የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ምሳሌ 28

28
1ኃጢአተኞች ማንም ሳያሳድዳቸው ይሸሻሉ፤ ደግ ሰዎች ግን እንደ አንበሳ ደፋሮች ናቸው።
2አንድ ሕዝብ ኃጢአተኛ ሲሆን መሪዎች ይለዋወጡበታል፤ ዐዋቂና አስተዋይ መሪ ሲኖረው ግን ለረዥም ጊዜ ጽኑ ሕዝብ ይሆናል።
3ድኾችን የሚጨቊን መሪ ሰብልን እንደሚያጠፋ ኀይለኛ ዝናብ ነው።
4ሕግን የማያከብሩ ሰዎች ክፉ ሰዎችን ያመሰግናሉ፤ ሕግን የሚያከብሩ ግን ክፉዎችን ይቃወማሉ።
5ክፉ ሰዎች ፍትሕ ምን እንደ ሆነ አያውቁም፤ እግዚአብሔርን የሚፈልጉ ሰዎች ግን በሙሉ ያስተውሉታል።
6ሀብታም ሆኖ አታላይ ከመሆን ይልቅ ድኻ ሆኖ ታማኝ መሆን ይሻላል።
7ሕግን የሚያከብር ልጅ ጥበበኛ ነው፤ ከማይረቡ ወስላቶች ጋር ወዳጅ የሚሆን ልጅ ግን አባቱን ያሳፍራል።
8በአራጣ በማበደርና ሰዎችን በመበዝበዝ የሚከብር ሰው ሀብቱ ሁሉ ለድኾች ልግሥና ለሚያደርግ ሰው ይተላለፋል።
9አንድ ሰው ሕግን ባያከብር ጸሎቱ በእግዚአብሔር ዘንድ አጸያፊ ይሆናል።
10እውነተኛውን ሰው አግባብቶ ወደ ክፉ መንገድ የሚመራ ባጠመደው ወጥመድ ይያዛል፤ ንጹሕ ሰው ግን የመልካም ሥራውን ዋጋ ያገኛል።
11ሀብታም ሰው ዘወትር ጥበበኛ የሆነ ይመስለዋል፤ አስተዋይ የሆነ ድኻ ግን የእርሱን ጠባይ መርምሮ ያውቃል።
12ደጋግ ሰዎች ድል በሚያደርጉበት ጊዜ ሰው ሁሉ ይደሰታል፤ ክፉ ሰዎች ሥልጣን በሚይዙበት ጊዜ ግን ሰው ሁሉ በሐዘን አንገቱን ይደፋል።
13ኃጢአቱን የሚደብቅ ኑሮው አይሳካለትም፤ ኃጢአቱን ተናዝዞ ዳግመኛ ኃጢአት ከመሥራት የሚቈጠብ ግን የእግዚአብሔርን ምሕረት ያገኛል።
14ሁልጊዜ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው የተባረከ ነው፤ እምቢተኛ የሚሆን ሰው ግን ችግር ላይ ይወድቃል።
15ድኾችን በጭካኔ የሚገዛ መሪ እንደሚያገሣ አንበሳና ተርቦ ምግቡን ለማደን እንደሚያደባ ድብ ነው።
16ማስተዋል የጐደለው መሪ ጨካኝ ይሆናል፤ ብዝበዛን የሚጠላ መሪ ግን ረጅም ዕድሜ ይኖረዋል።
17አንድ ሰው የሰውን ሕይወት ቢያጠፋ እስኪሞት ድረስ እየሸሸ ይኑር፤ ማንም ሰው አያስጠጋው።
18ታማኝ ሰው በሰላም ይኖራል፤ ጠማማ ሰው ግን በጒድጓድ ውስጥ ይወድቃል።
19ትጉህ ገበሬ በቂ ምግብ ይኖረዋል፤ በከንቱ ምኞት የሚመራ ግን እንደ ደኸየ ይኖራል።
20ታማኝ ሰው የተባረከ ሕይወት ይኖረዋል፤ ሀብታም ለመሆን የሚስገበገብ ሰው ግን ቅጣት ያገኘዋል።
21አድልዎ ማድረግ አይገባም፤ አንዳንድ ሰው ግን ቊራሽ እንጀራ ለማግኘት ብሎ ያደላል።
22ስስታም ሀብታም ለመሆን ሲጣደፍ ድኽነት በቶሎ የሚመጣበት መሆኑን አይገነዘብም።
23ሰውን ከማቈላመጥ ይልቅ እየመከረ የሚገሥጸውን ሰው በመጨረሻ ያመሰግነዋል።
24ከአባቱና ከእናቱ ሰርቆ “ኃጢአት አላደረግሁም” የሚል ሰው ከማንኛውም አጥፊ ሰው የተሻለ አይደለም።
25ስስታም ሰው ጠብን ያነሣሣል፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ሰው ግን ይበለጽጋል።
26በራሱ የሚታመን ሰው ሞኝ ነው፤ በጥበብ የሚመራ ሰው ግን በሰላም ይኖራል።
27ለድኾች የሚሰጥ ከቶ አይቸገርም፤ ድኾችን ላለማየት ዐይኖቹን የጨፈነ ግን በሰዎች ዘንድ የተረገመ ይሆናል።
28ክፉ ሰዎች ሲሾሙ ሰዎች ይደበቃሉ፤ እነርሱ ሲሻሩ ግን ጻድቃን ይበዛሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