መዝሙር 105:23-38
መዝሙር 105:23-38 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንዳያጠፋቸው የቍጣውን መቅሠፍት ይመልስ ዘንድ የተመረጠው ሙሴ በመቅሠፍት ጊዜ በፊቱ ባይቆም ኖሮ፥ ባጠፋቸው ነበር አለ። የተወደደችውንም ምድር ናቁ፥ በቃሉም አልታመኑም፥ በድንኳኖቻቸውም ውስጥ አንጐራጐሩ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል አልሰሙም። እጁንም አነሣባቸው። በምድረ በዳ ይጥላቸው ዘንድ፥ ዘራቸውንም በአሕዛብ መካከል ይጥል ዘንድ፥ በየሀገሩም ይበትናቸው ዘንድ። በብዔል ፌጎርም ዐለቁ፥ የሞተ መሥዋዕትንም በሉ፤ በሥራቸውም አነሣሱት ቸነፈርም በላያቸው በዛ። ፊንሐስም ተነሥቶ አዳናቸው፥ ቸነፈሩም ተወ። ያም እስከ ዘለዓለም ለልጅ ልጅ ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት። በክርክር ውኃ ዘንድም አስቈጡት፥ ስለ እነርሱም ሙሴ ተበሳጨ፤ መንፈሱን አስመርረዋታልና፤ በከንፈሮቹም አዘዘ። እግዚአብሔርም እንዳላቸው አሕዛብን አላጠፉም፤ ከአሕዛብ ጋር ተደባለቁ፥ ሥራቸውንም ተማሩ። ለጣዖቶቻቸውም ተገዙ፥ በደልም ሆነባቸው። ወንዶች ልጆቻቸውንና ሴቶች ልጆቻቸውን ለአጋንንት ሠዉ፤ ንጹሕ ደምንም አፈሰሱ፥ የወንዶች ልጆቻቸውንና የሴቶች ልጆቻቸውን ደም፥ ለከነዓን ጣዖቶች ሠዉ፥ ምድርም በደም ታለለች።
መዝሙር 105:23-38 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እስራኤል ወደ ግብጽ ገባ፤ ያዕቆብ በካም ምድር መጻተኛ ሆነ። እግዚአብሔር ሕዝቡን እጅግ አበዛ፤ ከጠላቶቻቸውም ይልቅ አበረታቸው፤ ሕዝቡን እንዲጠሉ፣ በባሪያዎቹም ላይ እንዲያሤሩ ልባቸውን ለወጠ። ባሪያውን ሙሴን፣ የመረጠውንም አሮንን ላከ። እነርሱም ታምራታዊ ምልክቶችን በመካከላቸው፣ ድንቅ ነገሮቹንም በካም ምድር አደረጉ። ጨለማን ልኮ ምድሪቱን ጽልመት አለበሰ፤ እነርሱም በቃሉ ላይ ማመፅን ተዉ። ውሃቸውን ወደ ደም ለወጠ፤ ዓሦቻቸውንም ፈጀ። ምድራቸውም፣ የነገሥታታቸው እልፍኝ ሳይቀር፣ ጓጕንቸር ተርመሰመሰባቸው። እርሱ በተናገረ ጊዜ የዝንብ መንጋ መጣ፤ ትንኞችም ምድራቸውን ወረሩ። ዝናባቸውን በረዶ አደረገው፤ ምድራቸውም ሁሉ መብረቅ አወረደ። ወይናቸውንና በለሳቸውን መታ፤ የአገራቸውንም ዛፍ ከተከተ። እርሱ በተናገረ ጊዜ አንበጣ መጣ፤ ስፍር ቍጥር የሌለውም ኵብኵባ ከተፍ አለ፤ የምድሪቱንም ዕፀዋት ሁሉ በላ፤ የመሬታቸውንም ፍሬ ሙጥጥ አደረገ፤ ደግሞም በአገራቸው ያለውን በኵር ሁሉ፣ የኀይላቸውንም ሁሉ በኵራት መታ። የእስራኤልንም ሕዝብ ብርና ወርቅ ጭኖ እንዲወጣ አደረገ፤ ከነገዶቻቸውም አንድም አልተደናቀፈም። እጅግ ፈርተዋቸው ነበርና፣ ወጥተው ሲሄዱ ግብጽ ደስ አላት።
