መዝሙር 105:1-20
መዝሙር 105:1-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ቸር ነውና፥ ምሕረቱም ለዘለዓለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ። የእግዚአብሔርን ኀይል ማን ይናገራል? ምስጋናውንስ ሁሉ ይሰማ ዘንድ ማን ያደርጋል? ፍርድን የሚጠብቁ፥ ጽድቅንም ሁልጊዜ የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው። አቤቱ፥ ሕዝብህን በይቅርታህ ዐስበን፥ በማዳንህም ይቅር በለን፤ የመረጥሃቸውን በጎነት እናይ ዘንድ፥ በሕዝብህም ደስታ ደስ ይለን ዘንድ፥ ከርስትህም ጋር እንከብር ዘንድ። ከአባቶቻችን ጋር ኃጢአት ሠራን፥ ዐመፅንም፥ በደልንም። አባቶቻችን በግብፅ ሀገር ሳሉ ተአምራትህን አላስተዋሉም፥ የምሕረትህንም ብዛት አላሰቡም፤ በኤርትራ ባሕር ባለፉ ጊዜ አስመረሩህ። ኀይሉን ያሳያቸው ዘንድ ስለ ስሙ አዳናቸው። የኤርትራንም ባሕር ገሠጻት፥ ደረቀችም፤ እንደ ምድረ በዳ በጥልቅ መራቸው። ከጠላቶቻቸውም እጅ አዳናቸው፥ ከጠላቶቻቸውም እጅ ተቤዣቸው። ያሳደዱአቸውንም ውኃ ደፈናቸው፥ ከእነርሱም አንድ ስንኳ አልቀረም። ያንጊዜም በቃሉ አመኑ፥ በምስጋናውም አመሰገኑት። ፈጥነውም ሥራውን ረሱ፥ በምክሩም አልጸኑም። በምድረ በዳም ምኞትን ተመኙ፥ በበረሃም እግዚአብሔርን አሳዘኑት። የለመኑትንም ሰጣቸው፤ ለነፍሳችውም ጥጋብን ላከ። ሙሴንም፥ እግዚአብሔር የቀደሰውን አሮንንም በሰፈር አስቈጧቸው። ምድር ተከፈተች፥ ዳታንንም ዋጠችው፥ የአቤሮንንም ወገን ደፈነች፤ በማኅበራቸው እሳት ነደደች፥ ነበልባልም ኃጥኣንን አቃጠላቸው። በኮሬብም ጥጃን ሠሩ፥ ቀልጦ ለተሠራ ምስልም ሰገዱ። ሣርንም በሚበላ በበሬ ምሳሌ ክብራቸውን ለወጡ።
መዝሙር 105:1-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ስሙንም ጥሩ፤ ሥራውንም በሕዝቦች መካከል ግለጡ። ተቀኙለት፤ ዘምሩለት፤ ድንቅ ሥራዎቹንም ሁሉ ተናገሩ። በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ፤ እግዚአብሔርን የሚሹት ልባቸው ደስ ይበለው። እግዚአብሔርንና ብርታቱን ፈልጉ፤ ፊቱንም ዘወትር ፈልጉ። ያደረጋቸውን ድንቅ ሥራዎች፣ ታምራቱንና ከአፉ የወጣውን ፍርድ አስቡ፤ እናንተ የአገልጋዩ የአብርሃም ዘሮች፣ ለራሱም የመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፤ አስታውሱ። እርሱ እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤ ፍርዱም በምድር ሁሉ ላይ ነው። ኪዳኑን ለዘላለም፣ ያዘዘውንም ቃል እስከ ሺሕ ትውልድ ያስታውሳል። ከአብርሃም ጋር ያደረገውን ኪዳን፣ ለይስሐቅም በመሐላ የተሰጠውን ተስፋ አይረሳም። ይህንም ለያዕቆብ ሥርዐት አድርጎ፣ ለእስራኤልም የዘላለም ኪዳን አድርጎ አጸናለት፤ እንዲህም አለ፤ “የርስትህ ድርሻ አድርጌ፣ የከነዓንን ምድር እሰጥሃለሁ።” በቍጥር አነስተኞች ሆነው ሳሉ፣ እጅግ ጥቂትና ባይተዋሮች ሳሉ፣ ከሕዝብ ወደ ሕዝብ ሲንከራተቱ፣ ከአንዱ መንግሥት ወደ ሌላው ሲቅበዘበዙ፣ ማንም ግፍ እንዲፈጽምባቸው አልፈቀደም፤ ስለ እነርሱም ነገሥታትን እንዲህ ሲል ገሠጸ፤ “የቀባኋቸውን አትንኩ፤ በነቢያቴም ላይ ክፉ አታድርጉ።” በምድሪቱ ላይ ራብን ጠራ፤ የምግብንም አቅርቦት ሁሉ አቋረጠ፤ በባርነት የተሸጠውን ሰው፣ ዮሴፍን ከእነርሱ አስቀድሞ ላከ። እግሮቹ በእግር ብረት ተላላጡ፤ በዐንገቱም የብረት ማነቆ ገባ። የተናገረው ቃል እስኪፈጸምለት፣ የእግዚአብሔር ቃል ፈተነው። ንጉሥ ልኮ አስፈታው፤ የሕዝቦችም ገዥ ነጻ አወጣው።
