤ ሕጎችህን አስተምረኝ። እግዚአብሔር ሆይ! የተስፋ ቃልህን ጠብቀሃል፤ ለእኔም ለአገልጋይህ ቸር ሆነሃል። በትእዛዞችህ ስለምተማመን አስተዋይነትንና ዕውቀትን ስጠኝ። አንተ እኔን ከመቅጣትህ በፊት እሳሳት ነበር፤ አሁን ግን ለቃልህ እታዘዛለሁ። አንተ ቸር ስለ ሆንክ ቸር የሆነውን ታደርጋለህ፤ ሕጎችህን አስተምረኝ። ምንም እንኳ ትዕቢተኞች በሐሰት ስሜን ቢያጠፉ እኔ ትእዛዞችህን በሙሉ ልቤ እጠብቃለሁ። እነርሱ ትዕቢተኞችና ስሜተ ቢሶች ናቸው፤ እኔ ግን በሕግህ ደስ ይለኛል። ሕግህን እንድማር ስላደረገኝ መቀጣቴ መልካም ሆነልኝ። ከብዙ ወርቅና ከብዙ ብር ይልቅ ለእኔ እጅግ ዋጋ ያለው አንተ የምትሰጠው ሕግ ነው። እጆችህ ሠሩኝ፤ አበጃጁኝም፤ ትእዛዞችህን እማር ዘንድ አስተዋይነትን ስጠኝ። በተስፋ ቃልህ ስለምታመን አንተን የሚያከብሩ ሁሉ እኔን በሚያዩበት ጊዜ ደስ ይበላቸው። እግዚአብሔር ሆይ! ፍርድህ እውነተኛ እንደ ሆነ ዐውቃለሁ፤ የቀጣኸኝም እውነተኛ በመሆንህ ነው። ለእኔ ለአገልጋይህ በሰጠኸው የተስፋ ቃል መሠረት ዘለዓለማዊው ፍቅርህ ያጽናናኝ። በሕግህ ደስ ስለሚለኝ ሕያው ሆኜ ለመኖር እችል ዘንድ ርኅራኄ አድርግልኝ። በሐሰት ያለምክንያት የሚከሱኝ ትዕቢተኞች ይዋረዱ፤ እኔ ግን ሕግህን አሰላስላለሁ። አንተን የሚፈሩ ትእዛዞችህን ያውቁ ዘንድ ወደ እኔ ይምጡ። ኀፍረት እንዳይደርስብኝ ሕግህን በትክክል እንድፈጽም እርዳኝ። የአንተን አዳኝነት በሙሉ ልቤ እመኛለሁ። እምነቴን በቃልህ ላይ አድርጌአለሁ። “መቼ ታጽናናኝ ይሆን?” ብዬ የተስፋ ቃልህን በመጠባበቅ ዐይኖቼ ደከሙ። ጢስ በሚጤስበት ቤት ተሰቅሎ እንደ ተጨማደደ የወይን ጠጅ አቊማዳ ከጥቅም ውጪ ሆኜአለሁ፤ ይህም ሁሉ ሆኖ ሕግህን አልረሳሁም። እኔ አገልጋይህ እስከ መቼ ልቈይ? የሚያሳድዱኝንስ የምትቀጣቸው መቼ ነው? ሕግህን የማይጠብቁ ትዕቢተኞች እኔን ለማጥመድ ጒድጓድ ቆፍረዋል። ትእዛዞችህ ሁሉ የጸኑ ናቸው፤ ያለ ምክንያት ስለሚያሳድዱኝ እርዳኝ! እነርሱ ሊገድሉኝ ጥቂት ቀርቶአቸው ነበር፤ እኔ ግን ትእዛዞችህን ችላ አላልኩም። ሕግህን እጠብቅ ዘንድ በዘለዓለማዊ ፍቅርህ ሕይወትን ስጠኝ።

መዝሙር 119:1-88 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በመንገዳቸው እንከን የሌለባቸው፥ በጌታም ሕግ የሚመላለሱ ምስጉኖች ናቸው። ሕጉን የሚጠብቁ፥ በፍጹም ልብ የሚሹት ምስጉኖች ናቸው፥ ዓመፅንም አያደርጉም፥ በመንገዶቹም ይሄዳሉ። ሕጎችህን በሚገባ እንጠብቅ ዘንድ አንተ አዘዝህ። ደንቦችህን ለመጠበቅ መንገዶቼ ምነው በቀኑ። ትእዛዞችህንም ሁሉ ስመለከት በዚያን ጊዜ አላፍርምና። አቤቱ፥ ትክክለኛ ፍርድህን ስማር በቅን ልብ አመሰግንሃለሁ። ሥርዓትህን እጠብቃለሁ፥ በፍጹም አትጣለኝ። ጎልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው። በፍጹም ልቤ ፈለግሁህ፥ ከትእዛዝህ አታርቀኝ። አንተን እንዳልበድል፥ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ። አቤቱ፥ አንተ ቡሩክ ነህ፥ ደንቦችህን አስተምረኝ። ከአፍህ የሚወጡትን ፍርዶች ሁሉ በከንፈሮቼ ደገምኳቸው። በብልጽግና እንደሚደሰቱ ሁሉ በሕጎችህ መንገድ ደስ አለኝ። ደንቦችህን አሰላስላለሁ፥ መንገዶችህንም እመለከታለሁ። በድንጋጌዎችህ ደስ ይለኛል፥ ቃልህንም አልረሳም። ለአገስልጋይህ መልካም አድርግለት፤ ሕያው እንድሆን፥ ቃልህንም እንድጠብቅ። ዐይኖቼን ክፈት፥ ከሕግህም ተኣምራትህን አያለሁ። እኔ በምድር እንግዳ ነኝ፥ ትእዛዛትህን ከእኔ አትሰውር። ፍርዶችህን ሁልጊዜ በመፈለግ ነፍሴ በናፍቆት ደቀቀች። ከትእዛዛትህ የሚያፈነግጡተን ትዕቢተኞችንና ርጉማንን ገሠጽህ። ሕግህን ጠብቄአለሁና። ስድብንና ነውርን ከእኔ አርቅ። መስፍኖች ደግሞ ተቀምጠው እኔን አሙኝ፥ አገልጋይህ ግን ሕግህን ያሰላስል ነበር። ሕግህም ተድላዬ ነው፥ ደንቦችህም አማካሪዎቼ ናቸው። ነፍሴ ወደ አፈር ተጠጋች፥ እንደ ቃልህ ሕያው አድርገኝ። መንገዶቼን ዘረዘርሁ፥ ሰማኸኝም፥ ደንቦችህን አስተምረኝ። የድንጋጌዎችህን መንገድ እንዳስተውል አድርገኝ፥ ተኣምራትህንም አሰላስላለሁ። ከኀዘን የተነሣ ነፍሴ በዕንባ ተዋጠች፥ እንደ ቃልህ አጠንክረኝ። የሐሰትን መንገድ ከእኔ አርቅ፥ የሕግህንም ጸጋ ስጠኝ፥ የእውነትህን መንገድ መረጥሁ፥ ፍርድህንም አልረሳሁም። አቤቱ፥ ሕግህን ተጠጋሁ፥ አታሳፍረኝ። ልቤን ባሰፋኸው ጊዜ፥ በትእዛዞችህ መንገድ ሮጥሁ። አቤቱ፥ የደንቦችህን መንገድ አስተምረኝ፥ ለትሩፋትም እጠብቀዋለሁ። እንዳስተውል አድርገኝ፥ ሕግህንም እንድጠብቅ፥ በፍጹም ልቤም እጠብቀዋለሁ። እርሷን ወድጃለሁና የትእዛዝህን መንገድ ምራኝ። ልቤን ወደ ምስክርህ አዘንብል፥ ወደ ስስትም አይሁን። ከንቱ ነገርን እንዳያዩ ዐይኖቼን መልስ፥ በመንገድህ ሕያው አድርገኝ። እንዲፈራህ ባርያህን በቃልህ አጽና። ፍርድህ መልካም ናትና የምፈራውን ስድብ ከእኔ አርቅ። እነሆ፥ ትእዛዝህን ናፈቅሁ፥ በጽድቅህ ሕያው አድርገኝ። አቤቱ፥ እንደ ቃልህ፥ ምሕረትህና መድኃኒትህ ይምጡልኝ። በቃልህ ታምኛለሁና ለሚሰድቡኝ በነገር እመልስላቸዋለሁ። በፍርድህም ታምኛለሁና የእውነትን ቃል ከአፌ ፈጽመህ አታርቅ። ለዘለዓለም ዓለም ሁልጊዜ ሕግህን እጠብቃለሁ። ትእዛዛትህንም ፈልጌአለሁና አስፍቼ እሄዳለሁ። በነገሥታት ፊት ምስክርህን እናገራለሁ፥ አላፍርምም፥ እጅግም በወደድኋቸው በትእዛዛትህ ደስ ይለኛል። እጆቼንም ወደ ወደድኋቸው ወደ ትእዛዛትህ አነሣለሁ፥ ሥርዓትህንም አሰላስላለሁ። ለባርያህ የሰጠኸውን የተስፋ ቃልህን አስብ። ቃልህ ሕያው አድርጎኛልና