መዝሙር 105:23-38 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ወደ ግብጽ ሄደ፤ በዚያም አገር ስደተኛ ሆኖ ኖረ። እግዚአብሔር ወገኖቹን አበዛቸው፤ ከጠላቶቻቸውም ይልቅ አበረታቸው። እግዚአብሔር ግን ወገኖቹን እንዲጠሉና፥ በአገልጋዮቹም ላይ በተንኰል እንዲነሡ ግብጻውያንን አስጨከነ። ከዚህ በኋላ አገልጋዩን ሙሴንና የመረጠውን አሮንን ላከ። እነርሱ በግብጽ ምድር የእግዚአብሔርን ድንቅ ነገሮችና ተአምራትን አደረጉ። እግዚአብሔር በአገሩ ላይ ጨለማ እንዲሆን አደረገ፤ ይሁን እንጂ ግብጻውያን ትእዛዞቹን አልፈጸሙም። የወንዞቻቸውንም ውሃ ወደ ደም ለወጠ፤ ዓሣዎቻቸውንም ሁሉ ገደለ። አገራቸው በእንቁራሪት ተሸፈነች፤ ቤተ መንግሥቱ እንኳ ሳይቀር ሁሉ ቦታ በእንቁራሪት ተሞላ። ተናካሽ ዝንቦችና ተናካሽ ትንኞች በአገሩ ሁሉ ላይ እንዲርመሰመሱ አዘዘ። እግዚአብሔር በአገራቸው ላይ በዝናብ ፈንታ የበረዶ ናዳንና መብረቅን አወረደ። የወይን ተክሎቻቸውንና የበለስ ዛፎቻቸውን አጠፋ፤ ሌሎቹንም ዛፎቻቸውን ሁሉ ሰባበረ። እርሱ ባዘዘው መሠረት ሊቈጠር የማይችል የአንበጣና የኲብኲባ መንጋ መጣ። በምድሩ ላይ ያለውን ለምለም ተክልና ሰብል ሁሉ በልተው እንዲጨርሱ አደረገ፤ የእያንዳንዱን ግብጻዊ ቤተሰብ የበኲር ልጅ ገደለ። ከዚህ በኋላ እስራኤላውያንን መርቶ አወጣ፤ ሲወጡም ብርና ወርቅ ይዘው ነበር፤ ከነገዶቻቸውም መካከል ወደ ኋላ የቀረ ማንም አልነበረም። ግብጻውያንም እጅግ ፈርተዋቸው ስለ ነበር፤ በመውጣታቸው ተደሰቱ።
መዝሙር 105:23-38 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እስራኤልም ወደ ግብጽ ገባ፥ ያዕቆብም በካም አገር ተቀመጠ። ሕዝቡንም እጅግ አበዛ፥ ከጠላቶቻቸውም ይልቅ አበረታቸው። ሕዝቡን ይጠሉ ዘንድ በአገልጋዮቹም ላይ ተንኰል ይፈጽሙ ዘንድ ልባቸውን ለወጠ። አገልጋዩን ሙሴን የመረጠውንም አሮንን ላከ። ተኣምራቱን በላያቸው ድንቁንም በካም አገር አደረጉ። ጨለማን ላከ፥ ጨለመባቸውም፥ በቃሉም ዐመፁ። ውኃቸውን ወደ ደም ለወጠ፥ ዓሦቻቸውንም ገደለ። ምድራቸውና የንጉሦቻቸው ቤቶች በእንቁራሪት ተሞሉ። ተናገረ፥ የዝንብ መንጋና ተናካሽ ትንኞች በዳርቻቸው መጡ። ዝናባቸውን በረዶ አደረገው፥ በምድራቸውም የእሳት ነበልባል ወረደ። ወይናቸውንና በለሳቸውን መታ፥ የአገራቸውንም ዛፍ ሁሉ ሰበረ። ተናገረ፥ አንበጣም ስፍር ቍጥር የሌለውም ኩብኩባ መጣ፥ የአገራቸውንም ተክሎች ሁሉ በላ፥ የምድራቸውንም ፍሬ በላ። የአገራቸውንም በኩር ሁሉ፥ የጉልበታቸውን መጀመሪያ ሁሉ መታ። ከወርቅና ከብርም ጋር አወጣቸው፥ በወገናቸውም ውስጥ የተደናቀፈ አልነበረም። ፈርተዋቸው ነበርና ግብጽ በመውጣታቸው ደስ አላት።