መዝሙር 104:24-30
መዝሙር 104:24-30 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሕዝቡንም እጅግ አበዛቸው፥ ከጠላቶቻቸውም ይልቅ አበረታቸው። ሕዝቡን ይጠሉ ዘንድ በባሪያዎቹም ላይ ይተነኰሉ ዘንድ ልባቸውን ለወጠ። ባሪያውን ሙሴን፥ የመረጠውንም አሮንን ላከ። የተአምራቱን ቃል በላያቸው ድንቁንም በካም ምድር አደረገ። ጨለማንም ላከ ጨለመባቸውም፤ ቃሉንም መራራ አደረጉት። ውኃቸውን ደም አደረገ፥ ዓሦቻቸውንም ገደለ። ምድራቸው በንጉሦቻቸው ቤቶች ጓጕንቸሮችን አወጣች።
መዝሙር 104:24-30 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ብዙ ነው! ሁሉን በጥበብ ሠራህ፤ ምድርም በፍጥረትህ ተሞላች። ይህች ባሕር ሰፊና የተንጣለለች ናት፤ ታላላቅና ታናናሽ እንስሳት፣ ስፍር ቍጥር የሌላቸውም ነፍሳት በውስጧ አሉ። መርከቦች በላይዋ ይመላለሳሉ፤ አንተ የፈጠርኸውም ሌዋታን በውስጧ ይፈነጫል። ምግባቸውን በወቅቱ ትሰጣቸው ዘንድ፣ እነዚህ ሁሉ አንተን ተስፋ ያደርጋሉ። በሰጠሃቸውም ጊዜ፣ አንድ ላይ ያከማቻሉ፤ እጅህንም ስትዘረጋ፣ በመልካም ነገር ይጠግባሉ። ፊትህን ስትሰውር፣ በድንጋጤ ይሞላሉ፤ እስትንፋሳቸውንም ስትወስድባቸው ይሞታሉ፤ ወደ ዐፈራቸውም ይመለሳሉ። መንፈስህን ስትልክ፣ እነርሱ ይፈጠራሉ፤ የምድርንም ገጽ ታድሳለህ።
መዝሙር 104:24-30 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ብዙ ነገሮችን ፈጥረሃል፤ ሁሉንም በጥበብ አድርገሃል፤ ምድር አንተ በፈጠርካቸው ነገሮች ተሞልታለች። ከቊጥር በላይ በሆኑ ታላላቅና ታናናሽ ሕያዋን ፍጥረቶች የተሞላው ትልቁና ሰፊው ባሕር እነሆ፥ በላዩ መርከቦች ይመላለሳሉ፤ በውስጡም አንተ የፈጠርከው ሌዋታን የተባለ ታላቅ ዘንዶ ይጫወታል። እነዚህ ሁሉ ምግባቸውን በየጊዜው እንድትሰጣቸው ተስፋ የሚያደርጉት አንተን ነው። አንተ ምግብ ስትሰጣቸው እነርሱም ይመገባሉ፤ አንተ እጅህን ስትዘረጋ እነርሱም መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ በልተው ይጠግባሉ። አንተ ስትለያቸው ሁሉም ይደነግጣሉ፤ እስትንፋሳቸውን ስትወስድባቸውም ይሞታሉ፤ ወደ ተገኙበትም ዐፈር ይመለሳሉ። እስትንፋስ ስትሰጣቸው ግን ይፈጠራሉ፤ ለምድርም አዲስ ሕይወት ትሰጣለህ።
መዝሙር 104:24-30 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ ሥራህ እጅግ ብዙ ነው፥ ሁሉን በጥበብ አደረግህ፥ ምድርም ከፍጥረትህ ተሞላች። ይህች ባሕር ታላቅና ሰፊ ናት፥ በዚያ ስፍር ቍጥር የሌለው ተንቀሳቃሽ፥ ታላላቆችና ታናናሾች እንስሶች አሉ። በዚያ ላይ መርከቦች ይሄዳሉ፥ በዚያም ላይ የፈጠርኸው ዘንዶ ያጫውትሃል። ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸው ዘንድ እነዚህ ሁሉ አንተን ተስፋ ያደርጋሉ። በምትሰጣቸውም ጊዜ ይሰበስባሉ፥ እጅህን ትከፍታለህ፥ ከመልካም ነገርም ይጠግባሉ። ፊትህን ስትሰውር ይደነግጣሉ፥ ነፍሳቸውን ታወጣለህ ይሞታሉም፥ ወደ አፈራቸውም ይመለሳሉ። መንፈስህን ትልካለህ ይፈጠራሉም፥ የምድርንም ፊት ታድሳለህ።