መዝሙር 105:1-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ስሙንም ጥሩ ያደረገውንም ሁሉ ለአሕዛብ ንገሩ። ለእግዚአብሔር የምስጋና መዝሙር ዘምሩ፤ ያደረገውንም አስደናቂ ነገር ሁሉ ተናገሩ። በቅዱስ ስሙ ደስ ይበላችሁ! እግዚአብሔርን የሚፈልግ ሰው ሁሉ ሐሴት ያድርግ! በእግዚአብሔርና በኀያል ሥልጣኑ ተማመኑ፤ ዘወትርም እርሱን ፈልጉ። አገልጋዮች የሆናችሁ የእስራኤል ልጆች ሆይ! የእግዚአብሔር ምርጥ የሆናችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ! እግዚአብሔር ያደረጋቸውን ድንቅ ነገሮች፥ የሰጠውን ፍርድና ያደረጋቸውን ተአምራት አስታውሱ። እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤ ፍርዱም በዓለም ሁሉ ነው። ቃል ኪዳኑን ወይም የሰጠውን ተስፋ እስከ ሺህ ትውልድም ሆነ ለዘለዓለም አይረሳም። ከአብርሃም ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ይጠብቃል፤ ለይስሐቅ የሰጠውን የተስፋ ቃል ያጸናል። ለያዕቆብ ሥርዓት፥ ለእስራኤልም ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን አድርጎ አጸናው። ይህም ቃል ኪዳን “የከነዓንን ምድር እሰጥሃለሁ፤ ለአንተም የተመደበ ርስት ይሆናል” የሚል ነው። ይህም የሆነው እነርሱ በቊጥር አነስተኞች ለሀገሩም እንግዶች ሆነው ሳለ ነው። ከአንዱ ሕዝብ ወደ ሌላ ሕዝብ፥ ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር ተንከራተቱ። እግዚአብሔር ግን ማንም እንዲጨቊናቸው አልፈቀደም፤ ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ። “የተመረጡ አገልጋዮቼን አትንኩ፤ ነቢያቴንም አትጒዱ” በማለት አስጠነቀቃቸው። እግዚአብሔር ራብን በአገራቸው ላይ አመጣ፤ ምግባቸውንም ሁሉ አጠፋ። ነገር ግን ከእነርሱ አንዱን ሰው አስቀድሞ ላከ፤ እርሱም እንደ ባሪያ የተሸጠው ዮሴፍ ነበር። እግሮቹ በእግር ብረት ታስረው ነበር፤ በአንገቱም የብረት ቀለበት ነበር። ዮሴፍ ራሱ አስቀድሞ የተናገረው እስኪፈጸም ድረስና የእግዚአብሔር ቃል ትክክለኛነቱን እስኪያረጋግጥለት ድረስ ነው። ከዚያ በኋላ የግብጽ ንጉሥ ዮሴፍን ነጻ አደረገው።
መዝሙር 105:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሃሌ ሉያ! ጌታን አመስግኑ ስሙንም ጥሩ፥ ለአሕዛብም ድንቅ ሥራውን አውሩ። ተቀኙለት፥ ዘምሩለት፥ ተአምራቱንም ሁሉ ተናገሩ። በቅዱስ ስሙ ክበሩ፥ ጌታን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው። ጌታንና ኃይሉን ፈልጉ፥ ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ። አገልጋዮቹ የአብርሃም ዘር፥ ለእርሱም የተመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ የሠራውን ድንቅ ሥር አስቡ፥ ተአምራቱን የተናገረውንም ፍርድ። እርሱ ጌታ አምላካችን ነው፥ ፍርዱ በምድር ሁሉ ላይ ነው። ቃል ኪዳኑን ለዘለዓለም፥ እስከ ሺህ ትውልድ ያዘዘውን ቃሉን አሰበ፥ ከአብርሃም ጋር ያደረገውን ኪዳን፥ ለይስሐቅም የማለውን፥ ለያዕቆብ ሥርዓት እንዲሆን፥ ለእስራኤልም የዘለዓለም ኪዳን እንዲሆን አጸና፥ እንዲህም አለ፦ ለአንተ የከነዓንን ምድር የተመደበላችሁን ርስታችሁን እሰጣለሁ፥ ይህም የሆነው እነርሱ በቍጥር አነስተኛና፥ ለሀገሩም እንግዶች በነበሩበት ጊዜ ነው። ከሕዝብ ወደ ሕዝብ፥ ከመንግሥታትም ወደ ሌላ ሕዝብ አለፉ። የቀባኋቸውን አትንኩ፥ በነቢያቴም ላይ ክፉ አታድርጉ ብሎ፥ ሰው ግፍ ያደርግባቸው ዘንድ አልፈቀደም፥ ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ። በምድር ላይ ራብን ጠራ፥ የእህልን ኃይል ሁሉ ሰበረ። በፊታቸው ሰውን ላከ፥ ዮሴፍ ለባርነት ተሸጠ። እግሮቹም በእግር ብረት ደከሙ፥ እርሱም በብረት ውስጥ ገባ። ቃሉ እስኪመጣለት ድረስ፥ የጌታ ቃል ፈተነው። ንጉሥ ላከና ፈታው፥ የአሕዛብም አለቃ አስፈታው።