ምሳሌ 31:10-20
ምሳሌ 31:10-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ጠባየ መልካምን ሚስት ማን ያገኛታል? ከቀይ ዕንቍ እጅግ ትበልጣለች። ባሏ ሙሉ በሙሉ ይተማመንባታል፤ የሚጐድልበትም ነገር የለም። በሕይወት ዘመኗ ሁሉ፣ መልካም ታደርግለታለች እንጂ አትጐዳውም። የበግ ጠጕርና የተልባ እግር መርጣ፣ ሥራ በሚወድዱ እጆቿ ትፈትላቸዋለች። እንደ ንግድ መርከብ፣ ምግቧን ከሩቅ ትሰበስባለች። ገና ሳይነጋ ትነሣለች፤ ለቤተ ሰቧ ምግብ፣ ለሴት አገልጋዮቿም ድርሻቸውን ትሰጣለች። ራሷ አስባ የዕርሻ መሬት ትገዛለች፤ በምታገኘውም ገንዘብ ወይን ትተክላለች። ብርታትን ታጥቃ ሥራዋን ታከናውናለች፤ ክንዶቿም ለሥራ ብርቱ ናቸው። ሥራዋ ትርፋማ መሆኑን ታስተውላለች፤ በሌሊትም መብራቷ አይጠፋም። በእጇ እንዝርት ትይዛለች፤ በጣቶቿም ዘንጉን ታሾራለች። ክንዶቿን ለድኾች ትዘረጋለች፣ እጆቿንም ለችግረኞች ፈታ ታደርጋለች።
ምሳሌ 31:10-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ጠባየ መልካምን ሚስት ማን ሊያገኛት ይችላል? እርስዋ ከዕንቊ ይልቅ የከበረች ናት። ባልዋ ይተማመንባታል፤ የሚፈልገውን ነገር ሁሉ አያጣም። በምትኖርበት ዘመን ሁሉ መልካም ነገር ታደርግለታለች እንጂ ክፉ ነገር አታደርግበትም። ከሱፍ ክርና ከበፍታ ልብስ በመስፋት ደስ እያላት በሥራ ትጠመዳለች። እንደ ነጋዴ መርከብ ወደ ሩቅ ስፍራዎች በመሄድ ልዩ ልዩ ዐይነት ምግቦችን ትሰበስባለች። ለቤተሰብዋ ምግብ ለማዘጋጀትና ለሠራተኞችዋ ሥራ ለማከፋፈል ገና ሳይነጋ ትነሣለች። ደኅና መሬት ፈልጋ ትገዛለች፤ ሠርታ በምታገኘውም ገንዘብ የወይን አትክልት ቦታ ታዘጋጃለች። እርስዋ ትጉህ ሠራተኛ ከመሆንዋም በላይ በሥራዋ ብርቱ ናት። የምትሠራው ሁሉ ዋጋ እንዳለው ታውቃለች፤ ማታም ስትሠራ ስለምታመሽ መብራትዋ አይጠፋም፤ የነደፈችውን አመልማሎ በራስዋ እንዝርት ፈትላ ልብስዋን ትሠራለች። ለድኾችና ለችግረኞች ትለግሣለች።
ምሳሌ 31:10-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ልባም ሴትን ማን ሊያገኛት ይችላል? ዋጋዋ ከቀይ ዕንቁ እጅግ ይበልጣል። የባሏ ልብ ይታመንባታል። መልካም ነገር አይጐድልበትም። ዕድሜዋን ሙሉ መልካም ታደርግለታለች፥ ክፉም አታደርግም። የበግ ጠጉርና የተልባ እግር ትፈልጋለች፥ በእጆችዋም ደስ ብሎአት ትሠራለች። እርሷ እንደ ነጋዴ መርከብ ናት፥ ከሩቅ አገር ምግብዋን ትሰበስባለች። ገና ሳይነጋ ትነሣለች ለቤትዋም ሰዎች ምግባቸውን፥ ለአገልጋዮችዋም ሥራ ትሰጣለች። እርሻንም ተመልክታ ትገዛለች፥ ከእጅዋም ፍሬ ወይን ትተክላለች። ወገብዋን በኃይል ትታጠቃለች፥ ክንድዋንም ታበረታለች። ማትረፍዋን ታስተውላለች፥ መብራትዋ በሌሊት አይጠፋም። እጅዋን ወደ አመልማሎ ትዘረጋለች፥ ጣቶችዋም እንዝርትን ይይዛሉ። እጅዋን ወደ ድሀ ትዘረጋለች፥ ወደ ችግረኛም እጅዋን ትሰድዳለች።