መዝሙረ ዳዊት 119:1-88

መዝሙረ ዳዊት 119:1-88 መቅካእኤ

በመንገዳቸው እንከን የሌለባቸው፥ በጌታም ሕግ የሚመላለሱ ምስጉኖች ናቸው። ሕጉን የሚጠብቁ፥ በፍጹም ልብ የሚሹት ምስጉኖች ናቸው፥ ዓመፅንም አያደርጉም፥ በመንገዶቹም ይሄዳሉ። ሕጎችህን በሚገባ እንጠብቅ ዘንድ አንተ አዘዝህ። ደንቦችህን ለመጠበቅ መንገዶቼ ምነው በቀኑ። ትእዛዞችህንም ሁሉ ስመለከት በዚያን ጊዜ አላፍርምና። አቤቱ፥ ትክክለኛ ፍርድህን ስማር በቅን ልብ አመሰግንሃለሁ። ሥርዓትህን እጠብቃለሁ፥ በፍጹም አትጣለኝ። ጎልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው። በፍጹም ልቤ ፈለግሁህ፥ ከትእዛዝህ አታርቀኝ። አንተን እንዳልበድል፥ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ። አቤቱ፥ አንተ ቡሩክ ነህ፥ ደንቦችህን አስተምረኝ። ከአፍህ የሚወጡትን ፍርዶች ሁሉ በከንፈሮቼ ደገምኳቸው። በብልጽግና እንደሚደሰቱ ሁሉ በሕጎችህ መንገድ ደስ አለኝ። ደንቦችህን አሰላስላለሁ፥ መንገዶችህንም እመለከታለሁ። በድንጋጌዎችህ ደስ ይለኛል፥ ቃልህንም አልረሳም። ለአገስልጋይህ መልካም አድርግለት፤ ሕያው እንድሆን፥ ቃልህንም እንድጠብቅ። ዐይኖቼን ክፈት፥ ከሕግህም ተኣምራትህን አያለሁ። እኔ በምድር እንግዳ ነኝ፥ ትእዛዛትህን ከእኔ አትሰውር። ፍርዶችህን ሁልጊዜ በመፈለግ ነፍሴ በናፍቆት ደቀቀች። ከትእዛዛትህ የሚያፈነግጡተን ትዕቢተኞችንና ርጉማንን ገሠጽህ። ሕግህን ጠብቄአለሁና። ስድብንና ነውርን ከእኔ አርቅ። መስፍኖች ደግሞ ተቀምጠው እኔን አሙኝ፥ አገልጋይህ ግን ሕግህን ያሰላስል ነበር። ሕግህም ተድላዬ ነው፥ ደንቦችህም አማካሪዎቼ ናቸው። ነፍሴ ወደ አፈር ተጠጋች፥ እንደ ቃልህ ሕያው አድርገኝ። መንገዶቼን ዘረዘርሁ፥ ሰማኸኝም፥ ደንቦችህን አስተምረኝ። የድንጋጌዎችህን መንገድ እንዳስተውል አድርገኝ፥ ተኣምራትህንም አሰላስላለሁ። ከኀዘን የተነሣ ነፍሴ በዕንባ ተዋጠች፥ እንደ ቃልህ አጠንክረኝ። የሐሰትን መንገድ ከእኔ አርቅ፥ የሕግህንም ጸጋ ስጠኝ፥ የእውነትህን መንገድ መረጥሁ፥ ፍርድህንም አልረሳሁም። አቤቱ፥ ሕግህን ተጠጋሁ፥ አታሳፍረኝ። ልቤን ባሰፋኸው ጊዜ፥ በትእዛዞችህ መንገድ ሮጥሁ። አቤቱ፥ የደንቦችህን መንገድ አስተምረኝ፥ ለትሩፋትም እጠብቀዋለሁ። እንዳስተውል አድርገኝ፥ ሕግህንም እንድጠብቅ፥ በፍጹም ልቤም እጠብቀዋለሁ። እርሷን ወድጃለሁና የትእዛዝህን መንገድ ምራኝ። ልቤን ወደ ምስክርህ አዘንብል፥ ወደ ስስትም አይሁን። ከንቱ ነገርን እንዳያዩ ዐይኖቼን መልስ፥ በመንገድህ ሕያው አድርገኝ። እንዲፈራህ ባርያህን በቃልህ አጽና። ፍርድህ መልካም ናትና የምፈራውን ስድብ ከእኔ አርቅ። እነሆ፥ ትእዛዝህን ናፈቅሁ፥ በጽድቅህ ሕያው አድርገኝ። አቤቱ፥ እንደ ቃልህ፥ ምሕረትህና መድኃኒትህ ይምጡልኝ። በቃልህ ታምኛለሁና ለሚሰድቡኝ በነገር እመልስላቸዋለሁ። በፍርድህም ታምኛለሁና የእውነትን ቃል ከአፌ ፈጽመህ አታርቅ። ለዘለዓለም ዓለም ሁልጊዜ ሕግህን እጠብቃለሁ። ትእዛዛትህንም ፈልጌአለሁና አስፍቼ እሄዳለሁ። በነገሥታት ፊት ምስክርህን እናገራለሁ፥ አላፍርምም፥ እጅግም በወደድኋቸው በትእዛዛትህ ደስ ይለኛል። እጆቼንም ወደ ወደድኋቸው ወደ ትእዛዛትህ አነሣለሁ፥ ሥርዓትህንም አሰላስላለሁ። ለባርያህ የሰጠኸውን የተስፋ ቃልህን አስብ። ቃልህ ሕያው አድርጎኛልና ይህች በመከራዬ ደስ አሰኘችኝ። ትዕቢተኞች እጅግ ዐመፁ፥ እኔ ግን ከሕግህ አልራቅሁም። ከጥንት የነበረውን ፍርድህን አሰብሁ፥ አቤቱ፥ ተጽናናሁም። ሕግህን ከተዉ ከኃጢአተኞች የተነሣ ኀዘን ያዘኝ። በእንግድነቴ አገር ሥርዓትህ መዝሙር ሆነችኝ። አቤቱ፥ በሌሊት ስምህን አሰብሁ፥ ሕግህንም ጠበቅሁ። ትእዛዛትህንም ፈልጌአለሁና ይህች ሆነችልኝ። ጌታ ድርሻዬ ነው፥ ቃልህን እጠብቃለሁ አልሁ። በፍጹም ልቤ ወደ ፊትህ ተማለልሁ፥ እንደ ቃልህ ማረኝ። ስለ መንገዶችህ አሰብሁ፥ እግሬንም ወደ ምስክሮችህ መለስሁ። ትእዛዝህን ለመጠበቅ ጨከንሁ አልዘገየሁምም። የኀጥኣን ገመዶች ተተበተቡብኝ፥ ሕግህን ግን አልረሳሁም። ስለ ጽድቅህ ፍርድ፥ በእኩለ ሌሊት አመሰግንህ ዘንድ እነሣለሁ። እኔ ለሚፈሩህ ሁሉ፥ ትእዛዝህንም ለሚጠብቁ ባልንጀራ ነኝ። አቤቱ፥ ምሕረትህ በምድር ሁሉ ሞላች፥ ሥርዓትህን አስተምረኝ። አቤቱ፥ እንደ ቃልህ ለባርያህ መልካም አደረግህ። በትእዛዛትህ ታምኛለሁና መልካም ምክርና እውቀትን አስተምረኝ። በፊት ስቼ ከመንገድህ ርቄ ነበር፥ አሁን ግን ቃልህን ጠበቅሁ። አቤቱ፥ አንተ ቸር ነህ፥ በቸርነትህም ሥርዓትህን አስተምረኝ። የትዕቢተኞች ዓመጽ በላዬ በዛ፥ እኔ ግን በፍጹም ልቤ ትእዛዛትህን እፈልጋለሁ። ልባቸው እንደ ወተት ረጋ፥ እኔ ግን በሕግህ ደስ ይለኛል። ሥርዓትህን እማር ዘንድ ያስጨነቅኸኝ መልካም ሆነልኝ። ከአእላፋት ወርቅና ብር ይልቅ የአፍህ ሕግ ይሻለኛል። ዮድ። እጆችህ ሠሩኝ አበጃጁኝም፥ እንዳስተውል አድርገኝ፥ ትእዛዛትህንም እማራለሁ። በቃልህ ታምኛለሁና የሚፈሩህ እኔን አይተው ደስ ይላቸዋል። አቤቱ፥ ፍርድህ ጽድቅ እንደ ሆነች፥ በእውነትህም እንዳስቸገርኸኝ አወቅሁ። ምሕረትህ ለመጽናናቴ ትሁነኝ፥ እንደ ቃልህም ለባርያህ ይሁነው። ሕግህ ተድላዬ ናትና ቸርነትህ ትምጣልኝ፥ በሕይወትም ልኑር። ትዕቢተኞች በዓመፅ ጠምመውብኛልና ይፈሩ፥ እኔ ግን ትእዛዝህን አሰላስላለሁ። የሚፈሩህና ምስክሮችህን የሚያውቁ ወደ እኔ ይመለሱ። እንዳላፍር ልቤ በሥርዓትህ የቀና ይሁን። ነፍሴ መድኃኒትህን ናፈቀች፥ በቃልህም ታመንሁ። መቼ ታጽናናኛለህ እያልሁ ዐይኖቼ ስለ ቃልህ ፈዘዙ። በጢስ ውስጥ እንዳለ አቁማዳ ሆኛለሁና፥ ሥርዓትህን ግን አልረሳሁም። የባርያህ ዘመኖች ስንት ናቸው? በሚያሳድዱኝስ ላይ መቼ ትፈርድልኛለህ? ኃጢአተኞች ጉድጓድ ቆፈሩልኝ፥ አቤቱ፥ እንደ ሕግህ ግን አይደለም። ትእዛዛትህ ሁሉ እውነት ናቸው፥ በዓመፅ አሳድደውኛል፥ እርዳኝ። ከምድር ሊያጠፉኝ ጥቂት ቀርቶአቸው ነበር፥ እኔ ግን ትእዛዛትህን አልተውሁም። እንደ ምሕረትህ ሕያው አድርገኝ፥ የአፍህንም ምስክር እጠብቃለሁ።