መዝሙር 104:1-35
መዝሙር 104:1-35 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ስሙንም ጥሩ፥ ለአሕዛብም ሥራውን ንገሩ። ተቀኙለት፥ ዘምሩለት፥ ተአምራቱንም ሁሉ ተናገሩ። በቅዱስ ስሙም ትከብራላችሁ። እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው፤ እግዚአብሔርን ፈልጉት፥ ትጸናላችሁም፤ ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ። የሠራውን ድንቅ ዐስቡ፥ ተአምራቱን፥ የአፉንም ፍርድ። ባሪያዎቹ የአብርሃም ዘር፥ ለእርሱም የተመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ እርሱ እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤ ፍርዱ በምድር ሁሉ ነው። ለዘለዓለም የሚኖር ቃል ኪዳኑን፥ እስከ ሺህ ትውልድ ያዘዘውን ቃሉን ዐሰበ። ለአብርሃም የሠራለትን፥ ለይስሐቅም የማለውን፤ ለያዕቆብ ምስክርነትን አጸና። ለእስራኤልም ለዘለዓለም የሚኖር ኪዳኑን፤ እንዲህም አለው፥ “ለአንተ የከነዓንን ምድር፥ የርስታችሁ ገመድ ትሆናችሁ ዘንድ እሰጣለሁ፤” እነርሱ በቍጥር እጅግ ጥቂቶችና፥ በውስጧ ስደተኞች ሲሆኑ። ከሕዝብ ወደ ሕዝብ፥ ከነገሥታት ወደ ሌላ ሕዝብ አለፉ። ሰው ግፍ ያደርግባቸው ዘንድ አልተወም፥ ስለ እነርሱም ነገሥታቱን ገሠጸ። የቀባኋቸውን አትዳስሱ፥ በነቢያቴም ላይ ክፉ አታድርጉ። በምድር ላይ ራብን አመጣ፥ የእህልን ኀይል ሁሉ አጠፋ። በፊታቸው ሰውን ላከ፤ ዮሴፍ ተሸጠ፥ አገልጋይም ሆነ። እግሮቹም በእግር ብረት ሰለሰሉ፥ ሰውነቱም ከብረት አመለጠች። ቃሉ ሳይደርስ፥ የእግዚአብሔር ቃል ፈተነው። ንጉሥ ላከ፥ ፈታውም፥ የሕዝብም አለቃ አድርጎ ሾመው። የቤቱ ጌታም አደረገው፥ በገንዘቡ ሁሉ ላይ ገዢ አደረገው፥ አለቆቹን ሁሉ እንደ እርሱ ይገሥጽ ዘንድ፥ ሽማግሌዎቹንም እንደ እርሱ ጥበበኞች ያደርጋቸው ዘንድ። እስራኤልም ወደ ግብፅ ገባ፥ ያዕቆብም በካም ምድር ተቀመጠ። ሕዝቡንም እጅግ አበዛቸው፥ ከጠላቶቻቸውም ይልቅ አበረታቸው። ሕዝቡን ይጠሉ ዘንድ በባሪያዎቹም ላይ ይተነኰሉ ዘንድ ልባቸውን ለወጠ። ባሪያውን ሙሴን፥ የመረጠውንም አሮንን ላከ። የተአምራቱን ቃል በላያቸው ድንቁንም በካም ምድር አደረገ። ጨለማንም ላከ ጨለመባቸውም፤ ቃሉንም መራራ አደረጉት። ውኃቸውን ደም አደረገ፥ ዓሦቻቸውንም ገደለ። ምድራቸው በንጉሦቻቸው ቤቶች ጓጕንቸሮችን አወጣች። እርሱ ተናገረ፥ የውሻ ዝንብ ትንኝም በምድራቸው ሁሉ መጡ። ዝናባቸውን በረዶ አደረገው፥ እሳትም በምድራቸው ነደደ። ወይናቸውንና በለሳቸውን መታ፥ የሀገራቸውንም ዛፍ ሁሉ ሰበረ። ተናገረ፥ አንበጣም፥ ስፍር ቍጥር የሌለውም ኵብኵባ መጣ፥ የምድራቸውንም ፍሬ ሁሉ በላ የተግባራቸውን ሁሉ መጀመሪያ በላ፥
