ምሳሌ 28:1-7
ምሳሌ 28:1-7 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ክፉ ሰው ማንም ሳያሳድደው ይሸሻል፤ ጻድቅ ግን እንደ አንበሳ ልበ ሙሉ ነው። አገር ስታምፅ፣ ገዦቿ ይበዛሉ፤ አስተዋይና ዐዋቂ ሰው ግን ሥርዐትን ያሰፍናል። ድኾችን የሚያስጨንቅ ሰው፣ ሰብል እንደሚያጠፋ ኀይለኛ ዝናብ ነው። ሕግን የሚተዉ ክፉዎችን ያወድሳሉ፤ ሕግን የሚጠብቁ ግን ይቋቋሟቸዋል። ክፉዎች ፍትሕን አያስተውሉም፤ እግዚአብሔርን የሚሹ ግን ሙሉ በሙሉ ያውቁታል። በአካሄዱ ነውር የሌለበት ድኻ፣ መንገዱ ጠማማ ከሆነ ባለጠጋ ይሻላል። ሕግን የሚጠብቅ አስተዋይ ልጅ ነው፤ ከሆዳሞች ጋር ጓደኛ የሚሆን ግን አባቱን ያዋርዳል።
ምሳሌ 28:1-7 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኃጢአተኞች ማንም ሳያሳድዳቸው ይሸሻሉ፤ ደግ ሰዎች ግን እንደ አንበሳ ደፋሮች ናቸው። አንድ ሕዝብ ኃጢአተኛ ሲሆን መሪዎች ይለዋወጡበታል፤ ዐዋቂና አስተዋይ መሪ ሲኖረው ግን ለረዥም ጊዜ ጽኑ ሕዝብ ይሆናል። ድኾችን የሚጨቊን መሪ ሰብልን እንደሚያጠፋ ኀይለኛ ዝናብ ነው። ሕግን የማያከብሩ ሰዎች ክፉ ሰዎችን ያመሰግናሉ፤ ሕግን የሚያከብሩ ግን ክፉዎችን ይቃወማሉ። ክፉ ሰዎች ፍትሕ ምን እንደ ሆነ አያውቁም፤ እግዚአብሔርን የሚፈልጉ ሰዎች ግን በሙሉ ያስተውሉታል። ሀብታም ሆኖ አታላይ ከመሆን ይልቅ ድኻ ሆኖ ታማኝ መሆን ይሻላል። ሕግን የሚያከብር ልጅ ጥበበኛ ነው፤ ከማይረቡ ወስላቶች ጋር ወዳጅ የሚሆን ልጅ ግን አባቱን ያሳፍራል።
ምሳሌ 28:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ክፉ ማንም ሳያሳድደው ይሸሻል፥ ጻድቅ ግን እንደ አንበሳ ተማምኖ ይኖራል። አገሪቱ ዓመፀኛ ስትሆን መሪዎችዋ ብዙ ሆኑ፥ በአስተዋይና በአዋቂ ሰው ግን ዘመንዋ ይረዝማል። ድሆችን የሚያስጨንቅ ድሃ ሰው እህልን እንደሚያጠፋ እንደ ዶፍ ዝናብ ነው። ሕግን የሚተዉ ሰዎች ክፉዎችን ያመሰግናሉ፥ ሕግ ጠባቂዎች ግን ይቃወሟቸዋል። ክፉዎች ሰዎች ፍትሕን አያስተውሉም፥ ጌታን የሚሹ ግን ሁሉን ያስተውላሉ። በጠማማ መንገድ ከሚሄድ ሀብታም ያለ ነውር የሚሄድ ድሀ ይሻላል። ሕግን የሚጠብቅ አስተዋይ ልጅ ነው፥ ራሳቸውን የማይቆጣጠሩትን የሚከተል ግን አባቱን ያሳፍራል።