መጽሐፈ ምሳሌ 29

29
1ብዙ ጊዜ ተገሥጾ በእምቢተኛነቱ የሚጸና ሰው በድንገት ይሰበራል። ፈውስም አይኖረውም።
2ደጋግ ሰዎች ሲሾሙ ሕዝቦች ይደሰታሉ፤ ክፉ ሰዎች ሲሾሙ ግን ሕዝቦች ይጨነቃሉ።
3ጥበብን የሚወድ አባቱ ያስደስታል፤ አመንዝሮችን የሚከተል ግን ሀብቱን ያባክናል።
4ንጉሥ ፍትሕ እንዳይጓደል በሚያደርግበት ጊዜ ሀገሩን ያረጋጋል፤ ሕዝብን የሚበዘብዝ መሪ ግን ሀገሩን ወደ ጥፋት ያደርሳል።
5ወዳጆቹን የሚያቈላምጥ ሰው ለእግራቸው ወጥመድ ይዘረጋል።
6ክፉ ሰው የገዛ ኃጢአቱ ወጥመድ ሆኖ ይይዘዋል፥ ደግ ሰው ግን እየዘመረ ሐሤትን ያደርጋል።
7ደግ ሰው ስለ ድኾች መብት ይቈረቈራል፤ ክፉ ሰው ግን ለእንደዚህ ዐይነቱ ነገር ግድ አይኖረውም።
8ለሌሎች ሰዎች ደንታ የሌላቸው ፌዘኞች በከተማ ውስጥ ብጥብጥ ያነሣሣሉ፤ ጠቢባን ግን የደፈረሰውን ጸጥታ መልሰው ያረጋጋሉ።
9ጥበበኛ ሰው ሞኝን ሰው ከሶ ፍርድ ቤት ቢያቀርብ ሞኙ ሰው በቊጣና በሳቅ ሰላምን ይነሣል።
10ነፍሰ ገዳዮች ንጹሑን ሰው ይጠላሉ፤ ደጋግ ሰዎችንም ለመግደል ይፈልጋሉ።
11ሞኝ ሰው የቊጣ ስሜቱን ይገልጣል፤ ጥበበኛ ሰው ግን ቊጣውን በትዕግሥት ይገታል።
12አንድ መሪ ሐሰተኛ ወሬ የሚቀበል ከሆነ ባለሟሎቹ የሆኑ ባለሥልጣኖች ሁሉ ግፈኞች ይሆናሉ።
13ለድኻና እርሱንም ለሚጨቊነው ሰው የዐይን ብርሃን የሚሰጠው እግዚአብሔር ስለ ሆነ በብርሃን አጠቃቀም ሁለቱም እኩል ናቸው።
14አንድ ንጉሥ ለድኾች በቅን የሚፈርድ ከሆነ ለረዥም ዘመን ያስተዳድራል።
15ልጆችን መገሠጽና መቅጣት ጥበብ እንዲያገኙ ያደርጋል፤ ልጅ ስድ ዐደግ የሆነ እንደ ሆነ ግን እናቱን ያሳፍራል።
16ክፉ ሰዎች ሥልጣን ሲይዙ ሕግ መተላለፍ ይበዛል፤ ደጋግ ሰዎች ግን የክፉ ሰዎችን ውድቀት ሳያዩ አይሞቱም።
17ልጅህን ቅጣ፤ ዕረፍትና ሰላም በማግኘት ደስ ትሰኛለህ።
18ከእግዚአብሔር የሚገለጥ መመሪያ ባይኖር ሕዝብ መረን ይለቀቃል፤ የእግዚአብሔርን ሕግ የሚያከብር ሰው ግን የተባረከ ነው።
19አንድን አገልጋይ በቃል በመገሠጽ ብቻ ለማረም አይቻልም፤ የምትለው ነገር ቢገባው እንኳ አይታዘዝም።
20ሳያስብ በችኰላ ከሚናገር ሰው ይልቅ ሞኝ የተሻለ ተስፋ አለው።
21አንድ ባሪያ ከልጅነቱ ጀምሮ ተቀማጥሎ ካደገ መጨረሻው አያምርም።
22ቊጡ ሰው ጠብን ያነሣሣል፤ ግልፍተኛም ብዙ በደልን ይፈጽማል።
23ትምክሕተኛነት ወደ ውድቀት ያደርስሃል፤ ትሑት ከሆንክ ግን ትከበራለህ።
24ከሌባ ጋር የሚተባበር ራሱን የጠላ ሰው ነው፤ ቢምልም እንኳ እውነትን አይናገርም።
25ሰውን የሚፈራ ችግር ላይ ይወድቃል፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን በሰላም ይኖራል።
26ብዙ ሰዎች የባለሥልጣንን ርዳታ ይፈልጋሉ፤ ፍትሕ የሚገኘው ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ነው።
27ክፉ ሰዎች በደጋግ ሰዎች ዘንድ የተጠሉ ናቸው፤ ደጋግ ሰዎችም በክፉ ሰዎች ዘንድ ይጠላሉ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