ይህች በመከራዬ ደስ አሰኘችኝ። ትዕቢተኞች እጅግ ዐመፁ፥ እኔ ግን ከሕግህ አልራቅሁም። ከጥንት የነበረውን ፍርድህን አሰብሁ፥ አቤቱ፥ ተጽናናሁም። ሕግህን ከተዉ ከኃጢአተኞች የተነሣ ኀዘን ያዘኝ። በእንግድነቴ አገር ሥርዓትህ መዝሙር ሆነችኝ። አቤቱ፥ በሌሊት ስምህን አሰብሁ፥ ሕግህንም ጠበቅሁ። ትእዛዛትህንም ፈልጌአለሁና ይህች ሆነችልኝ። ጌታ ድርሻዬ ነው፥ ቃልህን እጠብቃለሁ አልሁ። በፍጹም ልቤ ወደ ፊትህ ተማለልሁ፥ እንደ ቃልህ ማረኝ። ስለ መንገዶችህ አሰብሁ፥ እግሬንም ወደ ምስክሮችህ መለስሁ። ትእዛዝህን ለመጠበቅ ጨከንሁ አልዘገየሁምም። የኀጥኣን ገመዶች ተተበተቡብኝ፥ ሕግህን ግን አልረሳሁም። ስለ ጽድቅህ ፍርድ፥ በእኩለ ሌሊት አመሰግንህ ዘንድ እነሣለሁ። እኔ ለሚፈሩህ ሁሉ፥ ትእዛዝህንም ለሚጠብቁ ባልንጀራ ነኝ። አቤቱ፥ ምሕረትህ በምድር ሁሉ ሞላች፥ ሥርዓትህን አስተምረኝ። አቤቱ፥ እንደ ቃልህ ለባርያህ መልካም አደረግህ። በትእዛዛትህ ታምኛለሁና መልካም ምክርና እውቀትን አስተምረኝ። በፊት ስቼ ከመንገድህ ርቄ ነበር፥ አሁን ግን ቃልህን ጠበቅሁ። አቤቱ፥ አንተ ቸር ነህ፥ በቸርነትህም ሥርዓትህን አስተምረኝ። የትዕቢተኞች ዓመጽ በላዬ በዛ፥ እኔ ግን በፍጹም ልቤ ትእዛዛትህን እፈልጋለሁ። ልባቸው እንደ ወተት ረጋ፥ እኔ ግን በሕግህ ደስ ይለኛል። ሥርዓትህን እማር ዘንድ ያስጨነቅኸኝ መልካም ሆነልኝ። ከአእላፋት ወርቅና ብር ይልቅ የአፍህ ሕግ ይሻለኛል። ዮድ። እጆችህ ሠሩኝ አበጃጁኝም፥ እንዳስተውል አድርገኝ፥ ትእዛዛትህንም እማራለሁ። በቃልህ ታምኛለሁና የሚፈሩህ እኔን አይተው ደስ ይላቸዋል። አቤቱ፥ ፍርድህ ጽድቅ እንደ ሆነች፥ በእውነትህም እንዳስቸገርኸኝ አወቅሁ። ምሕረትህ ለመጽናናቴ ትሁነኝ፥ እንደ ቃልህም ለባርያህ ይሁነው። ሕግህ ተድላዬ ናትና ቸርነትህ ትምጣልኝ፥ በሕይወትም ልኑር። ትዕቢተኞች በዓመፅ ጠምመውብኛልና ይፈሩ፥ እኔ ግን ትእዛዝህን አሰላስላለሁ። የሚፈሩህና ምስክሮችህን የሚያውቁ ወደ እኔ ይመለሱ። እንዳላፍር ልቤ በሥርዓትህ የቀና ይሁን። ነፍሴ መድኃኒትህን ናፈቀች፥ በቃልህም ታመንሁ። መቼ ታጽናናኛለህ እያልሁ ዐይኖቼ ስለ ቃልህ ፈዘዙ። በጢስ ውስጥ እንዳለ አቁማዳ ሆኛለሁና፥ ሥርዓትህን ግን አልረሳሁም። የባርያህ ዘመኖች ስንት ናቸው? በሚያሳድዱኝስ ላይ መቼ ትፈርድልኛለህ? ኃጢአተኞች ጉድጓድ ቆፈሩልኝ፥ አቤቱ፥ እንደ ሕግህ ግን አይደለም። ትእዛዛትህ ሁሉ እውነት ናቸው፥ በዓመፅ አሳድደውኛል፥ እርዳኝ። ከምድር ሊያጠፉኝ ጥቂት ቀርቶአቸው ነበር፥ እኔ ግን ትእዛዛትህን አልተውሁም። እንደ ምሕረትህ ሕያው አድርገኝ፥ የአፍህንም ምስክር እጠብቃለሁ።

መዝሙር 119:1-88

መዝሙር 119:1-88 NASVመዝሙር 119:1-88 NASVመዝሙር 119:1-88 NASV