መዝሙር 104:1-35 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ፤ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ አንተ እጅግ ታላቅ ነህ፤ ክብርንና ግርማን ለብሰሃል። ብርሃንን እንደ ሸማ ተጐናጽፈሃል፤ ሰማያትንም እንደ ድንኳን መጋረጃ ዘረጋህ፤ የእልፍኝህን አግዳሚ በውሆች ላይ አኖርህ፤ ደመናትን ሠረገላህ አደረግህ፤ በነፋስ ክንፍ ትሄዳለህ። መላእክትህን መንፈስ፣ አገልጋዮችህንም የእሳት ነበልባል ታደርጋለህ። ለዘላለም እንዳትናወጥ፣ ምድርን በመሠረቷ ላይ አጸናት። በጥልቁ እንደ ልብስ ሸፈንሃት፤ ውሆችም ከተራሮች በላይ ቆሙ። በገሠጽሃቸው ጊዜ ግን ፈጥነው ሄዱ፤ የነጐድጓድህንም ድምፅ በሰሙ ጊዜ ሸሹ። በተራሮች ላይ ፈሰሱ፤ ወዳዘጋጀህላቸው ስፍራ፣ ወደ ሸለቆዎች ወረዱ። ተመልሰው ምድርን እንዳይሸፍኑ፣ ዐልፈውም እንዳይመጡ ድንበር አበጀህላቸው። ምንጮችን በሸለቆ ውስጥ እንዲሄዱ አደረግህ፤ በተራሮችም መካከል ይፈስሳሉ፤ የዱር እንስሳትም ከዚያ ይጠጣሉ፤ የሜዳ አህዮችም ጥማቸውን ይቈርጣሉ። የሰማይ ወፎች ጐጇቸውን በወንዞቹ ዳር ይሠራሉ፤ በቅርንጫፎችም መካከል ይዘምራሉ። ከላይ ከእልፍኝህ ተራሮችህን ታጠጣለህ፤ ምድርም በሥራህ ፍሬ ትረካለች። ከምድር ምግብን ታወጣ ዘንድ፣ ለእንስሳት ሣርን፣ ለሰው ልጆች ሥራ ዕፀዋትን ታበቅላለህ፤ የሰውን ልብ ደስ የሚያሰኝ ወይን፣ ፊቱን የሚያወዛ ዘይት፣ ልቡን የሚያበረታ እህል በዚህ ይገኛል። ደግሞም የእግዚአብሔር ዛፎች፣ እርሱ የተከላቸውም የሊባኖስ ዝግባዎች ጠጥተው ይረካሉ፤ ወፎች ጐጇቸውን በዚያ ይሠራሉ፤ ሽመላ በጥዶቹ ውስጥ ማደሪያ ታገኛለች። ረዣዥሙ ተራራ የዋሊያ መኖሪያ፣ የዐለቱም ዋሻዎች የሽኮኮ መሸሸጊያ ናቸው። ጨረቃን የወቅቶች መለያ አደረግሃት፤ ፀሓይም የምትጠልቅበትን ጊዜ ታውቃለች። ጨለማን ታመጣለህ፤ ሌሊትም ይሆናል፤ የዱር አራዊትም ሁሉ በዚህ ጊዜ ወጥተው ይራወጣሉ። የአንበሳ ግልገሎች ምግብ ፍለጋ ይጮኻሉ፤ የሚበሉትንም ከእግዚአብሔር ይሻሉ። ፀሓይ በወጣች ጊዜም ይመለሳሉ፤ በየጐሬያቸውም ገብተው ይተኛሉ። ሰውም ወደ ሥራው ይሄዳል፤ እስኪመሽም በተግባሩ ላይ ይሰማራል። እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ብዙ ነው! ሁሉን በጥበብ ሠራህ፤ ምድርም በፍጥረትህ ተሞላች። ይህች ባሕር ሰፊና የተንጣለለች ናት፤ ታላላቅና ታናናሽ እንስሳት፣ ስፍር ቍጥር የሌላቸውም የሚርመሰመሱ ፍጥረታት በውስጧ አሉ። መርከቦች በላይዋ ይመላለሳሉ፤ አንተ የፈጠርኸውም ሌዋታን በውስጧ ይፈነጫል። ምግባቸውን በወቅቱ ትሰጣቸው ዘንድ፣ እነዚህ ሁሉ አንተን ተስፋ ያደርጋሉ። በሰጠሃቸውም ጊዜ፣ አንድ ላይ ያከማቻሉ፤ እጅህንም ስትዘረጋ፣ በመልካም ነገር ይጠግባሉ። ፊትህን ስትሰውር፣ በድንጋጤ ይሞላሉ፤ እስትንፋሳቸውንም ስትወስድባቸው ይሞታሉ፤ ወደ ዐፈራቸውም ይመለሳሉ። መንፈስህን ስትልክ፣ እነርሱ ይፈጠራሉ፤ የምድርንም ገጽ ታድሳለህ። የእግዚአብሔር ክብር ለዘላለም ጸንቶ ይኑር፤ እግዚአብሔር በሥራው ደስ ይበለው፤ እርሱ ምድርን ሲመለከት፣ ትንቀጠቀጣለች፤ ተራሮችም እርሱ ሲዳስሳቸው ይጤሳሉ። በሕይወት ሳለሁ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ ቆሜ እስከ ሄድሁ ድረስም አምላኬን እወድሳለሁ። እኔ በእግዚአብሔር ደስ እንደሚለኝ፣ የልቤ ሐሳብ እርሱን ደስ ያሠኘው። ኃጥኣን ከምድር ገጽ ይጥፉ፤ ዐመፀኞች ከእንግዲህ አይገኙ።
መዝሙር 104:1-35 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ነፍሴ ሆይ! እግዚአብሔርን አመስግኚ! እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! እንዴት ታላቅ ነህ! ግርማንና ክብርን ለብሰሃል። ብርሃንንም እንደ ልብስ ተጐናጽፈሃል፤ ሰማይን እንደ ድንኳን ዘርግተሃል። በጠፈር ላይ ካለው ውሃ በላይ ቤትህን ሠርተሃል፤ ደመና ሠረገላህ ነው፤ በነፋስ ክንፎችም ትሄዳለህ። ነፋስ መልእክተኛህ ነው፤ የእሳት ነበልባልም አገልጋይህ ነው። ምድርን በመሠረትዋ ላይ አጽንተህ አቆምሃት፤ ከቶም አትናወጥም። ውቅያኖስን እንደ ልብስ አለበስካት፤ ውሃውም ተራራዎችን ሸፈነ። ውሃውን በገሠጽከው ጊዜ ከፊትህ ሸሸ፤ የትእዛዝህን ድምፅ በሰማ ጊዜ በፍጥነት ሮጠ። አንተ ወዳዘጋጀህለት ስፍራ፥ ወደ ተራራዎች ላይና ወደ ሸለቆዎች ውስጥ ፈሰሰ። ዳግመኛ ምድርን እንዳይሸፍንም የማይጥሰውን ወሰን አበጀህለት። ምንጮች በሸለቆ ውስጥ እንዲፈስሱ፥ ወንዞችም በተራራዎች መካከል እንዲወርዱ አደረግህ። በዚህ ዐይነት የዱር አውሬዎች የሚጠጡት ውሃ ያገኛሉ፤ የሜዳ አህዮችም ጠጥተው ጥማቸውን ያረካሉ። በነዚህም ምንጮችና ወንዞች አጠገብ ባሉት ዛፎች ላይ፥ ወፎች ጎጆአቸውን ሠርተው ያዜማሉ። ከሰማይ ዝናብን በተራሮች