መዝሙር 116:1-9
መዝሙር 116:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ጩኸቴንና ልመናዬን ስለ ሰማ እግዚአብሔርን እወደዋለሁ። እርሱን በምጠራው ጊዜ ሁሉ ስለሚሰማኝ፥ በዘመኔ ሁሉ ወደ እርሱ እጮኻለሁ። የሞት አደጋ ዙሪያዬን ከበበኝ፤ የመቃብር አስፈሪ ሁኔታ አሠቀቀኝ፤ በችግርና በሐዘን ተሸነፍኩ። በዚያን ጊዜ “አምላክ ሆይ! እባክህ አድነኝ!” ብዬ ወደ እግዚአብሔር ጮኽኩ። እግዚአብሔር ቸርና እውነተኛ ነው፤ አምላካችን መሐሪ ነው። እግዚአብሔር የዋሆች የሆኑትን ይጠብቃል፤ እኔ በተቸገርኩ ጊዜ አድኖኛል። እግዚአብሔር መልካም ነገር ስላደረገልኝ፥ ከእንግዲህ ወዲያ አልጨነቅም። እግዚአብሔር ከሞት አዳነኝ፤ እንባዬ እንዲቆም አደረገ፤ እግሮቼንም ከመደናቀፍ ጠበቃቸው። ስለዚህ ሕያዋን በሚገኙበት በእግዚአብሔር ፊት እኖራለሁ።
መዝሙር 116:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የልመናዬን ድምፅ ሰምቷልና፣ እግዚአብሔርን ወደድሁት። ጆሮውን ወደ እኔ አዘንብሏልና፣ በሕይወት ዘመኔ ሁሉ ወደ እርሱ እጣራለሁ። የሞት ወጥመድ ያዘኝ፤ የሲኦልም ጣር አገኘኝ፤ ጭንቅና ሐዘን አሸነፈኝ። እኔም የእግዚአብሔርን ስም ጠራሁ፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ነፍሴን ታድናት ዘንድ እለምንሃለሁ” አልሁ። እግዚአብሔር ቸርና ጻድቅ ነው፤ አምላካችን መሓሪ ነው። እግዚአብሔር አላዋቂዎችን ይጠብቃል፤ እጅግ ተቸግሬ ሳለሁ አዳነኝ። ነፍሴ ሆይ፤ ወደ ዕረፍትሽ ተመለሺ፤ እግዚአብሔር መልካም አድርጎልሻልና። አንተ ነፍሴን ከሞት፣ ዐይኔን ከእንባ፣ እግሮቼን ከመሰናከል አድነሃልና። እኔም በሕያዋን ምድር፣ በእግዚአብሔር ፊት እመላለሳለሁ።
መዝሙር 116:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሃሌ ሉያ! ጌታ የልመናዬን ድምፅ ሰምቶአልና ወደድሁት። ጆሮውን ወደ እኔ አዘንብሏልና በዘመኔ ሁሉ እጠራዋለሁ። የሞት ገመዶች ወጠሩኝ፥ የሲኦልም ሕማም አገኘኝ፥ ጭንቀትንና መከራን አገኘሁ። የጌታን ስም ጠራሁ፦ አቤቱ፥ ነፍሴን አድናት። ጌታ መሓሪና ጻድቅ ነው፥ አምላካችንም ርኅሩኅ ነው። ጌታ የዋሆችን ይጠብቃል፥ ተዋረድሁ፥ እርሱም አዳነኝ። ነፍሴ ሆይ፥ ወደ ዕረፍትሽ ተመለሺ፥ ጌታ መልካም አድርጎልሻልና፥ በእርግጥም ነፍሴን ከሞት፥ ዓይኔንም ከእንባ፥ እግሬንም ከመሰናከል አድነሃል። በሕያዋን አገር በጌታ ፊት እሄዳለሁ።