ላይ ታወርዳለህ፤ ምድርም በምትሰጣት በረከት ትሞላለች። ሣርን ለእንስሶች ታበቅላለህ፤ አትክልትንም ለሰው ልጆች ጥቅም እንዲውል ታደርጋለህ፤ በዚህ ዐይነት ሰው ምግብ የሚሆነውን ዘርቶ ይሰበስባል። ስለዚህ ልቡን ደስ የሚያሰኝ የወይን ጠጅ፥ ፊቱን የሚያበራ ዘይትና ብርታት የሚሰጠውን ምግብ ያዘጋጃል። እግዚአብሔር የተከላቸው የሊባኖስ ዛፎች በቂ ዝናብ ያገኛሉ፤ በላያቸውም ወፎች ጎጆዎቻቸውን ይሠራሉ፤ ሸመላዎችም በእነዚያ ዛፎች ላይ መኖሪያቸውን ያበጃሉ። ዋልያዎች በከፍተኛ ተራራዎች ላይ ይገኛሉ፤ ሽኮኮዎችም በተሰነጠቁ አለቶች ውስጥ ይኖራሉ። ጨረቃን የወቅቶች ምልክት እንድትሆን፥ ፀሐይ የሚጠልቅበትን ጊዜ እንዲያውቅ አድርገሃል። አንተ ጨለማን ፈጠርክ፤ ሌሊትም ሆነ፤ በጨለማም የዱር አውሬዎች ሁሉ ይወጣሉ። እግዚአብሔር የሚያዘጋጀውን ምግብ ሲያድኑ የአንበሳ ደቦሎች ያገሣሉ። ፀሐይ በሚወጣበት ጊዜ ሾልከው ይሄዳሉ፤ ተመልሰው በየመኖሪያቸው ውስጥ ይተኛሉ። ከዚህ በኋላ ሰዎች ለሥራ ይሰማራሉ፤ እስከሚመሽም ድረስ ሲሠሩ ይውላሉ። እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ብዙ ነገሮችን ፈጥረሃል፤ ሁሉንም በጥበብ አድርገሃል፤ ምድር አንተ በፈጠርካቸው ነገሮች ተሞልታለች። ከቊጥር በላይ በሆኑ ታላላቅና ታናናሽ ሕያዋን ፍጥረቶች የተሞላው ትልቁና ሰፊው ባሕር እነሆ፥ በላዩ መርከቦች ይመላለሳሉ፤ በውስጡም አንተ የፈጠርከው ሌዋታን የተባለ ታላቅ ዘንዶ ይጫወታል። እነዚህ ሁሉ ምግባቸውን በየጊዜው እንድትሰጣቸው ተስፋ የሚያደርጉት አንተን ነው። አንተ ምግብ ስትሰጣቸው እነርሱም ይመገባሉ፤ አንተ እጅህን ስትዘረጋ እነርሱም መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ በልተው ይጠግባሉ። አንተ ስትለያቸው ሁሉም ይደነግጣሉ፤ እስትንፋሳቸውን ስትወስድባቸውም ይሞታሉ፤ ወደ ተገኙበትም ዐፈር ይመለሳሉ። እስትንፋስ ስትሰጣቸው ግን ይፈጠራሉ፤ ለምድርም አዲስ ሕይወት ትሰጣለህ። የእግዚአብሔር ክብር ለዘለዓለም ይኑር! እግዚአብሔር በፈጠረው ነገር ሁሉ ደስ ይበለው። ምድርን ሲመለከት ትንቀጠቀጣለች፤ ተራራዎችን ሲነካ እነርሱም ይጤሳሉ። በሕይወት ዘመኔ ሁሉ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ በሕይወትም እስካለሁ ድረስ ለአምላኬ የምስጋና መዝሙር አቀርባለሁ። ደስታዬ በእርሱ ስለ ሆነ እርሱም በማቀርብለት የተመስጦ ጸሎት ደስ ይበለው። ኃጢአተኞች ከምድር ላይ ይጥፉ! ግፍ አድራጊዎችም ይደምሰሱ!
መዝሙር 104:1-35 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ነፍሴ ሆይ፥ ጌታን ባርኪ፥ አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ አንተ እጅግ ታላቅ ነህ፥ ክብርንና ግርማን ለበስህ። ብርሃንን እንደ ልብስ ለበስህ፥ ሰማይንም እንደ ድንኳን መጋረጃ ዘረጋህ፥ እልፍኙን በውኃ የሚሠራ፥ ሠረገላውን ደመና የሚያደርግ፥ በነፋስ ክንፍም የሚሄድ፥ ነፋሳትን መልእክተኞቹ የሚያደርግ፥ የእሳት ነበልባልም አገልጋዮቹ። ለዘለዓለም እንዳትናወጥ ምድርን በመሠረትዋ ላይ መሠረታት። በጥልቅ እንደ ልብስ ከደንሃት፥ በተራሮችም ላይ ውኆች ይቆማሉ። ከቁጣህም ይሸሻሉ፥ ከነጐድጓድህም ድምፅ ይደነብራሉ፥ ወደ ተራሮች ይወጣሉ፥ ወደ ቈላዎች፥ ወዳዘጋጀህላቸው ስፍራ ይወርዳሉ፥ እንዳያልፉትም ድንበር አደረግህላቸው ተመልሰው ምድርን እንዳይከድኑ። ምንጮችን ወደ ሸለቆዎች ይልካል፥ በተራሮችም መካከል ያልፋሉ፥ የዱር አራዊትን ሁሉ ያጠጣሉ፥ የበረሃ አህያዎችም ጥማቸውን ያረካሉ። የሰማይም ወፎች በእነርሱ ዘንድ ያድራሉ፥ በቅጠሎች መካከል ያዜማሉ ይጮኻሉ። ተራሮችን ከላይ የምታጠጣቸው፥ ከሥራህ ፍሬ ምድር ትጠግባለች። እንጀራን ከምድር ያወጣ ዘንድ ሣርን ለእንስሳ፥ ለምለሙንም ለሰው ልጆች ጥቅም ያበቅላል። ወይን የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል፥ ዘይትም ፊትን ያበራል፥ እህልም የሰውን ጉልበት ያጠነክራል። የጌታ ዛፎች እርሱም የተከላቸው የሊባኖስ ዝግባዎች ይጠግባሉ። በዚያም ወፎች ጎጆአቸውን ይሠራሉ፥ ሽመላዎችም ከበላያቸው ቤታቸውን ያበጃሉ። ረጃጅም ተራራዎች ለዋላዎች፥ ድንጋዮችም ለእሽኮኮች መሸሻ ናቸው። ወቅቶችን ለማመልከት ጨረቃን አደረግህ፥ ፀሐይም መግቢያውን ያውቃል። ጨለማን ታስቀምጣለህ፥ ሌሊትም ይሆናል፥ በእርሱም የዱር አራዊት ሁሉ ይወጡበታል። የአንበሳ ግልገሎች ለመንጠቅ ይጮኻሉ፥ ከእግዚአብሔርም ምግባቸውን ይሻሉ። ፀሐይ ስትወጣ ይሰበሰባሉ፥ በየዋሻቸውም ይተኛሉ። ሰው ወደ ተግባሩ፥ እስኪመሽም ድረስ ወደ ሥራው ይወጣል። አቤቱ፥ ሥራህ እጅግ ብዙ ነው፥ ሁሉን በጥበብ አደረግህ፥ ምድርም ከፍጥረትህ ተሞላች። ይህች ባሕር ታላቅና ሰፊ ናት፥ በዚያ ስፍር ቍጥር የሌለው ተንቀሳቃሽ፥ ታላላቆችና ታናናሾች እንስሶች አሉ። በዚያ ላይ መርከቦች ይሄዳሉ፥ በዚያም ላይ የፈጠርኸው ዘንዶ ያጫውትሃል። ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸው ዘንድ እነዚህ ሁሉ አንተን ተስፋ ያደርጋሉ። በምትሰጣቸውም ጊዜ ይሰበስባሉ፥ እጅህን ትከፍታለህ፥ ከመልካም ነገርም ይጠግባሉ። ፊትህን ስትሰውር ይደነግጣሉ፥ ነፍሳቸውን ታወጣለህ ይሞታሉም፥ ወደ አፈራቸውም ይመለሳሉ። መንፈስህን ትልካለህ ይፈጠራሉም፥ የምድርንም ፊት ታድሳለህ። የጌታ ክብር ለዘለዓለም ይሁን፥ ጌታ በሥራው ደስ ይለዋል። ምድርን ያያል እንድትንቀጠቀጥም ያደርጋል፥ ተራሮችን ይዳስሳል፥ ይጤሳሉም። በሕይወቴ ሳለሁ ለጌታ እቀኛለሁ፥ ለአምላኬም በምኖርበት ዘመን ሁሉ እዘምራለሁ። ቃሌ ለእርሱ ይጣፍጠው፥ እኔም በጌታ ደስ ይለኛል። ኀጥኣን ከምድር ይጥፉ፥ ዓመፀኞች ከእንግዲህ አይገኙ። ነፍሴ ሆይ፥ ጌታን ባርኪ። ሃሌ ሉያ።